
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ልትፈፅም ትችላለች በሚል ስጋት በዚህ ሳምንት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አውሮፓ እንደሚልኩ ፔንታጎን አስታውቋል።
ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ከሰሜን ካሮላይና ግዛቷ ፎርት ብራግ፣ ወደ ፖላንድ እና ጀርመን የሚላኩ ሲሆን በጀርመን ያሉ ተጨማሪ አንድ ሺህ ወታደሮች ወደ ሮማኒያ ይላካሉ።
ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌላት ብታስተባብልም 100 ሺህ የሚገመተውን ሠራዊቷን በዩክሬን ድንበር አካባቢ አሰማርታለች። ሩሲያ አሜሪካ ወታደሮች ማሰማራቷን «አጥፊ» ስትል ጠርታዋለች።
ሩሲያ የዩክሬንን ደቡባዊ ክሪሚያ ፔኒንሱላን ወደ ግዛቷ ያስገባችው ከስምንት አመታት በፊት ሲሆን በምሥራቅ ዶንባስ ግዛት የተነሳውን ደም አፋሳሽ አመፅም መደገፏን ተከትሎም በሁለቱ አገራት ውጥረት እንደነገሰ ነው።
ሞስኮ የዩክሬን መንግሥት የሚንስክን ስምምነት ተግባራዊ አላደረገችም ስትል ትከሳለች። በሩሲያ የሚደገፉ አማፂያን ሰፊ ግዛት ተቆጣጥረው ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ቢያንስ 14 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።
ይህንንም ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭና በምሥራቅም ሰላም እንዲሰፍን በሚል በሩሲያና በዩክሬን በኩል ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በአውሮፓ የሚሰማራው የአሜሪካ ጦር በዩክሬን በቀጥታ በጦርነቱ ተሳታፊ ባይሆንም ለአሜሪካ አጋሮች ድጋፍን ይሰጣል።
አሁን አሜሪካ በአውሮፓ እያደረገች ያለችው የጦር ስምሪት ባለፈው ወር ፔንታጎን ካስፈለገ ወደ አውሮፓ ለማሰማራት ዝግጁ እንዲሆኑ ካስጠነቀቀው 8 ሺህ 500 ወታደሮች በተጨማሪ ነው።
«ለፑቲን እንዲሁም እውነቱን ለመናገር ለዓለም ኔቶ [የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት] ለአሜሪካም ሆነ ለአጋሮቻችን ከፍተኛ ስፍራ ያለው ነው የሚለውን ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው» በማለት የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014