ዓለም ተፈጥሯዊ ጸጋዋን በፈጠራና በአዳዲስ ግኝቶች እያዋዛች ግስጋሴዋን ቀጥላለች። ሁል ጊዜም አዲስ ነገር ትሻለች፤ አዲስ ነገር ታስተዋውቃለች። በየጊዜው የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጆችን አሠራርና አኗኗር የሚያቀሉ ብቻ ሳይሆኑ ዘመናዊነትንም የሚያጎናጽፉ ናቸው። ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንደር እየቀየራት ባለበት በዚህ ዘመን ከኋላ ቀር አሠራር አለመላቀቅ ከዓለም ማሕበረሰብ መገለል እንደሆነ ብዙዎቻችን እንስማማለን።
ቴክኖሎጂ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኑን በአፍሪካና በሌላው ዓለም መካከል ያለውን ልዩነት ማጤን በቂ ነው። አፍሪካ ከየትኛውም አህጉር የተሻለ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ብትሆንም ይህን ጥሬ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ባለመገንባቷ በሌሎች ተበልጣለች።
አፍሪካ ዓለም ከደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ለመድረስ አዲሱን ትውልዷን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተዋወቅ ግድ ይላታል። አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ለቴክኖሎጂው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በፈጠራ የተካኑ ወጣቶችን የማፍራትና የማበረታታት ባህል እያዳበሩ መጥተዋል። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ይበል የሚያስብልና በሌሎችም ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው።
በኢትዮጵያም እንዲህ አይነት ተሞክሮዎች መታየት እየጀመሩ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ቴክኖሎጂው የፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ እየተጠቀሙ የፈጠራ ሥራዎችን ሲሠሩ እያየን ነው። የዛሬዎቹ የ”ወጣቶች” አምድ እንግዶቻችን የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ይጠቅማል የተባለ ሶፍትዌር ያበለጸጉ ጓደኛሞች ናቸው። ጓደኛሞቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ያስተዋሉት ችግር ወደ እዚህ ሥራ እንዲገቡ ያነሳሳቸው እንጂ ከዚያ በፊትም ሌሎች ሶፍትዌሮችን በማበልጸግ ሥራ ላይ አውለው እንደነበር ነግረውናል።
አሁን ‹‹ኢመላ Travel management and Booking System›› የተባለ ሶፍትዌር አበልጽገው የትራንስፖርት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ዘመናዊ አሠራርን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተዋወቁና ፍላጎትና ዝንባሌያቸው ያጣመራቸው ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከወጣቶቹ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
ክርስቲያን ተሾመ ተወልዶ አምስት ዓመት እስኪሆነው ድረስ የኖረው ሃዋሳ ከተማ ነው። ከዚያም ከቤተሰቦቹ ጋር አዲስ አበባ መጥቶ ትምህርቱን እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ የሲቪል ምህንድስና ትምህርቱን ይከታተል ነበር። በወቅቱ ከጓደኞቹ ጋር ሲተዋወቅ ሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነበር።
ሱራፌል ወርቁ በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን፣ ጎባ ከተማ ተወልዶ አድጓል። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ለከፍተኛ ትምህርት ጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን ይከታተል ነበር። በትውውቃቸው ወቅት እርሱም የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነበር።
