
ሞሮኮ ውስጥ ከቀናት በፊት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የገባውን የአምስት ዓመት ታዳጊን ለማትረፍ የነፍስ አድን ሠራተኞች የመጨረሻ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ታዳጊውን ከጥልቁ ጉድጓድ ለማውጣት የነፍስ አድን ሠራተኞች ቀን ከሌት እየጣሩ ይገኛሉ፡፡
32 ሜትር ወዳለው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ የገባውን ታዳጊ የራያንን ሕይወት ለማትረፍ የነፍስ አድን ሠራተኞች ቀን ከሌሊት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ታዳጊው ጉድጓድ ውስጥ መግባቱ ከተነገረ በኋላ በመላዋ ሞሮኮ ያለው ሕዝብ መልካም ዜና ለመስማት በጉጉት እየተጠባበቀ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከአደጋው ስፍራ ተስብስበው የነፍስ አድን ጥረቱን ውጤት እየተጠባበቁ ነው።
ታዳጊውን ከጥልቁ ጉድጓድ የማውጣቱ ጥረት ውስብስብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ይችላል የሚለው ስጋት ደግሞ ሥራውን የበለጠ አደገኛ አድርጎታል ተብሏል።
ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለማስወገድም ቡልዶዘሮች ታዳጊው ከገባበት ጉድጓድ አቅራቢያ ግዙፍ መተላለፊያ የቆፈሩ ሲሆን ባለሥልጣናት የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ታዳጊው እየተቃረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ታዳጊውን ከጥልቁ ጉድጓድ የማውጣቱ ጥረት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በሞሮኮ የአደጋ ጊዜ ተቋም ሠራተኞች አማካይነት ያለማቋረጥ ሲካሄድ መቆየቱ ተነግሯል።
አደጋው በደረሰበት ጊዜ የታዳጊው አባት በውሃ ጉድጓዱ ላይ የጥገና ሥራ እያከናወኑ ነበር። እናቱና ቤተሰቡ በሙሉ በከባድ ጭንቀት ውስጥ ሆነው የነፍስ አድን ሥራውን ውጤት እየተጠባበቁ ነው።
“ለቅጽበት ከሪያን ላይ አይኔን ዞር ሳደርግ ነው ወደ ጉድጓዱ የወደቀው። ከዚያች ጊዜ አንስቶ አስካሁን እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረም” ሲሉ አባት ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
ወደ ጉድጓዱ ውስጥ እንዲገባ ከተደረገ ካሜራ ላይ ሐሙስ ዕለት የተገኘ ምስል እንዳመለከተው ምንም እንኳን ታዳጊው ቀላል ጉዳት ቢደርስበትም በሕይወት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የኦክስጂን መተንፈሻ፣ ምግብና ውሃ በጉድጓዱ በኩል ለታዳጊው የላኩ ሲሆን ሄሊኮፕተርና የሕክምና ባለሙያዎችም በቦታው ሆነው በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ነው።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና ባለሙያዎች እንዳሉት ታዳጊው የገባበት ጉድጓድ ጥልቅ መሆንና መጥበብ የነፍስ አድን ጥረቱን አስቸጋሪ አድርጎታል። ባለፉት ቀናት ታዳጊው ወደ ወደቀበት የጉድጓዱ ክፍል ለመድረስ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ስኬታማ ሳይሆኑ መቅረታቸውም ተነግሯል።
በሰሜናዊ ሞሮኮ ቼፍቹዋን በሚባለው አካባቢ የደረሰው ይህ አደጋና የታዳጊውን ሕይወት ለማትረፍ ላለፉት አራት ቀናት ሲደረግ የሰነበተው ጥረት ከአገሪቱ አልፎ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል።
ባለሥልጣናት ተስፋ እንደሚያደርጉት ይህ የቀናት ጥረት ታዳጊውን ከጉድጓዱ በማውጣት መቋጫ ያገኛል በሚል ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014