የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ባለፉት አመታት በኢኮኖሚው ረገድ መሠረታዊ ስኬቶችን እንዳስመዘገበ የሚገልጽ ቢሆንም፣ አሁን ይህን ስኬቱን አደጋ ውስጥ የሚከት ተግዳሮት ገጥሞታል። ይህ ተግዳሮትም የኑሮ ውድነት ነው።
እርግጥ ነው የቡድኑ አባላት በፖሊሲ መዘወሪያው መንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች አንዳንድ መሠረታዊ መሻሻሎች በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲከሰቱ አድርገዋል።
ካስመዘገቧቸው ስኬቶች መካከል ጥቂቱን ለመግለጽ እንዲረዳ ይሄው የፖሊሲ አውጪ ኮሚቴ ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር ላይ ካወጣው መግለጫ ሁለት አንቀጾችን እንውሰድ እና እንመልከት፤- «አሁን በዕዳ ጫና ጎብጣ የነበረች አገራችን በመጠኑ ቀና ብላለች። በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሊቆም የደረሰው ኢኮኖሚያችን ሞተሩ መንቀሳቀስ ጀምሯል።
በስግብግብነት ሰፊ የአገር ሀብት እየተመዘበረባቸው በአደባባይ ምንም ሳይሠሩ ሸረሪት ያደራባቸው ፕሮጀክቶች ነፍስ ዘርተው ወደ ፍጻሜ እየደረሱ ነው። ተኮላሽተው የነበሩ እንደ ሕዳሴ ግድብ እና ስኳር ፋብሪካዎች የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን በጥብቅ ግምገማና ዲስፕሊን ግንባታቸው ተቀላጥፏል። ተንገራግጮ የቆመው ኢኮኖሚያችን እጅግ አስቸጋሪ የነበረውን ጊዜ አልፎ፣ በዘርፉ መሪዎች ጥንቃቄና በዜጎች ትብብር ወደ ጎዳናው ማስገባት ችለናል። ከለውጡ ማግሥት ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል እነዚህ ሦስቱ ይጠቀሳሉ።
የዓለምን ኢኮኖሚ ያንኮታኮተው የኮቪድ19 ወረርሽኝ፣ በአገራችንና በቀጣናው ተከስቶ ከፍተኛ እህል ያወደመው የአንበጣ መንጋ፣ በሕግ አልገዛም ያሉ አብሪተኞች በሁሉም አቅጣጫ የከፈቱት ጦርነት። ሌሎችም ፈተናዎች ነበሩ።
ሆኖም የኮቪድ አደጋንም ሆነ ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመቋቋም በጥንቃቄና በተጠና መንገድ ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎችን ለመውሰድ ችለናል። በዚህም ምክንያት ፈተናዎችን መቋቋም ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ማነቆ የነበሩብንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት መቻላችንን የሚያረጋግጡ በርካታ ድሎች አስመዝግበናል። ለአብነት ያክልም፣ እጅግ አነስተኛ የሆነው የአገር ውስጥ ቁጠባ አድጓል። በዚህም በተደጋጋሚ ዓመታት በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲፈተን የነበረውን የኢኮኖሚ ችግር እየቀረፍን መጥተናል። ይህም ከፍተኛ ብድርን ለግሉ ዘርፍ ማቅረብ አንድንችል አድርጎናል።
የወጪ ንግድ በተከታታይ ዓመታት ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ በመውጣት ከአምና ጀምሮ ወደ ተከታታይ ዓመታት እድገት ገብቷል። ዘንድሮ የ21 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ለመጀመሪያ ጊዜ አስረኛው ወር ላይ ሳይደረስ የወጪ ንግድ ገቢ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ሊሻገር ችሏል።
ይህም ካለፈው ዓመት የ10 ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ አለው። የሥራ ዕድል ፈጠራ ከግል ሴክተር መነቃቃት ጋር እንዲሁም የቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ዕድገትን እያስመዘገበ ይገኛል።» እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ስኬቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ አሳካኋቸው የሚላቸው እና ብዙም ክርክር የማይቀርብባቸው ስኬቶች ናቸው። ይሁንና ማክሮ ኢኮኖሚው አንዳንዶቹን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገን ሲታገል በሌላ አቅጣጫ ሌላ ስብራት እየገጠመው ይመስላል። ይህ ስብራትም የዋጋ ግሽበት ይባላል። በገበያው ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት ያለማቋረጥ እያሻቀበ ነው። በተለይም በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለው የዋጋ ግሽበት የብዙዎችን ኑሮ እያናጋ ነው።
