
ቻይና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትን የተቃወመችውን ሩሲያን እንደምትደግፍ አስታወቀች። ይህም የምዕራቡን ዓለም ግፊት ለመቋቋም በጋራ ለቆሙት አገራቱ ሌላ የአጋርነት ምልክት ሆኗቸዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የክረምት ኦሊምፒክን እያስተናገደች በምትገኘው ቻይና ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አገራቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ስምምነት የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥተዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን የምዕራቡ ዓለም አገራት የኔቶ ጥምረትን ጦር ሰበብ አርገው ሩሲያን ለማናጋት እየሞከሩ ነው ሲሉ ይከስሳሉ። ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ከዩክሬን ጋር ውጥረት በተፈጠረበት በዚህ ወቅት ሲሆን ዩክሬንን የመውረር ዕቅድ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች የቀድሞዋ የሶቪየት ግዛት በነበረችው በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ መስፍራቸው ከምዕራባውያን ጋር ያለው መቃቃርን አካሮታል። ሩሲያ እና ዩክሬን “አንድ አገር ናቸው” ብለው የሚያምኑት ፑቲን ዩክሬን ወደ የኔቶ አባል እንዳትሆን አበክረው እየጠየቁ ነው።
የፑቲንን የቤይጂንግ ጉብኝትን ተከትሎ የወጣው ረዥሙ የጋራ መግለጫ ዩክሬንን በቀጥታ ባይመለከትም አገራቱ ኔቶ የቀዝቃዛውን ጦርነት ርዕዮተ ዓለምን ያዘለ ነው ሲሉ ተችተዋል።
የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ምክክር ከክረምቱ ኦሊምፒክ መክፈቻ በፊት የተከወነ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ገጽ ለገጽ ሲገናኙ የትላንቱ የመጀመሪያቸው ነው።
መግለጫው “በሩሲያ እና በቻይና መካከል ያለው ወዳጅነት ገደብ የሌለው እና ‘የተከለከለ’ የሚባል የስምምነት መስክ የለም” ሲልም አክሏል።
ቻይናና ሩሲያ በተለያዩ የደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት አላቸው። ከዚህ ቀደም ሁለቱ አገራት በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደምና በአውስትራሊያ መካከል የተደረሰውና ‘አውኩስ’ የሚል ስያሜ ያለው ወታደራዊ ስምምነት “እጅግ ያሰጋናል” ብለው ነበር።
ከወራት በፊት ይፋ የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት አውስትራሊያ በእስያ ፓስፊክ አካባቢ ያለውን ደኅንነት ለማጠናከር በሚል በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን እየገነባች ነው።
ተግባሩ በደቡብ ቻይና ባሕር ባሉ አወዛጋቢ ግዛቶች ላይ ውጥረትን አንግሳለች በሚል የሚከሷትን ቻይና ለመመከት የተደረገ ጥረት ተደርጎ ተወስዷል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014