ፋሽን ዘመንን ይገልጣል፤ ወቅትን ያሳውቃል። አንድ ያየነው አለባበስ በየትኛው ዘመን ይዘወተር የነበረ ፋሽን ነው ተብለን ስንጠየቅ ወቅቱን የምንናገረው ለዚህ ነው። በመሆኑም በብዙዎች ተወዶ የሚዘወተረው የዚያ ዘመን ምልክት የወቅቱ ማሳያና መግለጫ ይሆናል።
ፋሽን በዕድሜ በፆታ እና በባህል ውስጥ የተለያየ ምልከታና ፍልስፍና አለው። አንዱ መርጦና ፈልጎ የመልበሱን ያህል ሌላው በበጎ ተፅእኖ ያንን ይከተላል።
የወደደውንና የፈለገውን የመልበሱን ያህል የወደዱለትና የመረጡለትን የሚለብስ የፋሽን መታያ የሚሆን ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው። ሕፃናት በፋሽን ኢንዱስትሪው ያላቸው ቦታ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሕፃናትን ከፋሽን ጋር፣ ልጆችን ከወቅቱ አልባሳትና ማጌጫ ጋር ማሰቡ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው።
ልጆች የተገኙበትን ዘመን መምሰላቸው፣ በዚያ ዘመን ግኝትና ፈጠራ ውስጥ ማለፋቸው አይቀሬ ነውና ዘመናቸውን የመሰለ ልብስና ማጌጫ ይጠቀማሉ። ይህ ማለት ከዘመናቸው የወጣ አለባበስ አይከተሉም ማለት ግን አይደለም፤ የባህል አልባሳትን፣ የአዋቂ አልባሳትን እንዲለብሱ በዘመናዊ ዝግጅት ውስጥ እንዲያልፉ / ፋሽንን እንዲላበሱ በማድረግ/ የተደረጉ አልባሳትን ሲለብሱ የሚታዩበት ሁኔታ አለ። ይህም በበዓላት ወቅት ተለምዷል።
ዘመናዊ አለባበስ ወይም ፋሽኑ ግን በብዛት ጎልቶ ይታያል። በሰርጉ፣ በልደቱና በመሳሰሉት ሁሉ ፋሽንን መሠረት አድርገው በተዘጋጁ አልባሳት ሲደምቁ ይታያሉ። በእነዚህ አጋጣሚዎች እነ ማሙሽና ሚጣ በአልባሳት ዝንጥ፣ በፀጉር አሠራርና ቁርጥ እምር ድምቅ ብለው እናያቸዋለን። ምንም እንኳን ለመልሰቡና ለመዘነጡ ምክንያት ወላጆችና ታላላቆች ቢሆኑም፣ በራሳቸው የተሠራ ቀለም በዕድሜያቸው የተለካ ማጌጥና በልካቸው የሚዋቡበት ፋሽን እነሱም ጋር አለ።
ሕፃናቱ የተገኙበት ዘመን የፈጠረላቸውን ተጎናጽፈው በእናት እቅፍ አልያም በአባት ጉያ ተጣብቀው እናገኛቸዋለን። በእርግጥም እነርሱ መዘነጫቸውን የመምረጡ ዕድል አግኝተው፤ ይሄ ከዚህ ጋር ይሄዳል፣ ያኛው ለዚህ ዘመን ተገኝ ብሩ ይመጥናል ብለው በራሳቸው አይመርጡ ይሆናል።
ለዚህ ደግሞ ከራሴ አስቀድሜ ለልጄ የሚሉት ወላጆች ኃላፊነት ይወስዳሉ። ወላጆች ገበያ ወጥተው የወደዱትና ሌላው ላይ አይተው ለልጄ ብገዛው ያሉትን ልብስ ይገዛሉ። ጌጣ ጌጦችን ለመግዛት ይደራደራሉ። ሕፃናቱም በወላጆቹ ምርጫ ይዋባሉ። ከተዘጋጁ ልብስ መሸጫ መደብሮች ውስጥ የሕፃናት አልባሳት የሚሸጡት ላይ ትኩረት አደረግን። አራት ኪሎ ድንቅስራ ሕንፃ ምድር ላይ የተዘጋጁ ሕፃናት አልባሳት መሸጫ ሱቆች ውስጥ ወደ አንዱ ጎራ ብለን ስለ ሕፃናት አልባሳት ገበያ ጠየቅን።
ሮማን በፍቃዱ ትባላለች፤ በሱቋ ውስጥ ለሽያጭ የሚሆኑ የሕፃናት አልባሳት በብዛት አዘጋጅታ ደንበኞቿን በመጠባበቅ ላይ ናት። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት በሁሉም መስክ የሥራ መቀዛቀዝ መኖሩን የምትገልፀው ሮማን፣ የሕፃናት አልባሳት በአንፃራዊነት ከሌሎች አልባሳት ገበያዎች የተሻለ የገበያ እንቅስቃሴ እንዳለው ትናገራለች።
ገና ከተወለደ ሕፃን መታቀፊያ ጀምሮ የተለያዩ የልጆች ፋሽን አልባሳት የምትሸጠው ሜሮን አልባሳቱን አብዛኛዎቹን ከውጭ አገር እያስመጣች ነው ለደንበኞቿ የምታቀርበው። ቻይና፣ ቱርክ፣ ዱባይና ጣሊያን በአብዛኛው የሕፃናት አልባሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣባቸው አገራት ናቸው። በአገር ውስጥ የሚመረቱ የሕፃናት አልባሳት በሱቋ ውስጥ የሉም። ለዚህም እንደ ምክንያት የምትጠቅሰው በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የሚዘጋጁ አዳዲስ ዲዛይን የሕፃናት አልባሳት በኅብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ አለመሆናቸውን ነው።
