በጥምቀት በዓል ሴቶች የቆነጠጡ 122 ልጆች ተቀጡ
ድሬዳዋ ፤(አ-ዜ-አ) ባፈው የከተራና የጥምቀት በዓል ሰሞኑን ሕዝብ ደስታውን በመግለጥ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ጭፈራ በሚደረግበት ሥፍራ እየተዘዋወሩ በተለይ ሴቶች ልጆችን ፀጥታ በመንሳት ሲጐነታትሉና ከኪስ ውስጥ ገንዘብ ሲያወልቁ የተያዙት ፻፳፪ የድሬዳዋ ወጣቶች በፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ተያዙ።
ከጥር ፲ እስከ ፲፪ ቀን ፷፫ ዓ.ም ድረስ በተከበረው በዚሁ በዓል ሰሞን ሴቶችን ፀጥታ በመንሳት ሲጐነታትሉ የተያዙት ፺ ጐረምሶች በዕለቱ የስካር መንፈስ ተጭኗቸው ስለተገኙ፤ ለተወሰነ ጊዜ ከታሠሩና ስካራቸው ከበረደላቸው በኋላ ለወደፊቱ ይህን ከመሰለው መጥፎ ተግባር እንዲርቁ የማስጠንቀቂያ ምክር ተሰጥቷቸው ሲለቀቁ፣ በድብደባ ወንጀልና በኪስ አውላቂነት የተያዙት ፴፪ቱ ደግሞ ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ ድረስ
በጣቢያ ታስረው የሚቆዩ መሆኑን የድሬዳዋ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ በሰጡት ዜና ገልጠዋል።
በተለይ በድብደባና ከኪስ ውስጥ ገንዘብ አውልቀዋል ተብለው የተከሰሱት ወጣቶች የተያዙት እጅ ከፍንጅ መሆኑን የጣቢያው አዛዥ አስረድተዋል። የድሬዳዋ ፖሊሶች በበዓሉ ሰሞን ልዩ ልዩ ጨዋታዎች በሚደረጉባቸው ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ ባደረጉት ጥብቅ ቁጥጥር ፻፳፪ ጐረምሶች ለመያዝ መቻላቸውን የጣቢያው አዛዥ የመቶ አለቃ ታደሰ ሀብቴ ገልጸዋል።
እነዚሁ ፻፳፪ ጐረምሶች ሴቶችን በመጐነታተል ሲቆነጥጡና ከኪስ ውስጥ ገንዘው ሲያወልቁ የተያዙት በጥምቀተ ባህርና በአብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ በተደረጉት ልዩ ልዩ ጨዋታዎች መካከል እየጠሸለኮለኩ በመግባት መሆኑ ታውቋል።
(ጥር 15 ቀን 1963 ዓ.ም)
በሞተው ሕፃን ለቅሶ ላይ ሁለት አባቶች ተጣልተው አንደኛው ቆሰለ
ድሬዳዋ ፤(ኢ.ዜ.አ) በድሬዳዋ ከተማ የ፰ ወር ዕድሜ የነበረው አንድ ሕፃን ልጅ ባረፈበት ፤ባለፈው ሳምንት ፤በለቅሶ ላይ ከተገኙት የሕፃኑ አባቶች ነን በሚሉ ሁለት ሰዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት አንደኛው መቁሰሉን የድሬዳዋ ፪ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ገለጡ።
የሟች እናት ወይዘሮ በላይነሽ ተድላና አቶ አበበ በጅጋ በወዳጅነት ሲኖሩ ፤ በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ተለያይተው ነበር። ከዚያም በኋላ ወይዘሮ በላይነሽ ከአቶ ፀጋዬ ወልደማርያም ጋር በወዳጅነት ስትኖር ፍሬው ተስፋዬ የተባለ ልጅ ተወለደ።
ወይዘሮ በላይነሽ ተድላ ለሁለቱም ወዳጆቿ ልጅ የወለደችላቸው መሆኑን ስለገለጠችላቸው ፤ሁለቱም ሰዎች ካለማወቅ እንደ ልጃቸው ያሳድጉት እንደነበር ታውቋል።
