የአሜሪካ መንግሥት በሶማሊያ ዴሞክራሲ እክል ፈጥረዋል ያላቸው ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታወቀ::
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የቪዛ ዕቀባው በተቃዋሚዎች ላይ ኃይል በሚጠቀሙ መሪዎች ላይም ተፈጸሚ ይሆናል ብለዋል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ ማዕቀብ የተሰማው ሶማሊያ አጠቃላይ ምርጫ መካሄድ ከነበረበት ጊዜ አንድ ዓመት በዘገየችበት ጊዜ ነው።
የፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ የሥልጣን ዘመን ካበቃም አንድ ዓመት አስቆጥሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምክንያታዊ ያልሆነ እስር በሚፈጽሙ፣ በጋዜጠኞች እና በታቃዋሚዎች ላይ ጫና በሚያሳድሩ እና በምርጫ ሂደት ላይ መሰናክል በሚፈጥሩ ላይ የቪዛ ማዕቀቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል። ይህ የቪዛ ማዕቀብ በባለሥልጣናቱ የቅርብ የቤተሰብ አባላት ላይም እንደሚጣል አንቶኒ ብሊንከን ሶማሊያን በሚመለከት ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።
“ማዕቀቡ የምርጫ ሂደትን ባደናቀፉ እንዲሁም ምርጫን በተያዘለት ጊዜ ተአማኒነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡትን ይመለከታል” ብለዋል።
አያይዘውም ጋዜጠኞች እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በማስፈራራት፣ በማሰር እና በማንገላታት እጃቸው ያለበት ባለሥልጣኖች በቪዛ ዕቀባው እንደሚካተቱ አክለዋል።
“የሶማሊያ ብሔራዊ እና የፌዴራል መንግሥቱ አመራሮች ተአማኒ እና ግልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ነበረባቸው” ብለዋል ብሊንከን።
አገራቸው በሶማሊያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለመተባበር ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ፈርማጆ የፓርላማ እንዲሁም የፕሬዝደንታዊ ምርጫን አራዝመው ሥልጣን ላይ ለመቆየት መወሰናቸው ሶማሊያን ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ከከተታት ሰነባብቷል።
ሶማሊያ የፓርላማ ምርጫን እስከ የፊታችን የካቲት 27 አከናውና ወደ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንደምትሄድ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014