የጥበቡን ዓለም የተቀላቀለው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር በሕይወት ማህደሩ የሰፈረው ማስረጃ ይናገራል። የኢትዮጵያ የዘመናዊ ቴአትር መድረክ ፈርጥ፤ ጌታቸው ደባልቄ። የከርሞ ሰው፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ ቴዎድሮስ፣ ሃኒባል፣ በልግ፣ ሥነ ስቅለት፣ ኦቴሎ እና በበርካታ የኢትዮጵያ ታሪካዊና አይረሴ ቴአትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት ይታወቃል።
ይህ ኢትዮጵያዊው የቴአትር ሰው የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲም ነበረ። እነምኒልክ ወስናቸው፣ መሐሙድ አህመድ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ግርማ ነጋሽ፣ ጠለላ ከበደ፣ አስናቀች ወርቁ የሠሯቸውን ሥራዎች ተጫውቷል። ከ50 ያላነሱ የሙዚቃ ግጥሞችን አበርክቷል። 10 ያህል የተውኔት ድርሰቶችንም ለመድረክ አብቅቷል።
የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ታሪካዊ የቴአትር ሥራዎች የነገሠባቸው ነበሩ። የኢትዮጵያን የጥበብና የኪነ ጠበብ ታሪኮችን በማወቅና በመድብል መልክ በማሳተምም ጉልህ ሚናውን ተወጥቷል። እኛም ዛሬ ይህንን ታላቅ የጥበብ ሰው በ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› አምዳችን ልንዘክረው እና የሕይወት ጉዞውን ልናወሳ ወደናል፤ መልካም ንባብ!
ከአዲስ ዓለም እስከ አዲስ አበባ
በድሮው ሸዋ ክፍለሀገር መናገሻ ወረዳ አዲስዓለም ከተማ ልዩ ስሙ ነጋዴ ሰፈር በሚባል አካባቢ ነው፤ የጥበቡ ፈርጥ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የተገኘው። ከወላጅ እናቱ ወይዘሮ አሰገደች ወልደገብርኤል እና ከአባቱ አቶ ደባልቄ አምበርብር ሚያዝያ 20 ቀን 1928 ዓ.ም ተወለደ።
እድሜው አራት ዓመት እንደሞላ የኔታ ፀጋዬ ተክለወልድ የተባሉ እውቅ የአማርኛና ግእዝ መምህር ጋር በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፊደል ቆጠረ። በዚህ ፍጥነቱም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ዳዊት ለመድገም የበቃ ሲሆን፣ አከታትሎም ወደ ድጓ እና ጾመ ድጓ ተሸጋግሯል። በዚህ ወቅት አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ። ትምህርት ላይ ፅኑ ተስፋም አቋምም የነበራቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ «ልጁን ያላስተማረ እንደገደለው ይቆጠራል!» ብለው እንደ አዋጅ አስነገሩ።
በዚህ ጊዜ አዲስዓለም የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ተገደዱ። አምስት መቶ የሚሆኑ ልጆች አፄ ምኒሊክ ለግብር ብለው ባሰናዱት አዳራሽ ትምህርታቸውን ሲጀ ምሩ ከእነዚህ መሀል ጌታቸው ደባልቄ አንዱ ነበር። በኋላም ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ትምህርት ቤት በተቀየረው የግብር አዳራሽ የተገኙትን ተማሪዎች ብዛት ተመልክተው አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ትእዛዝ አስተላለፉ። በዚህም ምክንያት አዲስ ዓለም ተብሎ በተሰየመው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እስከ 6ኛ ክፍል ተማረ።