ለዚህም እንደ ምክንያት የምትገልፀው ልብሶቹ የሚዘጋጅባቸው ጨርቆች ለሕፃናቱ ምቾት የሚሰጡ አለመሆናቸውን ከደንበኞቿ ደጋግማ እንደምትሰማ ትናገራለች። አልባሳቱ እንደሚሠራባቸው ቁስና የጥራት ደረጃ ከ250 ብር እስከ 900 ብር ድረስ ዋጋ ወጥቶላቸው ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ የገቡ የሕፃናት ፋሽን አልባሳት በዋጋቸው ከዘገዩት ይበዛሉ።
በተናጠል የሕፃናት መታቀፊያ ከ300 እስከ 600፣ ሙሉ ልብስ ከ340 ብር እስከ 900 ብር፣ካኒቴራ ከ80 ብር እስከ 150፣ሱሪ ከ90 ብር እስከ 350 ብር ድረስ ዋጋ ወጥቶላቸዋል። ወይዘሮ ማህሌት ውላቸው ለ4 ዓመት ልጅዋ ልብስ ስትገዛ እዚያው መሸጫ ሱቅ ውስጥ አገኘናት።
ወይዘሮ ማህሌት የሦስት ልጆች ናት። ከራሷ በላይ የምትሳሳላቸው ልጆቿ ዘንጠው ሲውሉ፤ አምሮባቸው ሲደምቁ እጅጉን ያስደስታታል። ከራሷ በተሻለም አዳዲስ የልጆች ፋሽን አልባሳት የመግዛት ልምድ አላት። አቅሟ በፈቀደው መጠን ጊዜን ጠብቃ ልጆቿን ታለብሳለች። አልባሳቱን በአብዛኛው የምትገዛው በዓል በደረሰ ጊዜ ቢሆንም፣ ሌሎች ልጆች ለብሰውት ያየችው አዲስና ፋሽን ልብስ የራሷ ልጆች እንዲዋቡበት ትገዛለች።
በአሁኑ ጊዜ ሕፃናት የተለያዩ ፋሽን አልባሳት በብዛት እየተለመደ መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ ማህሌት፤ ልጆች ስለ ፋሽን ግንዛቤው ባይኖራቸውም በተለያየ ጊዜ ወቅት ጠብቀው የሚመጡ የሕፃናት አልባሳት ወላጆች ተከታትለው ልጆቻቸውን ያለብሳሉ።
በተለይም ወቅታዊ አልባሳት ክረምትና በጋ በመጣ ቁጥር ለወቅቱ ምቹና ወቅታዊ ፋሽን የተከተሉ አልባሳት ለልጆች መርጦ መግዛትና ማስለበስ ተለምዷል። ገበያ ውስጥ የሚገኙ የልጆች አልባሳት በአብዛኛው ከውጭ አገር ተሠርተው የሚገቡ መሆናቸውን የታዘበችው ወይዘሮ ማህሌት፣ በአገር ውስጥ ዲዛይነሮች የተሠሩ አገራዊ ልብሶች ገበያው ላይ ሊኖሩ እንደሚገባና አገራዊ ምርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ታስገነዝባለች።
ዲዛይነር ሀቢባ ሙኒር ከ4 ዓመት በላይ ሙያው ላይ ቆይታለች። ጀሞ አካባቢ በሚገኘው ሱቋ ውስጥ በአብዛኛው የአዋቂ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት በራሷ ዲዛይን አዘጋጅታ ለገበያ ታቀርባለች። ዲዛይነር ሀቢባ ከሁለት ዓመት በፊት የሕፃናትና የልጆች አዳዲስ ዲዛይን አልባሳት አዘጋጅታ በሱቋ ለገበያ ታቀርብ እንደነበረና በወላጆች ግን የሚመረጡት ከውጪ የሚመጡ አልባሳት መሆናቸውን ትገልፃለች። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የምታነሳው እዚህ የሚሠሩት አልባሳት ሰፊ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቁ መሆናቸውን ነው።
ዋጋቸው ከውጭ ከሚመጡት ይጨምራል ትላለች። ከውጭ የሚመጡት አልባሳት በዓይነትና በዋጋም ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሳ፣ በአገር ውስጥ በልዩ ዲዛይን ከሚዘጋጁ የልጆች አልባሳት ጋር በዋጋ መወዳደር እንደማይችል ታብራራለች።
አንደ ባለሙያዋ ገለጸ በአገር ውስጥ የሚመረቱት የሕፃናት አልባሳት የሚሠሩባቸው ጨርቆችም ለአዋቂ ካልሆነ በስተቀር ለሕፃናት የሚሆኑ አይደሉም። ይህ ደግሞ የአገር ውስጥ የሕፃናት አልበሳት አምራቾች ሕፃናት አልባሳት ላይ እንደ ባለሙያ ትኩረት አድርገው እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል ባይ ናት።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014