“በዚህ በዛሬው ቀን በመዲናችን አዲስ አበባ በዚሁ የአፍሪካ ጉባዔ ላይ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁ የአፍሪካ አገር መሪዎች ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም ስንቀበላችሁ በጣም ደስ ይናል፡፡… ይህ ቀን ለአፍሪካውያን ታላቅ ቀን ነው”
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
የመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት) በአዲስ አበባ ሲመሰረት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩት ቀዳሚው የመሪዎች ንግግር ነው።ታሪክ 59 ዓመታት ወደ ኋላ ወስዶ በታሪክ አጋጣሚ የመጀመሪያውን የአፍሪካውያን ጥምረት ጉባኤ መነሻ እና ጉዞን እንዳስሳለን፤ ይህ ሳምንት መዲናችን 35ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እያስተናገደች ያለችበት መሆኑ በእዚህ ላይ ማተኮር ውስጥ የገባነው።
አፍሪካውያን በነፃነት እጦት ማቀቁ፣ የአህጉሪቱ አብዛኛው ክፍል በወራሪዎች ቅኝ ግዛት ስር ወደቀ።በእዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖር ይህን ሁኔታ መመልከት ያንገፈገፋቸው፣ ያኔ ስለ አገራቸው መብት የሚጠይቁ ጥቁሮች በተለያየ የአህጉሪቱ ክፍል ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።ነገር ግን ወራሪዎች ይህንን ይሰጉ ነበርና ጠንካራ በትራቸውን ነፃነቴን ባለ አፍሪካዊ ላይ ሁሉ አሳረፉ።
ወራሪዎቹ ለቅኝ ግዛት እጅ አልሰጥም ባለው ላይ ብርቱ ጥቃት ፈፀሙ።ሁኔታው ግን አፍሪካውያንን ለአፍታም አላቆማቸውም።ይልቁኑም የኢትዮጵያን የነጻነት ተምሳሌትነት አንግበው ለነፃነት መታገላቸውን አፋፋሙት።በዚህም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት በ1960ዎቹ ነፃነታቸውን መጎናፀፍ ቻሉ።ይህ በሆነ ማግስት አፍሪካውያን ይበልጥ ነፃነታቸውን ለማረጋገጥና የመጣባቸውን የጋራ ጠላት አብረው ለመመከት የአንድነት ቃል ኪዳን ሊገቡ አዲስ አበባ ላይ ተሰባሰቡ።
ወቅቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግንቦት 4 ቀን 1955 ላይ ወደ ኋላ ይመለሳል።ብዙ ክፍፍልና የአቋም መለያየት ውስጥ የነበሩት አፍሪካውያን ኢትዮጵያና ጥቂት የአፍሪካ አገራት ባደረጉት ጥረት ወደ አንድነት ተቃርበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት በቁ፡፡
ለተሰበሰቡ የጥቁር ሕዝብ መሪዎች የመጀመሪያው የጋራ ስብሰባ ላይ ከፊት ሆነው የአንድነት ጉባኤው እንዲካሄድና አፍሪካውያን በጋራ ለነፃነታቸው ትግል ይቆሙ ዘንድ ብርቱ ትግል ያደረጉት የጋናው ኩዋሚ ኑኩሩማ ፤-“ዛሬውኑ አንድ ካልሆንን እንጠፋለን… የኢኮኖሚ ነጻነታችን የሚረጋገጠው በአንድነታችን ነው” ሲሉ የአፍሪካውያን አብሮ መቆም አስፈላጊነትና ወሳኝነት ለጉባኤተኛው አስረዱ።በአንድ ሀሳብና በአንድ ድርጅት መሪነት በጋራ ስለራሳቸው ሊመክሩ አብረው ሊሰሩ ቃል ተገባቡ።
አፍሪካን አንድ በማድረጉ ጥረት ጅማሮ ላይ ስለ አፍሪካ ነፃነትና ሉዓላዊ ክብር የቆሙ ሁለት ቡድኖች ነገር ግን፤ የየራሳቸው ሀሳብና ግብ ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች ተመሰረቱ።እነዚህም የካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ቡድኖች በመባል ይታወቃሉ።እነዚህ ቡድኖችም አፍሪካውያን በፖለቲካና በኢኮኖሚ ራሳቸውን መቻል፣ በኮንፌዴሬሽን አንድ መሆን አለባቸው የሚለው የካዛብላንካ ቡድንና አፍሪካውያን በራሳቸው ለመቆም ኢኮኖሚያቸውን ለማደራጀትና ጠንካራ ይሆኑ ዘንድ በሌሎች አህጉራትና አገራት መደገፍ አለባቸው የሚለውን ሀሳብ ያቀፈው የሞኖሮቪያ ቡድን ናቸው::
ከመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ በፊት በ1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሁለቱም ቡድኖች እንድትካፈል ጥያቄ ቢቀርብላትም የአቋማቸው መነጣጠልንና የተለያየ ቡድን መፈጠሩን ፈፅሞ ባትደግፈውም በጊዜያዊነት በካዛብላካ ቡድን ስብሰባ ላይ ተካፍላለች:: ስብሰባውም ናይጄሪያ ሌጎስ ላይ ነበር የተደረገው:: በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ተወካይ ቀጣይ ስብሰባው አዲስ አበባ እንዲሆን ግብዣ አቀረቡ::
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጥቅም ለማረጋገጥ ብለው የቆሙት የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን አንድ በማድረግ ለአፍሪካ ነፃነትና ለሕዝቧ ኑሮ መሻሻል ይተጉ ዘንድ ጥሪ አቀረበች:: በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች በኢትዮጵያ ተገኝተው ስለአፍሪካ አንድነትና አብሮነት እንዲመክሩ ብዙ ማግባባቶችን አደረገች፡፡
አፍሪካውያን አዲስ አበባ ላይ እንዲሰበሰቡ ብዙ ሥራዎች ተሠሩና ለሁሉም መሪዎች ጥሪ ቀረበ፤ በዚህም 32 የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ተወካዮች ተሰበሰቡ።አዲስ አበባ ያኔ ልክ እንደ ዛሬው አፍሪካውያንን ለመቀበልና ኢትዮጵያን የአገራቸው ያህል እንዲቆጥሯት ለማድረግ በተለያየ መልኩ ጥሩ መስተንግዶ ስታቀርብም ቆየች።ስብሰባውም የተካሄደው ዛሬ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተብሎ በሚጠራው የቀድሞው ሕንጻ/ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ በመባል ይታወቃል/ ነበር።
ከመሪዎቹ ስብሰባ ቀደም ብለው አዲስ አበባ ላይ የተገኙት የአፍሪካ አገራት ተወካዮች የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ አፍሪካ ቡድኖች መተዳደሪያን ውድቅ በማድረግ አንድ ተቋም መመሥረት የሚያስችለውን አጀንዳ በመቅረፅ ምቹ ሁኔታን ፈጠሩ።መሪዎቹም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መከሩ:: በመጨረሻም ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች የአንድነት መተዳደሪያ በአራት ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በፈረንሳይና በእንግሊዘኛ ተዘጋጀ ፤ ቻርተር ላይ ተፈራረሙ::
ድርጅቱ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ተሰብስቦ እየመከረ ስለ አፍሪካውያን እያወጋና ጉዳዮችን መርምሮ ለውሳኔ እያቀረበ ለጥቁሮች መብት ብዙ ታገለ።የቀሩት የአፍሪካ አገራት ነፃ እንዲወጡና ጠንካራ ሆነው እንዲቆሙ ብዙ ጣረ።ከመላው ዓለም ጋር በመሆንም ስለ አፍሪካውያን መብት መከበር ብዙ ሠራ።
አፍሪካውያን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ብለው ያዋቀሩት ከ50 ዓመታት በላይ ስለ አፍሪካውያን የተሟገተውና የሠራው ተቋም ለአፍሪካውያን በሚፈልጉት መልኩ ድል ሊያስገኝላቸው አልቻለም:: ድርጅቱም ሲጀምር ያሰበውን ማሳካት እየተሳነው መጣ:: ለአህጉሪቱ ሰላምና ብልፅግና ማስመዝገብም አቃተው።ይባስ ብሎ አፍሪካውያን እርስ በርስ መጋጨትና አንዱ ካንዱ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባትን ያዘወትሩ ጀመር:: የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም እያደር የማስፈፀም አቅሙ እየተዳከመ ሄደ፡፡ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል ሀብት ውስንነትም ነበረበት፡፡
በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መተዳደሪያ ቻርተር ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአገራት ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ አይገባም በሚል ያሰፈረው አንቀፅ አገራቱ በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባራት እንዲፈፅሙና አንድነት ድርጅቱ የማስፈፀም አቅም እንዳይኖረው አደረገ:: በዚህም ድርጅቱ አቅም እያጣና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ሄደ፡፡
በዚህም የአፍሪካ አገራት ለአፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት፣ እንደ አዲስ የጋራ ተቋም ለማቋቋምና የተሻለ ለመሥራት አቀዱ።ይህ ነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት የመለወጥ ምክንያት ሆነ፡፡
በ1995 ዓ.ም የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተካው የአፍሪካ ኅብረት በደቡብ አፍሪካ ደርባን ተመሰረተ።በዚህ ወቅት ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በአዲስ መልክ አፍሪካን አጠንክረው አብረው ሊሠሩ በማለም 53 የአፍሪካ አገራት በአባልነት ተመዘገቡ።የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ መልክ ተጠናክሮና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተሰኝቶ በአባል አገሮች ጉዳዮች ላይ የመወሰን አቅሙን አሳድጎ ሥራ ጀመረ፡፡
ኅብረቱ ሰነዶቹን ፈትሾና ራሱን አጠንክሮ ግጭቶችን ለማስቀረት እንዲሁም ሲከሰቱም በመፍታት አስፈላጊ ሲሆንም ሰላም አስከባሪ ኃይል በአህጉሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በመላክ ሥራውን አጠናከረ:: በአህጉሪቱ ውስጥ ስልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የሚቆናጠጡትን በማውገዝና እውቅና ባለመስጠት ለዲሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት የራሱን ሚና በመወጣት ላይም ይገኛል።ነገር ግን አፍሪካ እጅግ የሰፋ የፖለቲካ ችግር፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ማኅበራዊ ምስቅልቅል የሚስተዋልባት አህጉር መሆንዋ ቀጠለ።ይህም ኅብረቱ ዛሬም ድረስ ዓላማውን ማሳካት እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል፡፡
አህጉሪቱ ዛሬ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ፈተናዋ ሆኗል።በሞግዚት መልክ የሚያስተዳድሩ ምዕራባውያን እንዳሉም ይታወቃል፤ እናም ከእዚህ ሁሉ ጫና እንድትላቀቅ፣ በራስዋ ጉዳይ መወሰን እንድትችል ኅብረቱም አባል አገራቱም በኅብረት እንዲቆሙ የአፍሪካውያን ምኞት ነው።ለዚህም አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለአፍሪካ ድምፅ መከበርና እውናዊ ነፃነት መረጋገጥ የሚያሰሙት የተናጠል ጥረት ተጠናክሮ እየወጣ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው፡፡
ትናንት በተጀመረው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤም አፍሪካውያን መሪዎች ልክ እንደ ቀደምቶቹ የአፍሪካ መሪዎች ስለ አፍሪካ በነፃነት የሚመክሩበትና ውሳኔ የሚያሳልፉበት እንደሚሆን አፍሪካውያን ይጠብቃሉ።
አፍሪካ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እየተፈተነች ናት።ምዕራባውያን በአፍሪካ ሀገሮች ላይ በትንሹም በትልቁም ጫናና ማዕቀብ ይጥሉባቸዋል፤ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዳይወስኑ እያረጓቸው ነው።ከዚህ አልፈውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባላቸው ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን በመጠቀም በምክር ቤቱ ምንም ድምጽ በሌላት አፍሪካ ላይ ያሻቸውን ውሳኔ እያሳለፉ ናቸው።አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በዚህ ምክር ቤት ድምጿ እንዲሰማ መሥራት የዚህ ዘመን የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ኃላፊነት ነው።የወቅቱ የአፍሪካውያን ፍላጎትም ይሄው ነው።
አፍሪካውያን ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በምዕራባውያን የሚደርስባቸውን ጫና ላለመቀበልና የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን አለባቸው።የ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳታፊ መሪዎችም ይህን የኢትዮጵያን በቃ/ ኖ ሞር/ ዘመቻ መቀላቀል የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ ላይ መሆናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ ዘመቻውን በማድነቅ እልፍ ሲልም በመቀላቀል ከዘመቻው አቀንቃኝ ኢትዮጵያ ጎን በመቆም ምዕራባውያን ከጣልቃ ገብነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እጃቸውን እንዲሰበስቡ በቃ ማለት ይጠበቅባቸዋል። ዘገባውን ስናዘጋጅ የአፍሪካ ኅብረት ድረ ገጽን፣ በኅብረቱ ምስረታ ወቅት የወጡ ዜናዎችና መጣጥፎችን በመረጃነት ተገልግለናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014