ከአፍሪካ ዋነኛ የነጻነት ተምሳሌቶች እና ተወዳጅ የነጻነት ታጋዮች አንዱ ነበሩ። የነጭ አገዛዝን እምቢኝ በማለታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ። ይህ አቋማቸው ያልወደደው የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝ ለ27 ዓመታት በእስር ቤት ወርውሯቸዋል።
ለሠላም፣ ዲሞክራሲ እና ነጻነት ለሁሉም ሲሉ ሰብከዋል። ሀገራቸውም ከዘር መድልዎ አገዛዝ እንድትላቀቅ በመርዳት የደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያው ጥቊር ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል። አንደበተ-ርቱእ፣ ትሁት እና ሆደ-ቡቡ በመኾናቸውም ይታወሳሉ። ኒልሰን ማንዴላ።
የአፓርታይድ ስርአት አራማጆች እሳቸውን ወደ እስር በመወርወር ችግሩን መፍታት እንደሚችሉ ገምተው ነበር። እሳቸው ግን አልተበገሩላቸውም። ታስረውም ስርአቱን መታገላቸውን አላቆሙም። እኚህ ታላቅ የነጻነት ታጋይ ከ27 ዓመት እስራት በሁለዋ ከእስር የተፈቱት የካቲት 4 ቀን 1988 ነው። እኛም የዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ ርአስ ጉዳያችን አርገናቸዋል።
የህግ ባለሙያ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ እኤአ በ1944 የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የሚባለውን የደቡብ አፍሪካ አንጋፋ የጥቁሮች የፖለቲካ ድርጅት ተቀላቀሉ። ቀስ በቀስ በጆሀንስበርግ የድርጅቱ የወጣቶች ክንፍ አመራር ሆኑ። በ1952 ደግሞ በምህፃረ ቃል ኤኤንሲ በመባል የሚታወቀው የዚሁ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኑ።
አሁንም ለአፓርታይድ አሻፈረኝ በማለት ደምና ሁከት አልባ ተቃውሞ ማስተባበር ጀመሩ። በዚህም የነጮችን የበላይነት እና የዘር መድልዎ ስርአት በመቃወም ታግለዋል። በ1960 በሻርቪል ሰላማዊ የጥቁሮች ተቃውሞ ላይ ከደረሰው ፍጅት በኋላ ማንዴላ የፖለቲካ ድርጅታቸውን በአናሳዎቹ የነጮች መንግሥት ላይ የሽምቅ ውጊያ እንዲያደርግ ረድተዋል በሚል ተጠረጠሩ።
በ1961 ማንዴላ በአገር ክህደትና ሉዓላዊነትን በመናጋት በሚል ቢያዙም ነፃ ተብለው ተለቀቁ። በዓመቱ ኢሕጋዊ በሆነ መልኩ ደቡብ አፍሪካን ለቀቁ። ማንዴላ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ስልጠና ወስደዋል።
በ1962 ተይዘው ክስ ተመስርቶባቸውና ተፈርዶባቸው በሮቢን ደሴት ለአምስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። በ1964 እንደገና ለፍርድ ቀርበው ከብዙ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ አመራሮች ጋር ተከሰው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው።
ማንዴላ ከተፈረደባቸው 27 ዓመት እስራት 18ቱን ዓመት አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በሮቢን ደሴት ነበር ያሳለፉት። ከአልጋ በስተቀር ምንም በማታስገባ ክፍል እየኖሩ ከባድ ጉልበት የሚጠይቅ የካባ ሥራ ያሠሩዋቸውም ነበር። በስድስት ወር አንዴ አንድ ደብዳቤ ጽፎ መላክና የተላከላቸውን እንዲቀበሉ ሲፈቀድላቸው ከጎብኚዎቻቸው ጋር የሚገናኙት በዓመት አንድ ቀን ለ30 ደቂቃ ያህል ብቻ ነበር።
እንዲያም ሆኖ ግን ማንዴላ በአቋማቸው ጽኑ ሆነው ቆይተዋል። በዚህም የፀረ አፓርታድ ትግሉ ትዕምርታዊ (ምልክታዊ) መሪ መሆን ችለዋል። እስር ቤት ሆነው ፀረ አፓርታይድን በመምራት ብቻ ሳይሆን ሲቪላዊ አለመታዘዞችን በማስተባበር ባደረጉት ትግል የአፓርታይዱ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሮቢን ደሴት ያለውን የእስር ሁኔታ ሊያሻሽልላቸው ተገዷል። ቀጥሎም በቤት ውስጥ የቁም አስር ሆነው ወደ ሚጠበቁበት ቦታ ተወሰዱ።
በ989 ኤፍ ደብሊው ዴ ክለርክ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ አፓርታይድን ለማስወገድ አቀዱ። ዴ ክለርክ በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ላይ የተጣለውንም ዕገዳ አነሱ። በነማንዴላ ላይ የተላለፈውን የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት አነሱ። በፌብሩዋሪ 1990 ማንዴላ ከእሥር እንዲለቀቁ አዘዙ።
ማንዴላ ቀስበቀስ ድርጅታቸው ኤኤን ሲ ከአናሳዎቹ መንግሥት ጋር አፓርታይድን ጥሎ ሁሉን አካታች መንግሥት እንዲመሠረት ወሰኑ። በ1993 ማንዴላና ዴክለርክ የኖቤል የሠላም ሽልማት በጋራ አሸናፊ ሆኑ።
ከአንድ ዓመት በኋላ ኤኤን ሲ የሀገሪቱን የመጀመሪያ ነፃ ምርጫ አሸናፊ ሆነና ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ማንዴላ በ1999 ከፓለቲካው አለም ራሳቸውን በጡረታ አገለሉ። ከዚያም ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት እስከ ዲሴምበር 2013 ድረስ በሰላም፣ በማኅበራዊና ፍትሕ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይንቀሳቀሱ ነበር።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014