አርቲስት ጌታቸው ትምህርቱን እየተማረ በነበረባቸው ዓመታት ትምህርት ቤቱ ያዘጋጃቸው በነበሩ መዝሙሮች በዘማሪነት ንቁ ተሳትፎ የነበረው ከመሆኑም በላይ በትምህርት ቤቱ የወላጆች ቀን በተከበረ እለት የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር በነበሩት በአቶ ቀነአ ተጽፎ በተዘጋጀው የአርበኞች ታሪክ ተውኔት ላይ ተዋናይ ሆኖ ተጫውቷል። ንጉሠ ነገሥቱ ከአምቦ ተመልሰው አዲስ ዓለም የማርያም በዓልን ለማክበር በመጡበት ጊዜ፤ ጌታቸው ንጉሡ ፊት ራሱ የጻፈውን ግጥም አንብቦ የሦስት ሽልንግ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
በልጅነት በትምህርቱም ብርቱና ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቆይታው የውጤት ደረጃ ከአንደኛ እና ሁለተኛ ዝቅ አይልም። ይሁንና ጌታቸው ይኖ ርበት በነበረው ከተማ ይሰጥ የነበረው ትምህርት ከመጀመሪያ ደረጃ የዘለለ አልነበረምና፤ ስድስተኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላ ለአንድ ዓመት ጊዜውን ትምህርት ሳያገኝ አሳልፏል።
ለትምህርት የነበረው ጉጉት ከፍተኛ ስለነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል አዲስ አበባ አጎቱ ጋር አቀና። በዛም መጀመሪያ አዳሪ ተማሪ ቤት እንዲማር ተሞከረ፤ ነገር ግን ሳይሳካ በመቅረቱ ኮከበ ፅባሕ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ጀመረ። በኮከበ ጽባሕ አንድ የትምህርት መንፈቅ ዓመት ካጠናቀቀ በኋላ ጊዮርጊስ አደባባይ ላይ ታዳጊው ጌታቸው የማዘጋጃ ቤት ሙዚቀኞች ዩኒፎርማቸውን ገጭ አድርገው ህብረ ዜማዎችን ሲጫወቱ ተመልክቶ ልቡ ክፉኛ ተሳበ። ጊዜ አላጠፋም፤ መጋቢት 20 ቀን 1944 ዓ.ም የሙዚቃና የቴአትር ፈተና ወስዶ ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ማዘጋጃ ቤት ለመቀጠር በቃ።
በጥበብ እልፍኝ
የጌታቸው የጥበብ ሕይወት ጉዞ የመጀ መሪያው ምዕራፍ እንግዲህ ይሄኔ ነበር የተከፈተው። የማዘጋጃ ቤቱን የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለሦስት ወራት ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ ሁሉም የሙዚቃና ቴአትር ቡድን አባላት ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት በአዳሪነት ገብተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደረገ። ያኔ ጌታቸው ደባልቄም ወደዛ ከገቡት መካከል አንዱ ሆነ።
ጊዜ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ለሙ ዚቃና ቴአትር ትኩረት የተሰጠበት፤ ብሔራዊ የሀገር ፍቅርን እና ጀግንነት ስሜትን ለማጠናከርና ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ቁምነገሮችን እያዝናኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ ያላቸውን ጉልበት ታውቆ የታመነበት ነበር። በዛም እምነት ለዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ምስረታ እንደጥንስስ የሚቆጠረውን የሙዚቃና የቴአትር ቡድንን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስር በ1943 ዓ.ም ተደራጅቶ ነበር።
እንግዲህ ይህ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስር የተቋቋመው የሙዚቃና ቴአትር ቡድን ነበር የጌታቸው ደባልቄን ልብ አሸፍቶ ከኮከበ ፅባሕ ትምህርት ቤት ያስወጣው እናም የብዙ ዘመን የሙያ አጋር ከሆኑት አርቲስቶች ጋር የቀላቀለው። በዚህ ጊዜ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ እድሜው ገና 14 ዓመት ነበር።
