
የካናዳ መዲና ኦታዋ ከንቲባ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎች አመጽን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ። ጂም ዋትሰን በመዲናዋ የተቃዋሚዎች ቁጥር ከፖሊስ በልጦ ኦታዋ “ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጪ ሆናለች” ብለዋል። ከንቲባው ተቃዋሚዎቹ ለነዋሪዎች የደህንነት ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደረቅ ጭነት አሸከርካሪዎቹ ‘ፍሪደም ኮንቮይ’ በሚል መሪ ቃል የጀመሩት እንቅስቃሴ መንግሥት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች አስገዳጅ የኮቪድ ክትባት መውሰድ አለባቸው ማለቱን ተከትሎ ነው። አሽከርካሪዎቹ መኪኖችን በማቆም እና ድንኳኖችን በመትከል የኦታዋን መሃል ከተማን ከእንቅስቃሴ ውጪ አድርገዋል።
ከንቲባው ሲኤአርኤ ለተባለ የካናዳ ሬዲዮ ሲናገሩ፤ ተቃዋሚዎቹ ሳያቋርጡ የጡሩምባ ድምጽ እና ርችት እየተኮሱ ‘ግዴለሽነታቸውን’ እያሳዩ ነው በለዋል።”በግልጽ በቁጥር ተበልጠናል። . . . ይህ መቀየር አለበት። ከተማዋን መልሰን መያዝ አለብን” በማለት ከንቲባው ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ከንቲባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅን ተከትሎ ባለሥልጣናት ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ ባይገልጹም፤ ፖሊስ ግን የኃይል ጭማሪ እንደሚያደርግ እና ለተቃውሞ ሰልፎች ድጋፍ የሚሰጡትን በቁጥጥር ሥር እንደሚያውል አስታውቋል።
አዋጁ የከተማ አስተዳደሩ ለድንገተኛ አደጋ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች አገለግሎቶችን እንዲሰጥ ያስችለዋል ተብሏል። የከተማው አስተዳደር በመግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን የአደጋ እና የደህንነት ከባድ ስጋት የሚያንፀባርቅ ሲሆን የሌሎች ግዛት እና የመንግሥት አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል ብሏል። በርካታ የኦታዋ ነዋሪዎች ሰልፉን ተቃውመዋል።
ፖሊስ ከሠላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ ከ60 በላይ ምርመራዎችን እያደረገ መሆኑን እሑድ ዕለት አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል “ስርቆት፣ የጥላቻ ወንጀሎች እና የንብረት ውድመት” ይገኙበታል። በርካታ ሰዎች መታሰራቸውንና ተሽከርካሪዎችም መያዛቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በኦታዋ የተካሄደውን ተቃውሞ ለመቀላቀል ለሰዓታት በመኪና የተጓዘች አንዲት ሰልፈኛ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ሰልፉ “ስለ ነጻነታችን” የሚደረግ ነው ብላለች።” የምናውቃቸው ሁለት ጓደኞቼ በእነዚህ ግዳጆች ምከንያት ሥራቸውን አጥተዋል” ስትል የኮቪድ ክትባቶች ደህንነት እና ውጤታማነት ላይ ስጋት እንዳላት ተናግራለች።
ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴው የተቀሰቀሰው የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎች የአሜሪካ-ካናዳ ድንበርን ሲያቋርጡ የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ እንዳለባቸው ባለፈው ወር የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014