በየካቲት ወር ከሚታወሱት ክስተቶች ሌላኛው ደግሞ የሆሎታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ነው። የጦር ትምህርት ቤቱ የተመሰረተው ከ86 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 7 ቀን 1929 ዓ.ም ነው።
ከአዲስ አበባ በስተ ምእራብ ስላሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሆሎታ ገነት ከተማ ከአዲስ አበባ ባልተናነሰ ታሪካዊ መነሻ አላት። በ1903 ዓ.ም የመጀመሪያው በውሃ ኃይል የሚሰራ ወፍጮ የተተከለባት ታሪካዊ ከተማ መሆኗን የታሪክ ምሁሩ ሪቻርድ ፓንክረስት ጽፈውላታል።
ከተለያዩ የበይነ መረብ ገጾች ባገኘነው መረጃ፤ የከተማዋ ስም ሆሎታ (ኦለታ) ሲባል ገነት የሚለውን ስም የሰጧት ግን አፄ ምኒልክ እንደነበሩና ይህም ከቦታው ማራኪነት የተነሳ እንደነበር ታሪኩን የሚያውቁ መናገራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። መረጃዎቹ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግስታቸውን አዲስ ዓለም እና ሆሎታ ላይ ሰርተው እንደነበርም ይጠቁማሉ። ከቤተ መንግስታቸው ጋር ተያይዞም አሁን ማሰልጠኛው ባለበት ግቢ አቅራቢያ የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች። በጥምቀት ወቅት የኪዳነ ምህረት ታቦት በጦር ሰራዊቱ ታጅባ ወደ ጥምቀተ ባህር ትሸኝ ነበር ይባላል።
የሆሎታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በ1928 ዓ.ም በአምስት የስዊድን መኮንኖች አሰልጣኞች እገዛ ስራውን ጀመረ። ሆኖም ግን ወዲያው ፋሽሽት ጣልያን ሀገራችንን በመውረሩ የጦር ማሰልጠኛው በአግባቡ ስራውን ማከናወን አቃተው። በወቅቱ ስልጠና ይከታተሉ የነበሩ የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ ጦር ሰልጣኝ ብርቅ ተዋጊዎች ነበሩ። ወረራውን ተከትሎ ሰልጣኞቹም ሆኑ ስልጠናውን ያጠናቀቁ ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› በሚል አዲስ የአርበኞች እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጀመሩ።
የጥቁር አንበሳ ጦር በፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ወቅ በአርበኝነት የተሳተፉ የሆለታ ገነት ጦር ምሩቃን እና በውጭ የተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት ፀረ ፋሽሽት እንቅስቃሴ ነው። በጣሊያን ላይ ዘመናዊ የጦር ውጊያ በማሳየት ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ መንገድ ለሚዋጋው የኢትዮጵያ ገበሬ አርበኛ ዘመናዊ የውጊያ ስልትን በማስተማር የጥቁር አንበሳ ጦር ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም።
የጦር ትምህርት ቤቱ ፋሽስት ጣልያን ከሀገራችን ተባርሮ ንጉሰ ነገስቱ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በ1935 ዓ.ም እንደገና ተመሰረተ። የጦር ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ አንጋፋው በዓለማችንም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ከተመሰረቱ ጥቂት የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ለሀገራችን የጦር ሰራዊት ታሪክ አንዱ እና አይነተኛ ቅርስም ነው።
የጦር ትምህርት ቤቱ በዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ በ1990 ዓ.ም ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የሆሎታ ገነት ጦር አካዳሚ በሚል ይታወቅ የነበረውን የኢህአዴግ መንግስት ሐየሎም አርአያ የጦር ማሰልጠኛ በሚል እንዲጠራ እንዳደረገው ይገለጻል።
ይህ የስም ለውጥ በወቅቱ በተለይ ከጦር ትምህርት ቤቱ ከተመረቁ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ዝነኛ ማሰልጠኛ ሆኖ የዘለቀን፣ ታሪካዊ መሰረት ያለውን ይህን ተቋም በምንም መልኩ በአንድ ሰው ስም መሰየም ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም የሚሉ ትችቶች ቆይተዋል። አካዳሚው በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሚል መሰየሙን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014