
ሰሜን ኮሪያ በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ክሪፕቶከረንሲ ሰርቃ የሚሳዔል አቅሟን እያሳደገችበት ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታወቀ። በፈረንጆቹ ከ2020 እስከ 2021 አጋማሽ ባለው ጊዜ የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ጥቃት አድራሾች ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዲጂታል መገበያያ መስረቃቸውን ምርመራው ይፋ አድርጓል።
እኚህ የሳይበር ጥቃቶች ለፒዮንግያንግ የኒውክልዬርና ባለስቲክ ፕሮግራም ማጠናከሪያ “ጠቃሚ የገቢ ምንጭ” ሆነዋል ይላል የተመድ ሪፖርት። የምርመራው ውጤት ባለፈው አርብ ነው ለተባበሩት መንግሥታት ቅጣት ሰጪ ኮሚቲ የተላለፈው። የሳይበር ጥቃቶቹ ቢያንስ ሶስት ጊዜ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ የተካሄዱ ዝውውሮችን ዒላማ ያደረገ ነው ተብሏል።
ሪፖርቱ፤ የሰሜን ኮሪያ ሳይበር ጥቃት አድራሾች ባለፈው ዓመት ብቻ 400 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው ዲጂታል ገንዘብ ሰርቀው ሊሆን ይችላል ሲል ቼይአናሊሲስ የተሰኘ ድርጅት ዋቢ አድርጎ አስነብቧል። በፈረንጆቹ 2019 ሰሜን ኮሪያ ለሚሳኤል ፕሮግራሟ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ 2 ቢሊዮን ዶላር በሳይበር ጥቃት አማካይነት አከማችታለች ሲል የተባበሩት መንግሥታት ወቅሶ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊዬርና ባለስቲክ ሚሳኤሎች ሙከራ እንዳታደርግ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እገዳ ተጥሎባታል። ምንም እንኳ ሰሜን ኮሪያ የተለያዩ ከባድ ቅጣቶች ቢጣልባትም የባለስቲክና እና ኒውክሊዬር ሚሳዔል ግንባታዋን ገፍታበታለች ሲል የተባበሩት መንግሥታት የለቀቀው ዘገባ ይጠቁማል።
ሰሜን ኮሪያ ከዲጂታል መገበያያው ክሪፕቶከረንሲ ባለፈው ቁሳቁስ፣ ቴክኖሎጂና እውቀት ከተቀረው ዓለም በተለያየ መላ እየወሰደች ነው ሲል ሪፖርቱ ፅፏል። የተባበሩት መንግሥታት ቅጣት ሰጪ ኮሚቴ ፒዮንግያን ሚሳዔል ሙከራዋን ቀጥላበታለች ይላል።አሜሪካ ባለፈው አርብ ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር ብቻ ዘጠኝ የሚሳኤል ሙከራዎች አድርጋለች ብላለች።
በተመሳሳይ አርብ ዕለት ቻይና እና ሩሲያ፤ የሰሜን ኮሪያን ሚሳኤል ሙከራ የሚተች መግለጫ ላይ አንፈርምም ብለዋል። እሑድ ዕለት አሜሪካ እንዳስታወቀችው የሰሜን ኮሪያ ልዩ ልዑክ ከጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ያወራሉ። የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ አክሎ በሰሜን ኮሪያ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየዘቀጠ ነው ብሏል። ይህ የሆነው አገሪቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ድንበሯን ሙሉ በሙሉ በመዝጋቷ ሊሆን እንደሚችልም ቢቢሲ ዘግቧል።
ከሰሜን ኮሪያ የሚወጣው መረጃ ውሱን መሆን በዓለም አቀፍ ማዕቀቦች አገሪቱ ምን ያህል እየተጎዳች እንደሆነ ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014