
ሁለት የአሜሪካ ሴናተሮች ሲአይኤ አሜሪካውያንን በሚስጥር እየሰለለ ነው ሲሉ ወነጀሉ። የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ዜጎቹን እየሰለለ ነው ብለዋል።
ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ሲአይኤ ዜጎች እየሰለለ እንደሆነ የተናገሩት ሴናተሮች ሮን ዋይደን እና ማርቲን ሄይንሪች ናቸው።
ሁለቱ ዴሞክራቶች ሲአይኤ ስለዘረጋው የዜጎች የስለላ መረብ ለደህንነት አመራሮች በደብዳቤ ገልጸዋል። አሜሪካ ውስጥ መንግሥት የዜጎችን የግል መረጃ በስለላ ይሰበስባል የሚል ክስ ሲሰማ የመጀመሪያው አይደለም።
ሲአይኤ እና ብሔራዊው የደህንነት ተቋም ኤንኤስኤ አገር ውስጥ ስለላ እንዳያካሂዱ እአአ በ1947 የወጣው ሕግ ያግዳቸዋል። ከአሜሪካ ውጭ ግን መረጃ መሰብሰብ ይችላሉ።
እአአ በ2013 የቀድሞው የሲአይኤ ሠራተኛ ኤድዋርድ ስኖውደን ሲአይኤ የአሜሪካውያንን የግል መረጃ ከተንቀሳቃሽ ስልካቸው እና ከበይነ መረብ እንቅስቃሴያቸው እየሰለለ እንደሆነ ለዓለም አጋልጧል።
ስለላ ይደረግባቸው ከነበሩት 90 በመቶው ተራ የአሜሪካ ዜጎች መሆናቸውን የስኖውደን የዋሽንግተን ፖስት ሐተታ ይጠቁማል።
የወቅቱ ከፍተኛ የደህንነት አመራሮች ሲአይኤ አሜሪካውያንን እየሰለለ እንደሆነ አናውቅም ሲሉ በምክር ቤት ፊት መካዳቸው ይታወሳል። ኋላ ላይ ግን በአሜሪካ ፍርድ ቤት ፕሪዝም የተባለው የሲአይኤ የዜጎች ስለላ ሕገ ወጥ ተብሏል።
ሁለቱ ሴናተሮች እንደሚሉት ሲአይኤ አሁንም በተራ አሜሪካውያን ላይ ሁለት የመረጃ መሰብሰቢያ መዋቅሮች ዘርግቷል። ይህንን ስለላ የሚያከናውነውም ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ነው።
ሲአይኤ ከዘረጋቸው ሁለት መዋቅሮች አንደኛውን ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ይፋ ቢያደርግም ሁለተኛውን የደህንንት መረጃ ለመጠበቅ ሲል ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
ሁለቱ የኒው ሜክሲኮ ሴናተሮች ሲአይኤ ሁለተኛውን መዋቅር ይፋ አለማድረጉ “ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነና የስለላ ተቋሙን ተአማኒነት የሚያሳጣ ነው” ብለዋል። አሜሪካውያን ለምን እንደሚሰለሉ፣ የተሰበሰበው መረጃ ምን ያህል እንደሆነም ይፋ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
አሜሪካን ሲቪል ሊበሬሽን ዩኒየን በበኩሉ “ሲአይኤ የትኛውን የግል መረጃችንን እንደሚሰበስብና መረጃውን እንዴት ለተጨማሪ ስለላ እንደሚያውለው ስጋት ገብቶናል” ብሏል የሲአይኤ ቃል አቀባይ “ሲአይኤ ከውጭ አገራት ግንኙነት ያላቸው አሜሪካውያንን መረጃ በተዘዋዋሪ ያገኛል” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
አያይዘውም “ሲአይኤ አሜሪካውያንን የሚመለከት መረጃ ሲያገኝ በወጣው ሕግ መሠረት መረጃውን ይጠብቀዋል። ይህ ሕግ መረጃው በምን መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውል መመሪያ ይሰጣል” ሲሉ አክለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014