የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሩሲያ ከዩክሬን ድንበር ወታደሮቼን አንቀሳቅሻለሁ ማለቷ ሐሰት ነው አሉ።
ባለሥልጣኑ አክለውም የሩሲያ ተጨማሪ 7 ሺህ ወታደሮች በቅርብ ቀናት ድንበር ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ሩሲያ ዩክሬንን «በማንኛውም ሰዓት» ለመውረር «የሐሰት» ምክንያት ልትከፍት ትችላለች ብለዋል።
ሞስኮ በበኩሏ ወታደሮቿ የጦር ልምምዳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከዩክሬን ድንበር ለቀው መውጣታቸውን ገልጻለች።
ይሁን እንጂ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ሩሲያ ወታደሮቿን ማስወጣቷን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም ብለዋል።
እንደ ጀርመን ቻንስለር ከሆነ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ስኮልዝ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት የስልክ ውይይት ሩሲያ የተባባሰውን ውጥረት ለማርገብ ትክክለኛ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባት ተስማምተዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር እቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ብትገልጽም ከ100 ሺህ የሚበልጡ ወታደሮቿን በድንበር አካባቢ ማስፈሯ ድንገት ወረራ ልትፈፅም ትችላለች በሚል ምዕራባውያንን አስግቷል።
ረቡዕ ዕለት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ታንኮች ክሬሚያን ለቀው ሲወጡ ለማሳየት ተንቀሳቃሽ ምሥል አውጥቷል።
ይሁን እንጂ እንደ ዋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆነ ረቡዕ ዕለት የደረሱትን ጨምሮ በቅርብ ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የሩሲያ ወታደሮች ድንበር ላይ ደርሰዋል።
ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ «ይህ ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ጋር ከምትዋሰንበት ድንበር እያስወጣሁ ነው ማለቷን ጥርጣሬ ውስጥ ከትቷል» ብለዋል።
«ሩሲያ ወታደሮቼን አስወጥቻለሁ ማለቷ ከዚህ እና ከመላው ዓለም ከፍተኛ ትኩረት እንድታገኝ አድርጓታል፤ ነገር ግን አሁን ይህ ሐሰት መሆኑን አውቀናል» ብለዋል ከፍተኛ ባለሥልጣኑ።
ባለሥልጣኑ ይህንን ያሉት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ «እስካሁን ወታደሮች ወጡ ሲባል ነው የሰማነው እንጂ፤ ሲወጡ አላየንም» ሲሉ ለቢቢሲ ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ይህ የተናገሩት ረቡዕ ዕለት ዩክሬን «የአንድነት ቀን» በሚል በዓል ስታከብር ነው። በዕለቱ በመላ አገሪቷ ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም ያላቸው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለዋል።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ዕለቱን «የአርበኝነት በዓል» ሲሉ ያወጁት የአሜሪካ ደህንነት ቢሮ በዚያን ዕለት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ልትፈፅም ትችላለች በሚል ላወጣው ሪፖርት ምላሽ ነው።
ረቡዕ ዕለት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ የሩሲያ ጦር ውጥረቱን ማርገቡን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደሌሉ ገልጸው፤ ከሩሲያ የሚሰነዘረው ማስፈራሪያ «እየተለመደ መጥቷል» ሲሉ ተናግረዋል።
በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው የኔቶ መከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ስቶልተንበርግ፣ ድርጅቱ አዳዲስ የውጊያ ቡድኖችን ማለትም ብቃት ያላቸውና ራሳቸውን የሚችሉ ትናንሽ ወታደራዊ ቡድኖች በመካከለኛው እና በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ለማቋቋም እያሰበ ነው ብለዋል።
ኔቶ ለሩሲያ ስጋት አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሞከሩት ሚኒስትሩ፤ ይህ ሃሳብ እአአ ከ2014 ጀምሮ 270 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የአውሮፓ መከላከያን ለማጠናከር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አካል መሆኑን አስረድተዋል።
ፈረንሳይ በሮማኒያ ውስጥ አንድ የጦር ቡድን ለመምራት ሃሳብ አቅርባ እንደነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሚኒስትር ስቶልተንበርግ በሰጡት መግለጫ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014