ካዮዋቅ መለሰ በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ተወልዶ ያደገ ነው። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ በጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመደበ። ከጓደኞቹ ጋር ሲተዋወቅ የአንደኛ አመት ተማሪ ነበር። አሁን አራተኛ አመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል።
ጓደኛሞቹ በጂማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖ ካምፓስ በነበራቸው ቆይታ ወደ ካምፓስ ሲገቡና ከካምፓስ ሲወጡ በትራንስፖርት ምክንያት በሚደርስባቸው መጉላላት ይማረሩ ነበር። ችግሩ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ በመሆኑ እንዴት መቃለል እንዳለበት ሃሳብ ይለዋወጡ ነበር።
የትራንስፖርት ካምፓኒዎችና ተሳፋሪዎች ባሉበት ቦታ ሆነው መረጃ መለዋወጥ የሚያስችለውን ሶፍትዌር ማበልጸግ እንደሚቻል ክርስቲያን በዘርፉ ግንዛቤ አላቸው ለሚላቸው ጓደኞቹ ያማክራቸዋል። በሃሳቡ ይስማማሉ፤ እንደውም የራሳቸውን ጥሩ ጥሩ ሃሳብ በማከል የክርስቲያንን ሃሳብ ያሳድጉታል። ወጣቶቹ ክሂሎቻቸውን በማውጣጣት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ያሰቡትን ሶፍትዌር ማበልጸግ ይጀምራሉ። ሁሉም ለሶፍትዌሩ መበልጸግ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
መነሻቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡና ሲወጡ የሚፈጠረውን የትራንስፖርት እጥረትና መተረማመስ ለማስወገድ ያለመ ቢሆንም በተለይም በዓመት በዓልና በተለያዩ ምክንያቶች ማሕበረሰቡም በዚህ አይነት ችግር የሚፈተን መሆኑ የችግሩን ደረጃ ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።
ወጣቶቹ ስለ ፈጠራ ሥራቸው ጥቅም እንዲህ ያስረዳሉ፤ የትራንስፖርት ዘርፉን ያዘምናል፤ በመናኽሪያ ውስጥ የሚታየውን ሰልፍ ያስቀራል፤ ሰዎችን ከስርቆትና ከአደጋ ይታደጋል፤ ሕገ-ውጥ የቲኬት ሽያጭን ለመቆጣጠርና ዘመናዊ አሠራርን ለመከተል ያስችላል።
ክርስቲያን በትራንስፖርት ዘርፍ ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ትኬት የመቁረጥ ልምድ የላቸውም ይላል። በተለይም አሁን አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ዘመናዊ ባሶች ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ አሠራርን ቢከተሉ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል፤ ለደንበኞቻቸውም የአግልግሎት እርካታ መስጠት ይችላሉ። ተጓዦች በአገልግሎቱ ያላቸውን ማንኛውንም አይነት አስተያየት በአግባቡ ማድረስ ያስችላቸዋል። ትኬት መሸጫ ቢሮዎች ከሥራ ሰዓት ውጪ ዝግ ስለሚሆኑ እንዲህ አይነቱ አሠራር ቢዘረጋ በማንኛውም ጊዜ ትኬት ማግኘት ያስችላል። የትኬት ግዢን በጥሬ ብር መፈጸም ኋላ ቀርነት ነው የሚለው ክርስቲያን ዘመኑ ያፈራውን የቴሌ ብር አገልግሎት ጥቅም ላይ በማዋል ሰዎች ከጥሬ ብር ዝውውር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማስቀረት ያስፈልጋል። ሶፍትዌሩ መጉላላትና እንግልትን ከማስቀረትም ባሻገር ዓለም የሚከተለውን ዘመናዊ አሠራር ወደ ማሕበረሰቡ ለማስረጽ እራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብሏል።
ወጣቶቹ ያበለጸጉት ይህ ሶፍትዌር በኢትዮጵያ አዕምሮ ንብረት ጽህፈት ቤት ህዳር 20 2014 ዓ.ም የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቶታል። ወጣቶቹ በአሁኑ ሰዓት “ቢቶፒያ አይቲ ሶልውሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር” በሚል መጠሪያ ማሕበር መስርተው ሥራቸውን ለተለያዩ የትራንስፖርት ካምፓኒዎች በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።