የዕቃዎች ዋጋ ከቀን ወደ ቀን ያለ አሳማኝ ምክንያት እየጨመረ ነው። በዚህም የተነሳ ሕዝብ ምሬት ውስጥ እየገባ ነው። ይህ ምሬት ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ መሠረታዊ የደህንነት ችግር እንዳይፈጥርም ያሰጋል። ስለዚህም አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው ሊታወቅ የሚገባው አንድ ነገር አሁን ለሚታየው የዋጋ ግሽበት መንስኤ የሚሆኑ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸው ነው። በተለይም የሕግ ማስከበር ዘመቻው ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና አምጥቷል።
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉት የኢኮኖሚ ጫናዎችም ችግሮችን እያባባሱ ነው። እዚህ ላይ በዓለም የተከሰተው ኮቪድ እና የዋጋ ግሽበት፤ በአገር ደረጃ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የጸጥታ መደፍረሶች እና በበርካታ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ እና የአንበጣ መንጋ ኢኮኖሚውን እንደፈተኑት እና የዋጋ ግሽበቱን እንዳናሩት ግልጽ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ አብዛኛው ሰው የሚገለገልባቸው ሸቀጦች ከውጪ የሚገቡ መሆን፣ የምርት እጥረት ሳይኖር ምርትን መደበቅ እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር እና ሌሎችም በዚህ ላይ ተደማሪ ምክንያቶች ናቸው። ሕዝብም እነዚህን ነገሮች ተገንዝቦ እየታገሰ ይገኛል።
ሆኖም የሕዝብ ትእግስት ምን ያህል ይዘልቃል የሚለውን ማሰብም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት አስቸኳይ ማስታገሻዎችን መውሰድ ይገባዋል። እርግጥ ይህ ከመንግሥት የተሰወረ የማይታወቅ ችግር ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱን በቁጥር አስደግፎ የሚነግረን ብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ነው። ስለዚህም መንግሥት ችግሩን ያውቀዋል። መፍትሄ መውሰድ እንዳለበትም መካሪ አያሻውም። እየወሰደም እንደሆነ በየጊዜው እየተናገረ ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል በየጊዜው ከውጭ የሚገቡትን እንደ ስንዴ፤ ዘይት እና ስኳር የመሳሰሉትን ለዚህ ማሳያ ማድረግ ይችላል። ነገር ግን ይህን ዓይነቱ ማስታገሻ ኢኮኖሚው የለመደው ይመስላል። የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልቻለም። ስለዚህም ሌላ ዓይነት ማስታገሻ ያስፈልጋል።
ለዚህም አዳዲስ ሀሳቦችን ማዋለድ ግድ ነው። ምሁራንን መጋበዝ እና ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ እንደሚሰማው አንዳንድ የኢኮኖሚ ምሁራን መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የኢኮኖሚ ውሳኔዎች ትክክለኝነት ላይ ልዩነት እንዳላቸው እየታየ ነው።
ለምሳሌ ያህል ሰሞኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቴሌቪዥን ጣቢያው በሠራው ዘገባ ላይ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር አጥላው አለሙ መንግሥት የብርን ከዶላር አንጻር ያለ ምንዛሬ እንዲዳከም ማድረጉ የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣም፤ ከውጭ የምናስገባው አልቀነሰም፤ ወደ ውጭ የምንልከውም አልቀነሰም፤ ስለዚህም ፖሊሲዎች መከለስ አለባቸው ባይ ናቸው። ሌሎችም ምሁራን በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እንዲሁ የተለያየ እይታ አላቸው። እርግጥ ምሁራኑ የሚሰጡት አስተያየት ከራሳቸው ሙያ አንጻር ብቻ በመሆኑ ምሉእ ነው ለማለት ያስቸግራል።
መንግሥት በበኩሉ አንድን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ሲወስን ከኢኮኖሚያዊ ገጽታው በተጨማሪ ፖለቲካዊ ማህበራዊ እና ሌሎች ገጾችንም ይመለከታል። ስለዚህም የምሁራኑ ሀሳብ ለብቻው ይሠራል ማለት ከባድ ነው። ቢሆንም ሀሳባቸውን ማድመጥ እና አማራጮችን በሙሉ ማየት ያስፈልጋል።
ከዚያም ከከርሞው ይጠቅማሉ ተብለው ከሚወሰዱ የፖሊሲ ውሳኔዎች ጎን ለጎን ወቅታዊ ችግሩን የሚያስታግሱ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። አልያም የዋጋ ግሽበቱ የሰላምንም ዋጋ ውድ ሊያደርገው ይችላል፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014