አሜሪካ በዩክሬን መዲና ኬቭ የሚገኘው ኤምባሲዋን ወደ ሌላ ከተማ ማዛወሯን አስታውቃለች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር /ኔቶ/ እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ እና ሩሲያ ጉዳዩን እንደማትቀበል በማሳወቋ በምስራቅ አውሮፓ ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተደቅኗል።
የሩሲያን ውሳኔ ተከትሎም የኔቶ አባል አገራት እንደ ተቋም እና እንደ አገር ከፍተኛ መጠን ያለው ጦር ወደ አካባቢው በማስፈር ላይ ሲሆኑ ሩሲያም ከ150 ሺህ በላይ ጦር ወደ ዩክሬን አስጠግታለች።
በዚህ ምክንያትም በአካባቢው ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የተለያዩ አገራት ጉዳዩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን አሜሪካ በዩክሬን መዲና ኬቭ የነበረውን ኤምባሲ ወደ ምዕራብ የአገሪቱ ከተማ ወደሆነችው ሊቪቭ ቀይራለች።
አሜሪካ ኤምባሲዋን ከኬቭ ለመቀየር የወሰነችው ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች በሚል ስጋት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ዜጎቿ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ በማስጠንቀቅ ላይ ስትሆን ዛሬ ወይም ነገ ሩሲያ ዩክሬንን ትወራለች ብላለች።
ሩሲያ በዩክሬን እና ቤላሩስ ድንበር ከ100 ሺህ በላይ ጦሯን ማስጠጋቷን ተከትሎ በማንኛውም ሰዓት ወረራውን ልትፈጽም ትችላለችም ብላለች።
አዲሷ የአሜሪካ ኤምባሲ በዩክሬን የተከፈተባት ከተማ ሊቪቭ ከኬቭ በ80 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ሲሆን፤ ለፖላንድ ቅርብ ከተማ እንደሆነች ተገልጿል።
በዩክሬን የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች አስቀድመው አገሪቱን ለቀው የወጡ ሲሆን ይህንን ማድረጓ አሜሪካውያንን ከዩክሬን ጋር እንደማያቀያይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ሰጥተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014