ፍሬው ተስፋዬ ጥር ፲፱ ቀን ፷፫ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ‹‹ልጄ ልጄ! ›› እያሉ ሁለቱም አባት ነን ባዮች ማልቀስ ጀመሩ። በዚሁ ጊዜ ‹‹መቼ የወለድከው ነው?›› በመባባል በመካከላቸው በተፈጠረው ጠብ አበበ በጅጋ የመፈንከት አደጋ ደርሶበታል።
ወ/ሮ በላይነሽ ተድላ ወዲያውኑ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቀርባ ልጁ የአቶ ተስፋዬ መሆኑን በመግለጥ፤ ወንጀል እንዳይፈጸም አመልክታለች።
በዚሁ መሠረት የቀብሩ የሥነ ሥርዓት እስሲፈጸም ድረስ አቶ አበበ በጅጋ በ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ ቆይቶ በማግሥቱ የተለቀቀ መሆኑን የጣቢያው አዛዥ ገልጠዋል።
(ጥር 26 ቀን 1963 ዓ.ም)
ሊገድል ሄዶ ተገደለ
ከበደው ኡጋአ የተባለው ሽፍታ ለታ በዳዳ በተባለው ሰው መገደሉን ከሸዋ ፖሊስ የማስታወቂያና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ተገለጠ፡፡ ከበደ በጅባትና ሜጫ አውራጃ ግንደ በረት ወረዳ ውስጥ ረጋሣ ኡርጌ የተባለውን የሚስቱን ወንድም በመግደል ሸፍቶ ሰላማዊውን ሕዝብ ያውከ እንደነበር ታውቋል፡፡
ይኸው ተከሳሽ እንደገና ለታ በዳዳን ጥር ፱ ቀን ፷፫ ዓ.ም ለመግደል ሲሄድ ገዳዩ ነቅቶበት የተገደለ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
(ጥር 15 ቀን 1963 ዓ.ም)
ሥጋ ስጠኝ አልሰጥም በሚል ምክንያት ሰው ገደለ የተባለው ሥጋ ሲበላ ተያዘ
አሰላ ፤(ኢ/ዜ/አ) በሥጋ ምግብ መውደድ ምክንያት ሰው ገድሏል ተብሎ ይፈለግ የነበረው ቱሉ ዲንኪ ወንጀሉን በፈጸመ ፳፰ ወሩ ዴራ ከተማ ውስጥ ከአንድ የሉካንዳ ቤት ገብቶ ሥጋ ሲበላ ተያዘ ።
ቱሉ ዲንኪ በሉካንዳ ቤቱ ሥጋ ሲበላ በተያዘ ጊዜ የአባቱን ስም በመለወጥ ‹‹ቱሉ ደጉ ነኝ›› በለማት አጭበርብሮ ለማምለጥ ሞክሮ ሳይሳካለት በመቅረቱ ወንጀሉን የፈጸመበትን ቦታ መርቶ አሳይቷል።
ቱሉ ዲንኪ ከ፪ ዓመት ከ፬ ወር በፊት ጎዳ አያና የተባለውን ሰው ሥጋ ገዝቶ ወደ ቤቱ ሲሄድ የያዘውን ሥጋ እንዲሰጠው ጠይቆት አልሰጥም ስላለው ማጅራቱን
በዱላ መትቶ የገደለው መሆኑን የሂጦሳ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ የ፲ አለቃ ታደሰ ገብረ ጻዲቅ ገልጠዋል።
ቱሉ በዚህ መሠረት ተከሶ ባለፈው ሳምንት አሰላ ያስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ በቀጠሮ ወደ ወህኒ ተልኳል።
ቱሉ ዲንኪ ወንጀሉን የፈጸመው በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላሎ አውራጃ በሂጦሳ ወረዳ ቦሩ በተባለው ወንዝ አጠገብ ሲሆን፤ የተያዘውም በዚሁ ወር መጀመሪያ መሆኑ ታውቋል።
(ጥር 21 ቀን 1963 ዓ.ም)
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014