አርቲስት ጌታቸው በዚሁ የሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን በመታቀፉ ከአንጋፎቹ የጥበብ ሰዎች ጋር መገናኘት፣ አብሮ ለመሥራትና ልምድ ለመቅሰም ችሏል። እንደባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ እና አፈወርቅ አዳፍሬ ከመሳሰሉ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ እንደ አባት ከሚታዩ ስመጥር እና ድንቅ የጥበብ ሰዎች ጋር እንዲሠራ እድል ያገኘው በዚህ ቡድን ምክንያት ነበር። በኋላም የሀገሪቱ እድገትና የከተማው እንቅ ስቃሴ ከፍ እያለ በመሄዱና የኪነጥበብ ሚናም እየተስፋፋ መጣ።
ታዲያ በአዲስ አበባ ውስጥ አንድ ዘመናዊ ቴአትር ማቋቋም አስፈላጊነቱ ታምኖበት በ1948 ዓ.ም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር፤ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተመሰረተ። በምስረታውም ለቴአትር ቤቱ የመጀመሪያ ዳይሬክተር የሆነው ኦስትሪያዊው ፍራንስ ዞልቬከር በሙዚቃና ቴአትር ዘርፍ ካሠለጠናቸው የቴአትር ቤቱ መስራች ባለሙያዎች መካከል አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ አንዱ ነበር። አርቲስት ጌታቸው በዚህ ጊዜ እድሜው 19 ዓመት ብቻ ነበር።
ለቴአትር ቤቱ የመጀመሪያ በሆነውና በወቅቱ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ተደርሶ በፍራንስ ዞልቬከር ተዘጋጅቶ በቴአትር ቤቱ ምረቃ እለት መክፈቻ ሆኖ በቀረበው ዳዊትና ኦሪዮን በተባለው ተውኔት አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የመጀመሪው ተዋንያን ከነበሩት መካከል አንዱ ነው። በቴአትር ቤቱ ከዚህ በኋላ በተዘጋጁ ተውኔቶች አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ከተጫወተባቸው ይልቅ ያልተሳተፈባቸውን መቁጠር ይቀላል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ከእነዚህ መሀል በየሰው ልብ ውስጥ ትዝታ ሆኖ እንዲኖሩ ካደረጉት ተውኔቶች ጥቂቶቹን ብቻ ለማንሳት ያህል፤ የቢትወደድ መኮንን «ዳዊትና ኦሪዮን»፣ የፍራንስ ዞልቬከር «ሥነ ስቅለት» ወይም «ወደ ክብር ጎዳና»፤ የከበደ ሚካኤል «አኒባል»፤ የግርማቸው ተክለ ሐዋርያት «ቴዎድሮስ»፣ የኬርቮክ ናልባንዲያን “ ጎንደሬው ገ/ማርያም” የሞልዬር «የፌዝ ዶክተር»፣ የጸጋዬ ገ/መድህን «የከርሞ ሰው»፣ የጎጎል «ዋናው ተቆጣጣሪ»፣ የአያልነህ ሙላት «ሻጥር በየፈርጁ»፣ የሻምበል ፈቃደ ዮሐንስ «ርጉም ሐዋሪያ» እንዲሁም ቀደም ሲል በማዘጋጃ ቤቱ የሙዚቃና ቴአትር ቡድን ውስጥ አባል በነበሩበት ጊዜ «ድንገተኛ ጥሪ»፣ «የእድሜ ልክ እስራት» እና «የፍቅር ጮራ» የተሰኙትን ተውኔቶች ጨምሮ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ከተጫወተባቸው 52 ተውኔቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በነገራችን ላይ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የመጀመሪያው የሆነውን «በድሉ ዘለቀ» የተሰ ኘውን የተውኔት ድርሰቱን ያበረከተው በ1946 ዓ.ም በአዲስ አባበ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃና የቴአትር ቡድን ውስጥ ይሠራ በነበረበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ እድሜው 17 ዓመት ነበር። ብሩህ አዕምሮን የታደለው አርቲስት ጌታ ቸው ደባልቄ ቴአትሮች ላይ ተዋናይ ሆኖ ከመጫወት ባሻገር በለጋ እድሜው አስቸጋሪውን እና ትእግስት የሚፈልገውን የተውኔት ድርሰት ተጋፍጦ በኋላም ይህንኑ አጠናክሮ ገፍቶበት በ1953፣ በ1954 እና በ1962 ዓ.ም «ከተፎና መንጥር»፣ «ያስቀመጡት ወንደላጤ» እና «ደኅና ሁኚ አራዳ» የተባሉ ተውኔቶችን ለአገሩ ቴአትር አፍቃሪዎች አበርክቷል።
አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ለአገሩ ቴአትር እድገት ያበረከታቸው የተውኔት ድርሰቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሌሎች እጅግ በርካታ አጫጭር ተውኔቶች እና በሀገር ፍቅር ቴአትርም ለህዝብ የቀረቡ ድርሰቶች እንካችሁ ብሏል። የአርቲስቱ ተውኔት አበርክቶ በዚህ ብቻ አያበቃም። በሙያ ዘመኑ 15 ያህል ተውኔቶችን አዘጋጅቷል። ከእነዚህም በርካታ የዝግጅት ሥራ ዎች መካከል የራሱ ድርሰት የሆነው «ደኅና ሁኚ አራዳ»፣ መክብብ ጌታቸው የተባሉ ሰው የተረጎሙት የሞልየር «የከተማው ባላገር»፣ የግርማ ዘውዴ «ለሰው ሞት አነሰው»፣ የደስታ ገብሩ «ምኞቴ»፣ የመሪ ጌታ አእምሮ ፈረደ «ፍቅር መጨረሻ» እና የማሞ ውድነህ «አሉላ አባነጋ» ከብዙ በጥቂቱ ይገኙባቸዋል። በቴአትር ሙያ ላይ ሁለገብ ተሳትፎ የነበረው ጌታቸው ደባልቄ በሌሎችም የኪነጥበብ ዘርፎችም ንቁ ተሳትፎ ነበረው።
በግጥምና ዜማ ድርሰትም ተሰጥኦው ስለነበረው ዛሬም ትውልድን መሻገር የቻሉ ሥራዎቹን ትቶልን አልፏል። ከነዚህ መሀል ጥቂቱን እንጠቅሳለን። አርቲስት ጠለላ ከበደ ታቀነቅነው የነበረና በግጥሙ ይዘት ለእስር የተዳረጉበት «ሎሚ ተራ-ተራ» ተከታታይ ትውልዶች እያቀነቀኑት እንሰማለን። ከዛም በተጨማሪ «አደረች አራዳ፣ የኔ ሀሳብ፣ ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ» አይረሴ ከሆኑት መካከል ይገኙበታል። አርቲስት ጌታቸው አቅሙ በፈቀደ መጠን ማስታወሻውን ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር የሚጥር ታላቅ ሰው ነበር። እስር ቤት በቆየባቸው ጊዜያት የገጠመውን እና የታዘበውን «ደንቆሮ በር» በሚል ርእስ መጽሐፍ ጽፎ ለህትመት ያበቃ ሲሆን፣ የአርቲስት አስናቀች ወርቁን የህይወት ታሪክም እንዲሁ ለትውልድ አስተላልፏል።
የሕይወት ገጽታ በእስር ቤት
የአርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ሕይወት አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሎሚ ተራ ተራ በተሰኘው የዘፈን ግጥሙ ሳቢያ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ እና ልዩ ቅርንጫፍ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት አራት ወር ከሃያ ቀን ታስሯል። የቴአትር ቤት ሞያተኞች ለመብታቸው በጮሁበት ጊዜ አብረው ጮኸው ለአምስት ወራት ያህል በታላቁ ቤተመንግስት፤ በማይጨው ጦር ሰፈር እና አራተኛ ክፍለጦር ታስሯል። እንዲሁም በ1969ዓ.ም በወቅቱ ለነበረ አንድ ፓርቲ አባል ሆነህ ወረቀት አንብበሃል በሚል ክስ ቤርሙዳ፤ ማእከላዊ ምርመራ እና ዓለም በቃኝ በተባሉ እስር ቤቶች ለከባድ ስቃይ ተዳርጓል።
የሚገርመው ታዲያ በእነዚህ ማረሚያና እስር ቤቶች በእስር በቆየበት ጊዜ ተስፋ መቁረጥም ሆነ ሌላ የመዳከም መንፈስ አልታየበትም። ይልቁንም ተውኔቶችን ለእስረኞች አስጠንቶ ቴአትር ያቀርብ ነበር። ደግሞም ጌታቸው ደባልቄ የኪነጥበብ ሰው ብቻ አልነበረም። ብዙውን እድሜውን በተዋ ናይነት ባሳለፈበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትር ክፍል ኃላፊ፤ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል። ከዛም በላይ በተለያዩ ጊዜአት የቴአትር ቡድኖችን በመምራት መላው ኢትዮጵያ ላይ ተዘዋውሯል።
