በኢትዮጵያ ስፖርት አንጋፋና ስመጥር ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስና ጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርቶች በርካታ ስፖርተኞችን አቅፎ በማሰልጠን ለውድድር ያበቃል፡፡ በተለያየ ጊዜም ክለቡን ወክለው በሚሳተፉ ቡድኖቹ እና ስፖርተኞቹ በሀገር አቀፍ ውድድሮች አሸናፊ በመሆን ውጤታማነቱን አስመስክሯል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ተካተው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተካፍለው ውጤታማ የሆኑ ስመጥር ስፖርተኞቹ ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ንግድ ባንክ በ2013 ዓ.ም ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞቹንና የስፖርት ባለሙያዎቹን ለማበረታታት ከትናንት በስቲያ የእውቅና እና ምስጋና መድረክ አካሂዷል፡፡ ባንኩ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነውን ህንጻ ሰሞኑን ማስመረቁን ምክንያት አድርጎ በተካሄደው የዕውቅና መርሃ ግብር 1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ለስፖርተኞቹ ሸልሟል፡፡
በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ቻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው እንዲሁም በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ባለቤት ለሆነው ቡድን ደግሞ ልዩ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ በአትሌቲክስ፣ የሴቶች እግር ኳስ እና ጠረጴዛ ቴኒስ በውድድር ዓመቱ የተገኙ ዋንጫዎችንም ስፖርተኞቹ ለባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስረክበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ አህመድ፤ ባንኩ ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ በስፖርት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞች ከማፍራት ባለፈ ጊዜያዊ የመለማመጃና የውድድር ሜዳ እድሳት መጠናቀቁን የጠቆሙ ሲሆን፤ የስፖርተኞች መኖሪያና የአሸዋ ትራክ ግንባታም አመቱ የተሳካበት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ለብሄራዊ ቡድን የሚሆኑ በርካታ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኝ እና የህክምና ባለሙያም ክለቡ ማስመረጥ መቻሉን አቶ አሊ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ቡድኖች የተመዘገበውን ውጤት አርዓያ በማድረግ ባንኩ እንደ አዲስ ያቋቋመው የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግብ አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት እና የስፖርት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ አቤ ሳኖ፤ የሴቶች እግር ኳስ ቡድኑን ጨምሮ በሌሎች ስፖርቶችም የሴት ቡድኖች በርካታ ዋንጫዎችን በማምጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በስፖርት ስኬታማ የሚሆኑት ስሜቱ ያላቸው በመሆኑ ገንዘብን መሰረት አድርጎ መግባት አግባብ አይደለም፡፡ ለስፖርቱ ፍላጎት ያለው ደግሞ ሁሌም አሸናፊ ለመሆን ጥረት ያደርጋል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ ለስፖርተኞቹ እድል መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ስፖርተኞቹ አሸናፊ ሲሆኑም እንደሚሸለሙ አክለዋል፡፡ ይህም የማደግ እድል እንዲሁም በሌሎች ተፈላጊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ባንኩም ስፖርተኞቹን ለማቆየት ከሌሎች ጋር ውድድር ይጀምራል ሲሉ የምስጋና መርሃ ግብሩን አስፈላጊነት ጠቁመዋል፡፡
በአንጻሩ እንደ አዲስ የተዋቀረውን ዋናውን ቡድን፣ በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ለሚገኙ የወንዶች እግር ኳስ ቡድኖች እንዲሁም ውጤት የማያስመዘግቡ የክለቡ አባላትን እንደማይታገስ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተሸነፉ እስከ ማሰናበት የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችልም አስገንዝበዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሌላው ዜጋ እድል እንዲያገኝ ሲባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወዳደረበት መስክ ተሸንፎ አያውቅም፤ ከአትሌቲክስ በቀር በስፖርተኞቹ ግን ይወቀሳል›› ብለዋል፡፡
በሴቶች እግር ኳስ የተሻለ ነገር ቢኖርም በኬንያ በተካሄደው የሴካፋ ውድድር ለማሸነፍ አቅደው ባለመሳተፋቸው ሊሸነፉ መቻላቸውን ጠቅሰው፤ በየትኛውም ውድድር አሸናፊ ለመሆን አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ እና ህልም እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
በማሳያነትም በቅርቡ የተመረቀውን የባንኩን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ገና ሲታቀድ ብዙዎች እውን እንደማይሆን ይገልጹ እንደነበር
አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም የተሻለ ነገር አቅዳችሁ ከሰራችሁ ባንካችን ከእናንተ ጋር ነው ስታሸንፉ ይሸልማችኋል፤ በመሆኑም ውጤትን መሰረት በማድረግ ዕድላችሁን ተጠቀሙበት፡፡ ባንኩ ስፖርትን የያዘው ለትርፍ ሳይሆን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመሆኑ ከክለቡ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ማፍራት እንፈልጋለን›› ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በስፖርተኞቹ የተገኙ ዋንጫዎችንም ተረክበዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም