126ኛው የአድዋ ድል ቀን ተቃርቧል፤ በአሉ በተለይም በአዲስ አበባ እንደ ቀደሙት አመታት ሁሉ በድምቅት እንደሚከበር ይጠበቃል። ለበአሉ ተብለው የሚዘጋጁ አልባሳት ብዛት እና አይነትም እየጨመረ ነው። ይህ የሚበረታታ ተግባር ነው።
ይህን ታላቅ በአል ከኢትዮጵያ በአልነት ከፍ አድርጎ የአፍሪካ ብሎም የመላው ጥቁር ህዝብ በአል አድርጎ ማክበር ያስፈልጋል። በበአሉ ሰሞን አንቅስቃሴዎች በሙሉ ይህን የሚያመለክቱ ሆነው መቃኘት አለባቸው። በተለይም አለባበሳችን አንድም የአድዋ ድልን የሚዘክሩ በሌላ መልኩ ደግሞ ህብረ ብሄራዊነትን እና ፓን አፍሪካኒዝምን የሚሰብኩ ቢሆኑ መልካም ይሆናል። ለዚህም ዲዛይነሮቻችን በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ በጥቁሮች ዘንድ በወርሀ የካቲት (ፌብሩዋሪ) የሚከበረውን የጥቁር ታሪክ ወር በአል እና ለዚያም ተብለው የሚዘጋጁ አልባሳትን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እያዩ መስራት ይኖርባቸዋል።
የተለያዩ ድረገጾችን ስናይ እንዳረጋገጥነው በዚህ የጥቁር ታሪክ ወር ላይ የሚለበሱ አብዛኛዎቹ አልባሳት የጥቁር አሜሪካውያንን አፍሪካዊ ዳራ በመዘከር ላይ እንደሚያተኩሩ ነው። አብዛኞቹ በዚህ ወር የሚለበሱ አልባሳት በተለምዶ የአፍሪካ ልብስ የሚባሉት አይነት በቀለም ያሸበረቁ አልባሳት ናቸው። አልባሳቱ ጥቁሮች የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ እንደሚመዘዝ የሚገልጹበት ሁነኛ መንገድ መሆኑ ይገለጻል።
በሌላ መልኩ በዚህ የጥቁር ታሪክ ወር የሚለበሱ አልባሳት በአንድ ጎን ጥቁሮች በባርነት በነበሩበት ወቅት የለበሷቸውን አልባሳት የሚያስታውሱ ሲሆን፣ ለነጻነት ባደረጉት ትግል ወቅት የመሯቸውን እና ብዙ ጀብድ የፈጸሙትን ጀግኖቻቸውን የሚያስታውሱበት ነውም ይባላል። አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ስኬታማ የሆኑ ጥቁሮችም በዚህ ወር አለባበስ ውስጥ በብዛት ይዘከራሉ።
እነዚህ አልባሳት በዚህ የጥቁር ታሪክ ወር ላይ በፋሽን ትርኢቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ በየአመቱ በዚህ ወር ላይ የሚለበሱ አዳዲስ ዲዛይኖችም ይተዋወቃሉ። ከዚህ በመነሳት እኛም በዚህ የአድዋ ወር ላይ ምን አይነት አለባበስን እንከተል ብለን ያሰላሰልናቸውን የተወሰኑ ሀሳቦችን ለማመልከት ወደድን። አንደኛ ታሪኩን በሙሉ በአለባበሳችን እናንሳ ፤ የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድል ነው። በአድዋ ጦርነት ላይ ያልተሳተፈ ብሄር እና ሀይማኖት አለ ለማለት ያስቸግራል።
በበአሉ ላይ የሚታዩ የአለባበስ ፋሽኖች የአድዋ ድልን ሙሉ ታሪክ የሚገልጹ መሆን ይኖርባቸዋል። በአለባበሳችን የጦር መሪዎችን ብቻ ሳይሆን ተራው ኢትዮጵያዊ ለብሶት የነበረውን ልብስ እና ፈጽሞት የነበረውን ተግባር መግለጽ ያስፈልጋል።
በአድዋ ጦርነት ላይ ሁሉም ብሄረሰብ የራሱን ብሄረሰብ አለባበስ ተጠቅሞ ነው የተሳተፈው። የትግሬ አለባበስን ለብሶ የመጣ አለ ፤ የአማራ አለባበስን ለብሶ በጦርነቱ የተሳተፈ አለ። የኦሮሞ አለባበስን ለብሶ የተሳተፈም አለ ፤ወዘተ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የወጡበትን ብሄረሰብ የሚገልጹ አልባሳት ለብሰው ነው ወደ ጦር ሜዳ የወረዱት። ስለዚህም እኛም በአሉን ስናከብር አለባበሳችንን በዚህ መልኩ ማድረግ ይኖርብናል።
ሁለተኛ፤-የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ የሆነና ፓን አፍሪካኒዝም እንዲያብብ ያደረገ ነው። ስለዚህ አፍሪካዊ እና ፓን አፍሪካዊ ገጽታው ከኢትዮጵያዊ ገጽታው አይተናነስም። ይህ በአል በሚከበርበት ወቅትም ይህ ፓን አፍሪካዊ ገጽታው ጎልቶ እንዲታይ መደረግ አለበት። ለዚህም የምንጠቀመው ቀላሉ መንገድ አልባሳት ናቸው።እዚህም ላይ ዲዛይነሮቻችን በጥምቅቱ፣ በመስቀሉ በገናው ወዘተ በአልባሳት እንዳደመቁን ሁሉ ፓን አፍሪካዊ ገጽታችንን ለማጉላት መስራት ይኖርባቸዋል።
በዘንድሮው የአድዋ ድል በአል ላይ አፍሪካዊ አልባሳትን በመልበስ አፍሪካውያንን ብሎም መላው ጥቁር ህዝብን የበአሉ አካል ማድረግ ቢቻል መልካም ይሆናል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት አፍሪካዊ አልባሳትን መልበስ በተለይ በአዲስ አበባ ተለምዷል። ይህን ልማድ ከአድዋ ድል በአል አከባበር ጋር ብናስተሳስረው ደግሞ የበለጠ መልካም ይሆናል። ያን ማድረግ የሚችሉ ዲዛይነሮችም በብዛት እንዳሉን የታወቀ ነው።
ሶስተኛ ፤-በዘንድሮው የአድዋ ድል በአል ላይ በልብሶቻችን ልናስታውሳቸው የሚገባን የዚህ ዘመን አርበኞች ነው። የአድዋ ድልን በተመለከተ ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል ያንን ድል አስጠብቀን በኢኮኖሚው እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ባለድል መሆን አልቻልንም የሚል ነው። ነገሩ እውነታነት አለው።
እርግጥ ነው ይህ ክስ እንደ ሀገር ቢሆንም፣ እንደ ግለሰብ በየተሰማሩበት መስክ ባለድል የሆኑ ጀግኖች አሉ። እነዚህ ጀግኖች በራሳቸው ልክ የራሳቸውን የህይወት አድዋን አሸንፈዋልና አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ስለዚህም ስማቸውን የያዙ አልባሳት ቢዘጋጁ አድዋ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ህያው ማስተማሪያ መሆኑን ማሳየት ይቻላል።
አራተኛ ፤ የዘንድሮውን የአድዋ በአል በአልባሳቶቻችን ለመከላከያ ሰራዊቱ እውቅና መስጠት እና ያለንን አክብሮት ማሳየት የምንችልበት ልናደርገው ይገባል። አድዋ በዋነኝነት የጦርነት ታሪክ ነው። አባቶቻችን ሀገርን ለማዳን እና ነጻነታችንን ለማስከበር ከፍተኛ የሆነውን የህይወት መስዋእትነት ከፍለው ድል የተቀዳጁበት። በዚህም ታሪክ ሲዘክራቸው እና ጀግንነታቸውንም እንደ አብነት ይዞ ሲታገል ኖሯል። ይህን ለሀገር አንድነት መስዋእት የመሆንን ታሪክ በዚህ ዘመንም መከላከያ ሰራዊታችን እና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በተግባር አሳይተዋል። ይህን ጀግንነት በዘንድሮው የአድዋ ድል በአል አከባበር ላይ ማስታወስ እና መዘከር ይገባል። ስለዚህም የፋሽን ዲዛይነሮች የሀገሪቱ ህግን በማይጥስ መልኩ እነዚህን የዘመናችን አርበኞች በአልባሳት ንድፎቻቸው እንዲዘከሩ ማድረግ ይችላሉ።
አምስተኛ፤- አድዋ የአንድ ቀን በአል አይደለም። አድዋ የአሸናፊነት ፍልስፍና ነው። ስለዚህም በየጊዜው ሊወራ ፤ ሊተነተን ፤ ሊከበር የሚገባው ድል ነው። ስለዚህም ዲዛይነሮች የሚሰሯቸው ልብሶች ለአንድ ቀን ብቻ የሚያገለግሉ ሳይሆኑ፣ ከበአሉም በኋላ ሰዎች በአዘቦት ቀንም ይሁን በበአል ቀን ሊለብሷቸው የሚችሉ መሆን አለባቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ ለበአላት ዲዛይን የሚደረጉ ልብሶች ከኢትዮጵያዊው የአለባበስ ወግ ወጣ ያሉ ሆነው ሲሰሩ አናያለን። ስለዚህም የሚዘጋጁ አልባሳት ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባርን የተላበሱ እና በማንኛውም ቦታ ሊለበሱ የሚችሉ ሆነው መሰራት ይኖርባቸዋል።
ስንጠቀልለው የፋሽን ዲዛይነሮቻችን ልክ በጥምቀት በአል ወቅት እንደሚያሳዩን የተራቀቀ ጥበብ ሁሉ በዚህ የአድዋ ድል በአል ላይም እንዲሁ አዳዲስ ዲዛይኖችን በማዘጋጀት በአሉን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፤ ብሎም አፍሪካዊ እና መላው የጥቁር ህዝብ በአል በማድረግ ረገድ ሊያግዙ ይገባል።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም