ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይህንን ሂደት የሚመራና የሚያስተባብር አካል ለማቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። በኢትዮጵያ የተለያዩ አላማዎችን አንግበው በፖለቲካው መድረክ ላይ ያሉ ኃይሎችና ልሂቃን እንዲሁም ህዝቡ ተቀራርበው ጥያቄዎችና ሐሳቦቻቸውን መሠረት አድርገው እንዲወያዩ ለማስቻል እንዲሁም ለሀገራዊ አንድነት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አገራዊ ምክክሩ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
የሚቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በህዝቡ፣ በፖለቲካ ፓርቲ እንዲሁም በልሂቃኑ መካከል ላለፉት ዓመታት ምላሽ ሳያገኙ ቀርተው መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማንሳት ታላላቅና ተከታታይ አገራዊ ምክክሮችን አሳታፊ በሆነ መንገድ በማካሄድ መግባባትን መገንባት ደግሞ የምክክር ኮሚሽኑ ዋነኛ አላማው ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሣሥ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ያጸደቀው እና ላለፉት ሁለት ወራት ሲረቀቅ ብሎም የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉበት የቆየው “የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን” አዋጅ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ እንደሆነ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ሁለት ጊዜ መሠረታዊ የማሻሻያ ስራዎችን አልፈዋል። አዋጁ በርካታ አስተያየቶችና ትችቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
በቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአሁኑ የፍትሕ ሚኒስቴር አርቃቂነት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መሪነት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ስላለው አዲሱ ኮሚሽን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔን አነጋግረናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን” ተቋቁሞ ወደ ስራ ለመግባት የተለያዩ ጥረቶች በመከናወን ላይ ናቸው። እርስዎ በኮሚሽኑ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?
ዶክተር አረጋዊ፦ እስከ ባለፉት ሶስት ዓመታት ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን የሚያዘው በሃይል ነበር። አገሪቱ ውስጥ የተገነባውን እሴት በማውደምና በመናድ አዲስ ሥርዓት በመጀመር በየጊዜው ቅራኔዎች መልካቸውን እየቀየሩ እርስ በእርስ መጣረስና አንድ የሚያደርጉ እሴቶቻችን ላይ ጥላሸት የመቀባት ሂደቶች ነበሩ።
አዲሱ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን መሰረት ለማስያዝ ታልሞ ሃሳቦች በመድረኮች ላይ ብቻ መፍትሄ የሚያገኙበትን አሰራር ለመዘርጋት ለሕዝብ ቃል በገባው መሰረት ወደ ተግባር ለመለወጥ አገራዊ የምክክር መድረኮች እንዲኖሩ በርካታ ርቀቶችን መሄዱም የሚያስመሰግነው ነው።
ይህንን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉትን የእርስ በእርስ ቅራኔዎችና መጠራጠሮች በተለይም በመንግሥት ሥርዓት ግንባታ፣ ሕገ መንግሥት፣ ታሪክና ትርክቶች እንዲሁም በርካታ ዋና ዋና የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሲገባን፤ ያልተግባባንባቸው ላይ አካታች የሆነ ብሔራዊ ውይይት በማድረግ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ይሰማኛል።
ይህም ይበል የሚያሰኝ እኔም ሆንኩ የምመራው ፓርቲ የምንደግፈው ሃሳብ ነው። ጎልተው የሚስተዋሉ ልዩነቶች ለጠመንጃ መማዘዝና የአገሪቱ ሰላም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖራቸው ይህ ብሔራዊ ውይይት ለዘላቂ መፍትሄዎቻችን ጉልህ ሚና ይጫወታል።
በሌላ በኩልም መንግሥት የጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄድ የጎላ ሚናም አለው። ብሔራዊ ምክክሩ በርካታ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር ምቹ ሁኔታዎችን በአገሪቱ ውስጥ ለመፍጠር ያስችላል፤ ለእነዚህ ውይይቶችም መንግሥት በርካታ አስቻይ ተግባራትን እየፈጸመ ቢሆንም ወደፊት እነዚህ አስቻይ ሁኔታዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ የምክክር ኮሚሽን ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል?
ዶክተር አረጋዊ፦ እዚህ ላይ አካታች ብሔራዊ ውይይት የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ማንኛውም ዜጋ ወይም ማንኛውም አስተሳሰብ ያለው ቡድንና ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚል አካል ