ሁሌ ጠዋትና ማታ በታሰርኩባት ጠባብ ክፍል መስኮት አጠገብ ቆሜ አባቴንና ሙሴን አስታውሳለሁ። አባቴ መምህር እንድሆንለት ነበር ፍላጎቱ፤ ለመምህርነት ልዩ ፍቅር ነበረው። ሁሌ በገባሁ በወጣሁ ቁጥር አንተ መምህር ነህ፤ ስትራመድ ይሄን እያሰብክ ተራመድ ይለኝም ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ረስቼው እጄን ሳልታጠብ ምግብ ከበላሁ፣ ጠዋት እንቅልፍ ጥሎኝ ትምህርት ቤት ከረፈደብኝ፣ ‹መምህር እንዲህ አይደለም፤ ለራሱ ሞልቶ ለሌሎች የተረፈ ነው፤ ራስህን የትም ቦታ ጎድሎ ሆነህ እንዳታገኘው›› ይለኛል። አባቴ እንዲህ ባለኝ በማግስቱ፤ ኅብረተሰብ አስተማሪያችን ክፍል ይገባና ዶክተር መሆን የምትፈልጉ እስኪ እጃችሁን አውጡ ሲል ከእኔ በቀር ሁሉም ተማሪ ያወጣል። ፓይለት መሆን የሚፈልግ ሁሉም ያወጣሉ። ኢንጅነር መሆን የሚፈልግ ብዙ እጆች ይወጣሉ። መምህር መሆን የምትፈልጉ ሲል ሁሉም ጸጥ ይላሉ። አባቴ ተደብቆ የሚያየኝ እየመሰለኝ ከዚያ ሁሉ ተማሪ መካከል እኔ ብቻ አወጣለሁ፡፡
ክፍላችን ውስጥ ያሉት ሁሉም ተማሪዎች ከመምህር ውጪ ሁሉንም መሆን የሚፈልጉ ናቸው። ታዲያ አባቴ ለምንድነው እኔን መምህር እንድሆን የሚያስተምረኝ ስል ራሴን እጠይቃለሁ። እቤት እንደ ደረስኩ ባኮረፈ ፊት አባቴን ‹‹ እኔ መምህር መሆን አልፈልግም› እለዋለሁ፡፡
ረጅም ዝምታ ይውጠዋል፤ የዝምታው ርዝመት ይገርመኛል። ሁሌም እንዲህ ዝም የሚለው መምህር መሆን አልፈልግም ያልኩት ቀን ነው። ከረጅም ዝምታ በኋላ ‹ለምንድነው መምህር መሆን የማትፈልገው? ይለኛል። ‹ክፍል ውስጥ እኮ ከእኔ በቀር መምህር መሆን የሚፈልግ አንድም ተማሪ የለም› እለዋለሁ፡፡
ዛሬም ድረስ የማትረሳኝን ምስጢራዊ ሳቁን እየሳቀ ‹ይሄውልህ ልጄ! ሰዎች እስከቻሉት ድረስ ብቻ ነው የሚያስቡት፤ እነሱ ከአንተና ከእኔ የተሻለ እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ መምህር መሆንን ያስቀድሙ ነበር፤ እነሱ የሰሙትን ነው የሚኖሩት፤ አንተ ግን ያየኸውን ነው የምትኖረው› ብሎ ያሳምነኛል። ኩርፊያዬን ትቼ አብሬው ምሳ እበላለሁ፡፡
አባቴ በእኔ ላይ ያለው እምነት ይገርመኛል። በእኔ ላይ ያለው ተስፋ፣ በእኔ ላይ ያለው ጽናት ያስደንቀኛል። በሕይወቴ ሁሌም የሚቆጨኝ የአባቴን እምነት ባለመኖሬ ነው። አባቴን መቼም አልክሰውም፤ ድጋሚ መፈጠርን የምሻው፣ ድጋሚ ልጅ መሆንን የምመኘው ላባቴ ልጅ ሆኜ እሱን ለማገልገል ነው።
ሙሴ የልጅነት ጓደኛዬ ነው፤ በሕይወቴ የሚቆጨኝ ነገር በሙሴ ልጅነት ውስጥ እኔ መገኘቴ ነው። ሙሴ በልጅነቱ ሁሉንም ዓይነት ሰው ነበር። የአባቴን እውነት የካድኩት፣ ጽናቱን የሻርኩት በሙሴ ጓደኝነት ውስጥ ነበር። ቤታችን ከቤታቸው ፊት ለፊት ነው፤ ስወጣ መጀመሪያ የማገኘው ሙሴን ነው፤ በራቸው አጠገብ ካለችው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ። በሙሴ ጓደኝነት የአባቴን አባትነት ረሳሁት።
በሙሴ ሰይጣናዊነት የአባቴን መልካምነት እያጣሁት መጣሁ። አሁን ላይ ሙሴን ሳስበው ሳጥናኤል ሰው ሆኖ ይመስለኛል። በልጅነቱ ውስጥ ያልነበረ ክፋት አልነበረም። ሰፈራችን እማማ አስካለ የሚባሉ አሮጊት አሉ፤ ግቢያቸው ውስጥ ብዙ ማንጎና ዘይቱን አለ። እዚያ እየወሰደ ነው ሌብነትን ያስተማረኝ። መጀመሪያ ቀን እንስረቅ ሲለኝ ‹እኔ መምህር ነኝ አልሰርቅም አለው ነበር። በአባቴ የተስፋ ጽላት ሩቅ የተጓዝኩ ቢሆንም በሙሴ ተንኮል ግን ከመተብተብ አልዳንኩም፡፡
ሙሴ ቃየልን ይመስለኛል፤ የአቤል ነፍሰ ገዳይ። ልጅነቴ ያደፈው በልጅነቱ ነው። ብዙ ጊዜ ወንዝ እንውረድ ብሎኝ ያውቃል። አንድ ቀን ይዞኝ ሄደ፤ ከመሬት ሁለት እኩያ ድንጋዮችን አነሳና ሰውነቱን በመታጠብ ላይ ወዳለ ሽማግሌ ወርውሮ ፈነከተው፤ በሌላ ቀን ደግሞ ገላቸውን የሚታጠቡ ሴቶችን ልብስ ይዞባቸው ሄደ። በሙሴ ክፋት የአባቴን እውነት እያጣሁት መጣሁ። እየቆየሁ ስሄድ ራሴን በራሴ ውስጥ አጣሁት፤ ሙሴን ሆንኩ። ሙሴን በሆንኩ በማግስቱ ወደ አባቴ ሄድኩና ‹እኔ መምህር መሆን አልፈልግም› አልኩት፡፡
ከረጅም ዝምታ በኋላ ‹ለምንድነው የማትሆነው? ሲል ጠየቀኝ፡፡
‹መሆን ስለማልፈልግ…› መለስኩለት። ያን ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአባቴ መልስ የሰጠሁበት ጊዜ ሆነ። አባቴ ወደ ጉያው አስጠጋኝና «ለማይጠቅምህ ነገር መልፋት የለብህም፣ የኔ ልጅ እስከሆንክ ድረስ ምርጥ ነገር የት እንደተቀመጠ ማወቅ አለብህ፡፡››ሲል መከረኝ።
መምህርነት እየሱስነት ነው። ይቺ ዓለም የተቃናችው በመምህራን ነው። መምህር ሁን ያልኩት በምክንያት ነው። የትምህርት ቤት ጓደኞችህ እንደ እኔ ዓይነት ብልህ አባት ስለሌላቸው ነው ለማይጠቅማቸው የሚተጉት። የሚፈልጉት ስልጣንና ክብር ከመምህር አብራክ ውስጥ እንደሚገኝ ቢረዱ ኖሮ ከዶክተርና ከፓይለት በፊት መምህር መሆንን ያስቀድሙ ነበር አለኝ፡፡
‹‹የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ አትሁን›› አለኝ። የተናገረው ነገር ለልጅነት ጭንቅላቴ የሚመጥን ስላልነበር ብዙም አልተረዳሁትም። ከሙሴ በሰማኋት ዘመነኛ ቃል ‹አልሰማህም› ስል እጆቼን በማወናጨፍ አባቴን ተሰናበትኩት። ለመጀመሪያ ጊዜ በአባቴ ላይ ክፉ ሆንኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በአባቴ ፊት የልጅነት ሞገስ አጣሁ። እግሮቼ እንዲጸኑና ዳር እንድደርስ የወርቅ ምንጣፍና የሜላት ግምጃ ለሆነኝ አባቴ ያን ቀን አልሰማህም ስል ተበትኩበት፡፡
ከሰዎች ሁሉ እንድልቅ እርካብ ሆኖ ባቆመኝ አባቴ ላይ ተዘባበትኩበት። ያን ቀን ስለ እኔ ሊሟገት፣ ስለእኔ ሊከራከር ስማኝ ልጄ እያለ ሲጠራኝ ረግጬው ሄድኩ። አባቴ እያናገረኝ ወደ ሙሴ ሄድኩ። በቆመበት ትቼው ስሄድ ያየኋቸው ያባቴ አይኖች ዛሬም ድረስ ይፋረዱኛል።
ሙሴን መከተል ጀመርኩ፤ ከአባቴ በላይ እውነት ሆኖ አገኘሁት። ከሙሴ ጋር ወዳጅነትን ከጀመርን አንስቶ ትምህርቴ ላይ ግዴለሽ ሆንኩኝ። ከምገባበት ይልቅ የማልገባበት ጊዜ በረከተ። ግቢ ውስጥ ሴት ተማሪዎችን ማስቸገር፣ ከመምህራን ጋር መጣላት፣ ከተማሪዎች ጋር መደባደብ ሥራዬ ሆነ። ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ በሙሴ ተንኮል የተዋጣለት ወመኔ ሆንኩኝ። እንዲህ ሆኜ አደኩ፤ በሙሴ ተንኮል አሁን ወህኒ ቤት ነው ያለሁት፡፡
በሕይወቴ ሁለት ነገሮች ያስቆጩኛል፤ የሙሴ ጓደኛ መሆኔና በአባቴ እውነት አለመጽናቴ። መጥፎ ጓደኛ መልካሙን አመል ያበላሻል፤ በጓደኛዬ እኔም ተበላሸሁ፡፡
ያኔ አባቴ ዝም ብሎ ከሚወደኝ ጓደኞቼ እነማን እንደሆኑ፣ ከነማን ጋር እንደምውል ቢያውቅ ዛሬ እንዲህ አልሆንም ነበር እላለሁ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014