ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ መንግሥት የገጠርና የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብሮችን ዘርግቶ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ጸጋ ተጠቅመው ኢኮኖሚ እያመነጩ ኑሯቸውን በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
መርሃግብሩ ተግባራዊ መሆን ከጀምረ ወዲህ በርካታ ወጣቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ባለሃብትነት ተሸጋግረዋል። ከሰሞኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከክልሎች ጋር የጋራ ግምገማ አድርጓል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት በበጀት ዓመቱ የስድስት ወር የክልሎች የሥራ እድል ፈጠራ ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር አርባ ሶስት በመቶ የቀነሰ መሆኑን ገልጿል።
ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ እንደምክንያት ቢጠቀስም ውጤቱ በሥራ እድል ፈጠራ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከክልሎች ጋር የተደረገውን የጋራ ግምገማ አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንደ አዲስ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ተከታታይነት ያላቸው የምክክር መድረኮችን ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በማካሄድ ዘርፉ በርካታ የለውጥ ሃሳቦች ማራማድ የሚያስችሉ ሂደቶችን ማለፉን ገልጸዋል።
እንደ አገር ኢኮኖሚው ከሚፈልገው ሽግግር አንጻር ተፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በክህሎት፣ በሥራ እድል ፈጠራና በኢንዱስትሪ ዘርፎች መሥራት እንደሚያስፈልግ በስፋት ሲጠና መቆየቱን ተናግረዋል።
የቀረበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ መቀጠል መሻሻል የሚገባቸውንም ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮችን በተጨባጭ ለመመልከት ምክክሩ እየተካሄደባት በነበረችው ሀዋሳ ከተማ በሥራ እድል ፈጠራ የተሰማሩ ወጣቶችን እንቅስቃሴ ለመቃኘት ሞክሯል።
አቶ ሀደራ ሀርቃ በአዋሳ ከተማ አስተዳዳር ሥራ እድል ፈጠራ ምክትል መምሪያ ኃላፊና የገጠር ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።
እርሳቸው እንደገለጹት እንደሀዋሳ ከተማ አስተዳዳር የሥራ እድል ፈጠራ በሶስት ዘርፍ የተዋቀረ ነው።ማኑፋክቸሪንግ፣ የከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና የገጠር ሥራ እድል ፈጠራ ናቸው።
ከጥቃቅን እና አነስተኛ ደረጃ ተነስተው መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ከፍተኛ፣ ከከፍተኛ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ የደረሱ መኖራቸውን ገልጸዋል።
በዘርፉ የከተማ አስተዳደሩን ሚና ሲገልጹ በሥራ እድል ፈጠራ አስተዳደሩ ለሥራው ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ይለያል፤ የክህሎት ስልጠና ይሠጣል፤ ያደራጃል፤ ብድር ያመቻቻል፤ ለሥራ ምቹ የሆነ ቦታ ይሰጣል፤ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፤ በመጨረሻም የገበያ ትስስር ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሥራ እድል ፈጠራ የተሰማሩ ወጣቶችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አቅርቧል። ወጣት ፍፁም ዮሃንስ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ታቦር ክፍለከተማ ፋራ ቀበሌ የአዶ ዶሮ እርባታ ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ነው።ማህበሩ ስድስት አባላት ያሉት ሲሆን የተመሰረተው በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ነው።
አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው ብድር 150 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዘው ሥራ እንደጀመሩ ወጣት ፍጹም ይገልጻል። በ2014 ዓ.ም መስከረም ወር ማህበሩ የመጀመሪያ ሥራውን ሲጀምር የአንድ ቀን እድሜ ያላቸውን በርካታ ጫጩቶች በመግዛት አሳድጎ መሸጥን ግቡ አድርጎ ነበር።
በዚሁ መሰረት ጫጩቶቹ ተቀልበው ከአርባ አምስት ቀን በኋላ አካላቸው ሲዳብር አንዷን ጫጩት መቶ ሀምሳ ብር ሂሳብ በመሸጥ አበረታች ጥቅም ማግኘታቸውን ይናገራል።
በሁለተኛው ዙር እጃቸው ላይ የነበረውን ገንዘብ አሰባስበው ስድስት መቶ ሰባ የሚሆኑ የእንቁላል ዶሮዎችን ገዝተው የእንቁላል ምርት ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳዳጉ መሄዳቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ ገልጾልናል።
አስተዳደሩ በዶሮ እርባታ ዘርፍ የሰባት ቀን ስልጠና ከሰጣቸው በኋላ የሥራ ቦታና ብድር አመቻችቶላቸዋል።የዶሮ መኖ እንዲያገኙም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አስተሳስሯቸዋል።
በገበያ ትስስር እስከ አሁን በአስተዳደሩ የተደረገላቸው ድጋፍ ባይኖርም ከአሳና እንስሳት እርባታ ቢሮ ጋር በቀጣይ በሚዘጋጁ የንግድ ባዛሮች አማካኝነት የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጾልናል።
በቀን አምስት መቶ ሰላሳ እንቁላል እንደሚያገኙና ይህንንም ለተለያዩ ሆቴሎች እያስረከቡ እንዳሉ ነግሮናል።ወደፊት ሁሉም ዶሮች መውለድ ሲጀምሩ በቀን የሚያገኙት የእንቁላል መጠን ስለሚጨምር በዚያው ልክ የገበያ ትስስር መፍጠር ስለሚያስፈልግ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቅሷል።
በአሁኑ ሰዓት ካፒታላቸው እያደገ መሆኑን የተናገረው የማህበሩ ሰብሳቢ ሁለት ጊዜ ከተበደሩት ገንዘብ ግማሽ ያህሉን መመለሳቸውን ተናግሯል።
በቀጣይ አስተዳደሩ የማስፋፊያ ቦታ ቢሰጣቸው የራሳቸውን የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ የመሥራት ህልም አላቸው። አንድ ቁምጣ የዶሮ መኖ አስከ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ብር እየገዙ የሚጠቀሙ መሆኑን የተናገረው ወጣቱ ማቀነባበሪያውን ቢሰሩ ትርፋቸው በእጥፍ እንደሚያድግ ገልጿል።
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ አጥ የነበሩ የማህበሩ አባላት መኖራቸውን የጠቀሰው ፍጹም አሁን በተመቻቸላቸው የሥራ እድል የራሳቸውን ገቢ እያመነጩ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ወጣቱ ሥራ የለም ብሎ ከመቀመጥ በአካባቢው ያለውን ጸጋ ወደ ኢኮኖሚ የሚቀይርበትን መንገድ ማሰብ ይጠበቅበታል ብሏል።መደራጀት የተለያዩ ሃሳቦችን ለማፍለቅና በትብብር ሠርቶ ለማደግ መፍትሄ እንደሆነ ከተሞክሮው መረዳቱን ገልጿል።
ሌላዋ በሥራ እድል ፈጠራ መርሃግብሩ ታቅፋ በሥራ ላይ ያገኘናት ወጣት ቤቴልሄም ማርቆስ ነች። ቤቴልሄም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ታቦር ክፍለ ከተማ ፋራ ቀበሌ የ‹‹2BNAD›› የወተት ከብት ርባታ ማህበር ሰብሳቢ ነች።
አስተዳደሩ ባዘጋጀላቸው የሥራ እድል ፈጠራ መሰረት አምስት ሆነው በመደራጀት የወተት ከብት ርባታ ሥራ እንደጀመሩ ትናገራለች።ከአምስቱ አባላት አራቱ ሴቶች ናቸው።አስተዳደሩ ስልጠና፣ የሥራ ቦታና ብድር ካመቻቸላቸው በኋላ ከ2013 ዓ.ም ነሃሴ ወር ጀምሮ ወደ ሥራ ገብተዋል።
መነሻ ካፒታላቸው ሁለት መቶ ሃያ ሺህ ብር ነው።በአካባቢው የወተት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም እንዳለ ካጠኑ በኋላ የወተት ከብት ርባታ ሥራ ለመጀመር መወሰናቸውን ትናገራለች።ሥራውን ሲጀምሩ በወተት ፍለጋ ረዥም መንገድ የሚጓዙ የአካባቢው ሰዎችንም ጭምር ለማሳረፍ ነበር።
ከማህበሩ አባላት ሶስቱ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው።በተማሩት የትምህርት ዘርፍ ሥራ እናፈላልግ ብለው ጊዜያቸውን ከማጥፋት ይልቅ ተደራጅተው መንግሥት ያመቻቸላቸውን የሥራ እድል መጠቀም የመጀመሪያ አመራጫቸው አድርገዋል።
የማህበሩ አባላት አሁን የራሳቸውን ሥራ መሥራት ከጀመሩ ወዲህ ደስተኛ ሆነዋል።ከራሳቸው አልፈው ለስድስት ሰዎችም የሥራ እድል ፈጥረዋል።በአጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታላቸውን ወደ ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር አሳድገዋል።
ወጣቶች በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ በማፈላለግ ጊዜያቸውን ከሚያባክኑ በየአካባቢቸው ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን ቢያጠኑ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ቤቴልሄም ምክር ለግሳለች። ከሁሉ በፊት ግን አዕምሮን አሳምኖ እራስን ለሥራ ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል።
ራሱን ለሥራ ያዘጋጀ ሰው በአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን በአጭር ጊዜ ወደ ኢኮኖሚ ቀይሮ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል ትላለች። በማህበር ተደራጅቶ መሥራት የተለያዩ ሀሳቦችን ለማመንጨት እና አቅምን አስተባበሮ ለመሥራት እንደሚጠቅም ቤቴልሄም ተናግራለች።
ሥራውን በቅርብ የጀመሩ ቢሆንም ተደራጅቶ መሥራታቸው ለውጤት እንዳበቃቸው ገልጻለች።ተራ በተራ ሥራዎችን እየተከፋፈሉ ይሠራሉ።ላሞችን መመገብ፣ ማጽዳት፣ ወተት መሸጥ፣ መኖ መግዛት ሁሉንም የሥራ ዘርፎች እየተቀያየሩ ይሠራሉ።
ሰባት የሚታለቡ ላሞች አሏቸው።በቀን ከሰባ እስከ ሰማኒያ ሌትር ወተት ለካፌዎችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ያኮናትራሉ።እያገኙ ያለው ውጤትም ተስፋቸው እንዲያብብ አድርጓቸዋል።የማህበሩ አባላት በቀጣይ የወተት ማቀነባበሪያ የመክፈት ህልም ይዘው ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ገልጻልናለች።
አስተዳደሩ በየጊዜው የሚያደርግላቸው ክትትልና ድጋፍ ለውጤታማነታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሳለች። ሌላው አዲስ ዘመን ያነጋገረው ወጣት ቀጄላ ፈርዳሞ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ቱላ ቀበሌ የአሊቶ የጓሮ አትክልት ልማት ማህበር ሰብሳቢ ነው።
ማህበሩ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ በገጠር ሥራ እድል ፈጠራ መርሃ ግብር ታቅፎ የጓሮ አትክልቶችን እያመረተ ይገኛል። መነሻ ካፒታሉ ስልሳ ሺ ብር ሲሆን አምስት አባላት አሉት።ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ አጥ የነበሩት አምስቱም የማህበሩ አባላት ዛሬ ባገኙት የሥራ እድል ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ናቸው። አንዳንዶቹም መኖሪያ ቤት መሥራት ችለዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ቃሪያ፣ ቲማቲምና ቆስጣ እያመረቱ እራሳቸውን ችለው ከመኖር ባሻገር የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። የእለት ወጪያቸውን እየሸፈኑ ከአንድ መቶ ሃምሳ ሺ ብር በላይ ባንክ አስቀምተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በማሳው ላይ ያለው ምርት ለገበያ ሲቀርብ አጠቃላይ ካፒታላቸው አምስት መቶ ሺ ብር ሊደርስ እንደሚችል የማህበሩ ሰብሳቢ ግምቱን ተናግሯል። የማህበሩ አባላት ተደራጅተው በመሥራታቸው ማንኛውንም የጉልበት ሥራ በትብብር እንዲሠሩ አስችሏቸዋል።ጠቃሚ ሀሳቦችንም እንዲለዋወጡ ረድቷቸዋል።
አንዱ መድሃኒት ሲረጭ ሌላው ይኮተኩታል፤ ምንም አይነት ድካም ሳይሰማቸው ሥራቸውን ለማከናወን እንደረዳቸው ሰብሳቢው ተናግሯል። ወጣቶች ከተማሩ በኋላ የሚፈልጉት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ መሥራት ነው።በተለይ የግብርና ሥራዎችን የመሥራት ፍላጎት አይታይባቸውም።
በተማሩት ትምህርት እየታገዙ በግብርና ሥራ ላይ ቢሰማሩ ግን ካልተማረው አርሶ አደር የተሻለ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል የማህበሩ ሰብሳቢ ቀጄላ። መንግሥት ሥራ አጦችን በማደራጀት የሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ወደ ሥራ ለመግባት ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸዋል።
የውሃ ፓምፕ እና የዘር መግዣ ገንዘብ ማግኘታቸው በሙሉ አቅም እንዲሠሩና በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።የመስኖ ሥራውን የሚያከናውኑበትን ቦታ ግን ከአርሶ አደር ላይ ተኮናትረው ነው። በዓመት የመሬቱን ኪራይ ለአርሶ አደሮች ይከፍላሉ።
አስተዳደሩ የእርሻ ቦታ ቢሰጣቸው በአጭር ጊዜ ሊለወጡ እንደሚችሉ ቀጄላ ተናግሯል። በትንሽ መሬት ላይ እንደ ወቅቱ ሁኔታ አትክልቶችን እየቀያየሩ በመትከል ወጤት ማግኘት ችለዋል።የሀዋሳ ከተማ በሰጣቸው የምርት ማከማቻና መሸጫ ቦታ ምርታቸውን ይሸጣሉ።
ወደፊት አሁን ከሚሰሩበት ሁለት ሄክታር መሬት ሰፋ ባለ ቦታ የመሥራት ፍላጎት አላቸው።በአዋሳ ከተማ እራሱን የቻለ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ የገበያ ማእከል የማዘጋጀት እቅድ እንዳላቸው የማህበሩ ሰብሳቢ ተናግሯል።
ኢያሱ መሰለ እና አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014