ያ ዘመን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ያበበበት እጅግ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ጎልተው የወጡበት ዘመን ነበር፤ 1950ዎቹ መጨረሻና 1960 መጀመሪያ አካባቢ።አድፍርስም በዚህ መሀል ብቅ ብሎ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነ አንዳንዶች አወዛጋቢ ሲሉት ብዙዎች ደግሞ የተደመሙበት የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ድንቅ ሥራ ነው፡፡
ይህ «አደፍርስ» የተሰኘ መጽሐፍ በይዘትና በአተራረክ ሂደቱ ከዚያ በፊት ከነበሩት ወጣ ያለ መሆኑ ነበር ለመነጋገሪያነት ያበቃው፡፡ መጽሐፉ ዛሬም ድረስ የሥነ ጽሑፍ ሀያሲያን ደጋግመው በምሳሌነት ይጠቅሱታል፡፡ በቋንቋ አገላለፁና ለየት ባለ የአተራረክ ስልቱ ከተለመደው የአፃፃፍ ዘይቤ ወጣ ማለቱን አንስተው ማስተማሪያ ያደርጉታል፡፡
አንዳንድ ብዕረኛ ወደፊት የሚሆነውን በእዝነ ህሊናችን አሻግሮ፤ ያለፈውን ደግሞ አቅርቦ የማሳየት ልዩ ክህሎት ይላበሳል፡፡ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ደግሞ በአደፍርስ ከወቅቱ ዘለግ ያለ ምልከታ፣ ከጊዜው የቀደመ እሳቤን ይዞ በዚያ እርሱ በተፈጠረበት ወቅት ያለን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወትን ነጠቅ ባለ መልኩ እያሳየ የገፀ ባህሪያቱ ልዩ ልዩ ሁነቶችን በተብራራ መልኩ አሳይቷል፡፡
በእርግጥም ሲያነቡት የእርሱን ያህል ድፍርስርስ ያለ እሳቤ ግራ የሚያጋባ አገላለፅና የታሪክ ኡደት ሆኖባቸው በትዕግስት ማጣት የመጽሐፉን ኃያልነት ዘንግተው ጀምረው ያልጨረሱትም ሞልተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አልፎትም ከፍ ያለ የሥነ ጽሑፍ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ድንቅ መጽሐፍ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
ደራሲው ድርሰቱን በእርሱ የመገንዘብ ልዩ አቅም በተለየ ሥነ ጽሑፋዊ ገፅታ አንድ መጽሐፍ ጽፎ ለገበያ አቀረበ፡፡ ታዲያ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ መጽሐፉን በተመለከተ ከሌላው ልዩ አተያይ ነበረው፡፡ ይህም በተለያየ መልክ ገልፆታል፡፡
መጽሐፉ መጀመሪያ ገበያ ላይ በ5 ብር እንዲሸጥ ተመን ወጥቶለት ተከፋፈለ፡፡ አንድ ቀን የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፤ የራሱን መጽሐፍ ለያዘ ወጣትና የመጽሐፍ አከፋፋይ መንገድ ሲዘዋወር አግኝቶት «እንዴት ነው ይህ መጽሐፍ እየተሸጠ ነው?»ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
የመጽሐፍ ሻጩ ግን ያገኘው ምላሽ የጠበቀው አልነበረም፡፡ «ሰው ዋጋው ተወደደብኝ እያለ እያነበበው አይደለም፡፡» አለው፡፡ ይሄኔ የእርሱ ታላቅ እሳቤ በአንባቢ ዘንድ ዋጋ ማጣቱ የቆጨው ሀሳቡ ለሌሎች ግልፅ አለመሆኑ ያስኮረፈው ዳኛቸው እንዲህ አለ «ከዛሬ ጀምሮ የመጽሐፉ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ በአስር ብር እንጂ እንዳትሸጡት፤ ዋጋው ጨምሯል፡፡» ብሎት ወደቤቱ ተመልሷል፡፡
እርግጥም ዘግይቶ የመጽሐፉን ታላቅነት የተረዱት ቢበዙም ጅምር ላይ ግን የመጽሐፉ ተፈላጊነት መቀነስ ደራሲው መሰል ሥራዎች ሠርቶ ለሕዝብ እንዳያቀርብ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮበታል፡፡ ከደራሲው ሥነ ጽሑፋዊ ብስለት አንፃር ብዙ ቱርፋቶቹን ናፈቅን እንጂ በእርግጥ ከአደፍርስ ሌላ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የፃፋቸው መጽሐፍትም አሉት፡፡
ደራሲውን በቅርብ ያውቁት የነበሩት ደራሲና ተርጓሚ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ዳኛቸው በባህሪውም በሥራውም ልዩ ሰው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ከድርሰቶቹ መካከል «አደፍርስ» የተሰኘው ልቦለድ ለየት ያለና የደራሲው ልዩ ክህሎት የተንፀባረቀበት የጎላ ሥነ ጽሑፋዊ አቅም የተንፀባረቀበት ድርሰት መሆኑን ያነሳሉ፡፡
አደፍርስ ወትሮ ከተለመደው ትረካዊ የአቀራረብ ስልት ወጣ ብሎ በራሱ መንገድ ድራማዊ በሆነ መልክ ታሪክ በመንገር የቀረበ ድርሰት ነው፡፡ ብዙዎች የአፃፃፉን አንድነት በመመልከት «ይህ መጽሐፍ ወጣ ያለና የማይገባ ነው» ይበሉት እንጂ ለሥነ ጽሑፉ የቀረቡ የዘርፉ ቤተሰቦች እንደ ዳዊት ደጋግመው እያነበቡ አዳዲስ ምስጢራት ከውስጡ ያገኙበታል፡፡
ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላው ሲሸጋገር አዳዲስ ሁነቶችና ገፀ ባህሪያት ይዞ በመቅረብ ወደ ሌላ ሳይወስዳቸው መቋጨቱ የድርሰቱን ግራ አጋቢነት የሚጠቅሱ ሰዎች የሚያነሱት ሂሳዊ አስተያየት ነው፡፡
በገፀ ባህሪያት አሳሳል በሚያደርጉት የሀሳብ ልውውጥ (ንግግር) ውስጥ አንዳች ምስል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ድንቅ ልቦለዳዊ ፈጠራ በጉልህ ይታያል፡፡ በመጽሐፉ ላይ አንድ አካባቢና በተለየ መልኩ የገለፀበትን ስለ መልካምድሩ ምስል ከሳች በሆነ መልኩ ያነሳበት ቕንጭብ ጽሑፉን እንመልከት፡፡
«ቁንዲ አንገቷን አስግጋ ቃፊርነት የቆመች መስላለች። የዓዋዲና የጀውሃ ጅረቶች ደረታቸውን ለፀሐይ ሰጥተው ይምቦገቦጋሉ። ሰማይና ምድር የተገናኘበት፣ ሕይወት ያሸለበችበት የሚመስለውን በስተግርጌ የሚታይ ሜዳ አቧራ ረግቶበታል … የይፋትና ጥሙጋ አውራጃን ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ዓለምን ሠርቶ ሲያበቃ የተረፈውን ትርክምክም ያጐረበት ዕቃ ቤቱ ይመስላል – ሸለቆው፣ ጉባው፣ ተራራው፣ ገመገሙ፣ ጭጋጉ፣ አቧራው ሕይወትን አፍኗት ተኝታለች – ያቺ በሌላው አገር የምትጣደፈው፣ የምትፍለቀለቀው፣ የምትምቦለቦለው ሕይወት እዚህ እፎይ ብላለች – በርጋታ፣ በዝግታ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ …» ይህንን መሰል ገለፃ፣ የበቃ የቋንቋ አጠቃቀምና የተዋዛ ምስል ከሳች ጽሑፍ አደፍርስን ስናገላብጥ ደጋግመን እናገኛለን፡፡
በዚሁ ወር ደራሲውን ያሰበ ስለ ሥራዎቹም ተነስቶ የተዘከረበት ታላቅ ድግስ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተካሂዶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ደራሲና ገጣሚ «ዳኛቸው ወርቁ ማን ነው?» በተሰኘ ርዕስ የውይይትና የመታሰቢያ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙ እውቅ ደራሲያንና የሥነ ጽሑፍ ቤተሰቦች ደራሲውንና ሥራውን እያወሱና እየዘከሩት አምሽተዋል፡፡ መድረኩ ላይ ደራሲው በሕይወት ዘመኑ የሠራቸው ድንቅ ሥራዎቹን እና ስብዕናውን በተመለከተ የሚያውቁት ስለሱ የሰሙትና ያነበቡትን እያነሱ ገልጸውታል፡፡
በዕለቱ ከተገኙት ደራሲያን መካከል ደራሲ እንዳለ-ጌታ ከበደ (ዶክተር) ባቀረቡት የዳሰሳ ጽሑፍ የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ላቀ ደረጃ ያሳደጉና የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፉ መድረክ ካስተዋወቁ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሲያን አንዱ መሆኑን አብራርቷል።
ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ «አደፍርስ» የተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ ጠጣርና ምጡቅ ሐሳቦችን በተከሸነ ውብ የአጻጻፍ ስልት፤ ከተለመደው የቋንቋ አጠቃቀም ስልት ለየት ባለ መልኩ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዕልና ያሳየ መሆኑንም የሚያነሳው ደራሲ እንዳለ ጌታ፣ የደራሲውን ልዩ ክህሎት ከሥራዎቹ ጋር በማስረጃነት ጠቅሷል፡፡
በመድረኩ ላይ በመገኘት ስለ ደራሲው ሥራዎች አስተያየት ከሰጡት እና ድርሰቶቹን በተመለከተ ንግግር ካደረጉት መካከል ገዛኸኝ ጸጋው (ዶክተር) ይገኙበታል፡፡ ገጣሚ ዳኛቸው «እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለአገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲና ተርጓሚ ነበረ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ደራሲው ማን ነው?