ጌታቸው ለሙያው ላሳየው ክብርና መሰጠት በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ምስጋናና ሽልማቶችን ተቀብሏል። ገና በጮርቃ እድሜው ትውልድ ከተማው በነበረበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርቦ ባቀረበው ግጥም ሦስት ሽልንግ መሸለሙ የሚታወስ ሆኖ፤ በሙያ ካደገና ከጎለመሰ በኋላ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በድጋሚ ገንዘብና ወርቅ ተሸልሟል። በ1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን በቴአትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል።
ከሚወዷቸው አንደበት
አርቲስት ጌታቸው በእስር እና በህመም ምክንያት አልጋ ላይ ከዋለባቸው ጊዜአት በቀር ብሔራዊ ቴአትር በየእለቱ ከመምጣት የሚያግደው ምንም ምክንያት አልነበረም፤ ዛሬ ያ እግር ተይ ዟል። የቴአትር ቤት ባለሙያዎች በአንድ ቃል «ተንቀሳቃሽ ቤተመዘክር» የሚሏቸው አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ፤ በስጋ ከማይንቀሳቀሱበት ዓለም ሄደዋል። ለሙያው የነበራቸው ፍቅርና ክብር፤ ችሎታቸውና ያሳዩት መሰጠት ሁሉ ግን ላይረሳ በጥበብ ዓለም መዝገብ ላይ ሰፍሯል።
የአርቲስቱ የሙያ ባልደረባ የሆኑት የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቅ አለ ማው ሲናገሩ፤ ጌታቸው ደባልቄ ከተስፋ ኮከብ አዳሪ ትምህርት ቤት ጀምሮ አብረዋቸው የኖሩ አብሮ አደጋቸው እንዲሁም የረጅም ጊዜም ጓደኛማቾች እንደነበሩ ያወሳሉ። «እጅግ የበዛ ክህሎት ያለው ታታሪ እንዲሁም ለሙያው እና ለሙያው ባልደረቦቹ ያለው ጥልቅ ፍቅርም ክብ ርም ለብዙዎቻችን አርዓያ የሚሆን የጥበብ ሰው ነበር።» ሲሉም ጌታቸውን ይገልጻሉ።
ሌላኛው የአርቲስቱ ወዳጅ ሙዚቀኛ መርዓዊ ስጦት ሲናገር፤ ጌታቸውን የማውቀው ማዘጋጃ ቤት በነበርንበት ወቅት ማለትም ከ1946 ጀምሮ ነው ይላል። እርሱ በወቅቱ ሙዚቃ ክፍል ተመድቦ ሲገባ ጌታቸውም እዚው ክፍል ሙዚቃ ይጫወት ነበር። እንደ ድምጻዊ ገለጻ አርቲስት ጌታቸው ጤናማ የሥራ እና የወዳጅነት ግንኙነት መፍጠር የሚችል ባለሙያ ነበር። «ጋሼ ጌታቸው የብሔራዊ ቴአትር እና የኪ ነጥበብ ህያው መዘክር ነበር።» ያሉት ደግሞ ክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ናቸው።
ከጌታቸው የተማሩት እጅግ ብዙ የጥበብ ክህሎት መኖሩንም አንስተዋል። «ብሔራዊ ቴአትር ሦስት መለያዎች አሉት ዋርካው፣ አንበሳውና ጋሽ ጌታቸው። ብሔራዊ ቴአትር ዛሬ አንድ መለያውን አጥቷል» ያለው አርቲስት ተስፋዬ ገ/ሃና ሲሆን አርቲስት ጌታቸው ወረቀት ሳይዝ፣ ሰነድ ሳያገላብጥ የተለያዩ ሁነቶችን ጊዜ፣ ቦታ፣ ቀንና ዓመተ ምህረት ሳያዛባ በቃሉ የሚያውቅና የሚያስታውስ ህያው መዝገብ ነበር ብሏል።
አርቲስት ጌታቸውን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና መምህራን፤ በሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የታሪክ ተመራማሪዎች፤ በጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅና ተፈላጊ ያደረገው ስለሀገሩ ሥነ ጥበብ ታሪክ ቋሚ መዝገብ ስለነበረ ነው። ይህ ታላቅ ሰብአዊ መዝገብ ዛሬ ተለይቶልናል። ሥራው ግን ህያው ሆኖ ለትውልድ ይሸጋገራል። አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የሁለት ሴት ልጆች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበረ። ለቤተሰቦቹ፣ ለመላው አድናቂዎቹ እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች መጽናናትን እንመኛለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
አብርሃም ተወልደ