ወጣቶቹ ማሕበሩ እስከ አሁን ድረስ ከመንግሥት የተደረገለት ምንም አይነት ድጋፍ እንደሌለ ነግረውናል። የፋይናንሰ ድጋፍ ያደረጉላቸው ግለሰቦች ግን አሉ። ግለሰቦቹ ድጋፍ ያደረጉላቸው ባዩት ነገር ደስ በመሰኘታቸውና ሲስተሙ ጥቅም ላይ ቢውል ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም እንዳለው ስለተረዱ ነው ይላሉ።
አብዛኛዎቹ የትራንስፖርት ድርጅቶች ሲስተሙን ሲመለከቱ ደስተኛ ይሆናሉ። ምክንያቱም በርካታ ሥራዎችን እንደሚያቀልላቸው ይረዳሉ። ሠራተኞቻቸውን በአግባቡ ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል፤ ደንበኞቻቸውንም ለመያዝ ይረዳቸዋል፤ በየቀኑ የሚገባውን ትክክለኛ ገቢ ለማወቅ ያስችላቸዋል። ይህ ሁሉ ፋይዳ ይኑረው እንጂ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ አንገብጋቢ ጉዳይ መስሎ ስለማይታያቸው ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነው ይላሉ።
በአንድ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር “አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል አለባችሁ” ብሎ የተወሰነ ግፊት አድርጎ ነበር። በዚያን ጊዜ ከፍተኛ መነቃቃትና ፍላጎት ያንጸባርቁ በርካታ ካምፓኒዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ግን የአገሪቱን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተከትሎ ጉዳዩ ከትኩረት ውጭ እየሆነ መጥቷል። በዚህ የተነሳ “ለደንበኞቻችን የተሻሻለና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንስጥ” የሚለው አዲስ አስተሳሰብ ማደግና ወደ ፊት መራመድ አልቻለም ይላል ክርስቲያን። ከተለመደው ባህላዊ አሰራር ቶሎ የመላቀቅ ፍላጎትም አይታይም።
ከዘመናዊ አሠራርና ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርርብ ያላቸው አንዳንድ የካምፓኒ ሃላፊዎች ግን ሲስተሙን ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጹላቸዋል። ከአስራ ዘጠኝ በላይ የሚሆኑ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች መካከል ሶፍትዌሩን የመጠቀም ፍላጎት ያሳዩት ከሶስት አይበልጡም።
አሠራርን የሚያቀላጥፉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤትችን መንግሥት ግፊት በመፍጠር እንዲተገበሩ ካላደረገ በስተቀር ካምፓኒዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የመለወጥ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ወጣቶቹ ይናገራሉ። እንደ ወጣቶቹ አባባል ከኋላ ቀር አሠራር የመውጣት ፍላጎት ከሌለ እድገትና ሥልጣኔ ሊመጣ አይችልም። ሶፍትዌሩ እስከ አሁን ድረስ ወደ ሥራ እንዳይገባ ያደረገው በተለይም በትራንስፖርት ሼር ካማፓኒዎች በኩል ከኋላ ቀር አሠራር የመላቀቅ ቁርጠኝነት አለመኖር ነው።
“ቢቶፒያ አይቲ ሶልውሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር” ሲስተሙን ከቴሌ ብር ጋር አስተሳስሮ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ቢሆንም የካምፓኒዎች ቁርጠኛ አለመሆንና አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ የሚያስገድድ ሕግ ባለመኖሩ ማሕበሩ ወደሥራ እንዳይገባ ማነቆ ሆኗል።
ማሕበሩ ሥልጠና እና የሶስት ወር ነጻ አገልግሎት የመስጠት እቅድ ይዞ ቢንቀሳቀስም እስከ አሁን ሲስተሙን የሞከረ የትራንስፖርት ካማፓኒ የለም። ሁሉም ካምፓኒዎች ከመሞከራቸው በፊት “ማን ተጠቅሞት ያውቃል?” የሚል ጥያቄ በማንሳት አርአያ የሚሆናቸውን ሲያጡ የመጠቀም ፍላጎታቸው ይቀዘቅዛል።
የማሕበሩ አባል ክርስቲያን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር አማካሪ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የመነጋገር እድል አግኝቶ እንደነበር ይገልጻል። በውይይቱ ወቅትም በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ካማፓኒዎች ዘመናዊ አሠራርን እንደሚፈልጉ እና ኢመላም ይህንን ክፍተት ሊሞላ እንደሚችል በቴክኖሎጂው አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል። ካማፓኒዎቹ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎትን መጠቀማቸው በአንድ በኩል ሥራቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳቸውና፤ በሌላ በኩል አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማበረታታት መሆኑን መክረዋል።
ይሁንና ዘርፉን የሚመራው አካል ገና ባለመሾሙ ምክንያት እንደተባለው በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አልተቻለም ነበር። አሁን ግን በቦታው ላይ ሰው ስለተመደበ ከቅርብ ቀን በኋላ መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ አድርገዋል። መንግሥት ሶፍትዌሩን ሥራ ላይ በማዋል በመናኽሪያዎች አካባቢ ያለውን አሠራር በማዘመን የሕብረተሰቡን የትራንስፖርት አጠቃቀም በማቅለል ፈጠራውን ማበረታታት ይኖርበታል ባይ ነው።
መንግሥት የሥራ እድል ፈጠራ መርሃ ግብር ዘርግቶ በርካታ ወጣቶችን ብድር እያመቻቸ ወደ ሥራ እንደሚያስገባ የተናገረው ክርስቲያን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶችም ተመሳሳይ ድጋፍ የማድረግ ልምድ ቢዳብር ችግር ፈቺ ግኝቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል ይላል።
ዓለም እየተመራች ያለችው በቴክኖሎጂ እንደመሆኑ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቁ ያለ ሥራ የተቀመጡ ወጣቶች ቢታገዙ ለአገር የሚተርፍ ፈጠራ ማፍለቅ እንደሚችሉ ሥራቸው ማሳያ እንደሆነ ወጣቶቹ ተናግረዋል።
‹‹ኢመላ Travel management and Booking System›› ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መስራት የሚያስችል ሶፍትዌር በመሆኑ ማሕበሩ ወደ ፊት በሌሎች በርካታ ማሕበራዊ ጉዳዮች የሚስተዋሉ ኋላ ቀር አሰራሮችን በዘመናዊ አሠራር የመተካት ራዕይ አለው ብለዋል። በተለይም ቢዘነስ ነክ ዝውውሮችን ለማቀላጠፍ ይሰራል። ለምሳሌ በሆቴልና ማኔጅመንት ዘርፍ፤ በመዝናኛዎች /ሲኒማዎች/ ሰዎች በያሉበት ቦታ ሆነው የመግቢያ ትኬት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ታስቧል።
ሱራፌል የፈጠራ ሥራ የሚሰሩ ወጣቶች የሚፈለገውን ድጋፍ እንደማያገኙ ይናገራል። መንግሥት በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከማበረታታት ይልቅ የቴክኖሎጂ ማዕከል የሆኑ እንደ ኢንሳ ያሉ የመንግሥት ተቋማትን ያበረታታል ይላል። በወጣቶች ላይ አመኔታ አሳድሮ ድጋፍ ቢያደርግ በቴክኖሎጂ የበለጸገች አገር መፍጠር ይቻላል ነው የሚለው።
እንደ ሱራፌል ሙያዊ አስተያየት ከውጭ የመጡ ሶፍትዌሮችን ከመጠቀም ይልቅ አገር በቀሎችን መጠቀም ቢቻል በቴክኖሎጂው ዘርፍ አቅምን የማሳደግ እድል ይፈጠራል።
አሁን የተወሰንነው በሶፍትዌር ላይ ነው። ወደ ፊት አፕሊኬሽኖችን የማበልጸግና ወደ ሀርድዌሮች የመሸጋገር ህልም አለን የሚለው ደግሞ ወጣት ካዮዋቅ ነው። ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ያለች አገር እንደ መሆኗ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያልተሞከሩ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል ብሏል። ዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አንድ ሳይባል ሁለት አይባልም ያለው ወጣቱ ከትንንሾቹ ሥራዎች ሳንጀምር ትልልቁ ላይ መደረስ አይቻልም ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል። ችሎታውና ዝንባሌው ያላቸው ወጣቶች ሌላ አካልን ከመጠበቅ እራሳቸው እየተደራጁ ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ መከተል እንደሚገባቸውም መክሯል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2022