ዳኛቸውን በቅርብ ያውቁት የነበሩት ደራሲና ተርጓሚ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ዳኛቸው የአገሩን ባህልና እሴቶች ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለጊዜ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ፣ ሥራን ለነገ ማሳደርን የማያውቅ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ አገር ወዳድ፣ ስለአገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው መሆኑን መስከረውለታል።
ዳኛቸው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል በረዳት መምህርነት እና በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን፣ በወቅቱ በተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጅ ገጣሚዎች ከነኢብሳ ጉተማ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ መስፍን ሀብተማርያም ወዘተ ጋር በመሆን በአዘጋጁት የግጥም መድብል «ወጣቱ ፈላስማ» በሚለውና በመሳሰሉት ግጥሞቹ የለውጥ ሐሳቡን ሲያስተጋባ የነበረ ገጣሚ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
የዳኛቸው ወርቁ ሌላው አብይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት በአፍሪካን ሲሪስ ውስጥ የታተመውና “ The Thirteenth Sun” የተሰኘውን መጽሐፍ አስታውሰው ተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ ልብወለድ ድርሰት እንደነበረውና ለኅትመት ከላከው በኋላ እንዳይታተም እንዲቋረጥ ማድረጉን በማውሳት ትዝታቸውን አጋርተዋል። «እምቢ በሉ ሰዎች» እና «የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ» የዚህ ድንቅ ደራሲ ቱርፋቶችና ለሥነ ጽሑፍ ያበረከታቸው የማይተኩ ስጦታዎቹም ነበሩ፡፡
በመጽሐፎቹ ውስጥ የምናገኘው የደራሲው የቋንቋ ብቃት አንብበን የምንደመምበት ነው፡፡ ከአደፍርስ ፈፅሞ የማይረሳ የገፀ ባህሪያት ንግግር መካከል የወይዘሮ አሰጋሽ እና የአሽከሩ ለብድር መጥቶ የሚነጋገሩት አልያም የሚያደርጉት የሀሳብ ልውውጥ አጠገባቸው ቆመን የምንሰማው ያህል ምሰል የሚፈጥርብን፣ የተወዳጀናቸው ያህል ስሜታችን የሚቆጣጠሩብን፣ ዳኛ የሆንን ያህል አንዱ ላይ እንድንፈርድ የሚያደርገን ሁኔታ ስንመለከት የደራሲው ልዩ ክህሎት በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ተገልጧል ያሰኛናል፡፡
አደፍርስ ውስጥ በተለየ መልኩ የተሳሉት አሽክሩ ወይም ጢሰኛው እመቤት ከሆነች ሴት ጋር የሚያደርገው ንግግር ሁሌም ስለ አደፍርስ በተወራ ቁጥር የሚታሰብ ነው፡፡ ወ/ሮ አሰጋሽ የተባሉ የገጠር እመቤት ከጢሰኛቸው ጋር ቲያትር መሰል የንግግር ልውውጥ ሲያደርጉ ያሳየናል። ጢሰኛው የዘንጋዳ ዘር አጥቶ ሊበደር ወደ እመቤቱ ዘንድ መጥቶ ይጠይቃል። ወ/ሮ አሰጋሽ በተባ አንደበት የጢሰኛቸውን ሞራል አንኮታኩተው ከሰበሩት በኋላ ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ ሰጥተውት በመኸር ወራት አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይነግሩታል።
እዚህ ውስጥ ማህበራዊ መስተጋብርን የሰዎች መብት ማንነትና ባህል የበላይነትና የበታችነት በማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ተፅዕኖ በጎላ መልኩ ያሳያል፡፡ የራሱን እሳቤና መስተካከል የሚገባቸው ማህበራዊ ህፀፆች መታረም የሚገባቸው ተገቢ ያልሆኑ ህፀፆች ያሳያል፡፡ እያነሳ ያስተምራል፡፡ ጉዳትና ጥቅማቸውን በሚገባ በተገቢው መልኩ ያመለክታል፡፡
በደራሲው ሥራዎች ውስጥ እጅጉን ጎልተው የሚታዩት የዳበሩና እጅጉን ገላጭ የሆኑ ቃላት ሲሆኑ እነዚህም ደራሲው የነበረው የላቀ የቋንቋ ክህሎት የሚያስረዱ ናቸው፡፡ በተለይም አደፍርስ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ስለ አደፍርስ ሲነሳ አብዝቶ የሚነገረው በመጽሐፉ ውስጥ የተገለፁት ልዩ ልዩ ሁነቶች ግራ ያጋባሉ፤ ለመረዳትም ያስቸግራሉ ብለው የሚሞግቱ አንባቢያን አንባቢው እያንዳንዱን የደራሲውን ምናባዊ ፈጠራ ተከትሎ በራሱ ማመስጠር አልያም መረዳት አለበት የሚሉቱን ይቃረናሉ፡፡ የአንድ ደራሲ ታላቅ ችሎታ ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ የቋንቋ አጠቃቀም ብቃቱና የራሱ የሆነ የአተራረክ ስልት ተጠቅሞ ተደራሲያኑ ዘንድ ማድረስ የሚፈልገውን መልዕክት በቀላሉ ማድረስ መቻሉ ነው፡፡ የሚሉት ደግሞ አደፍርስን በራሳቸው መነፅር ተመልክተው የዚህን ብያኔ ሰጥተዋል፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም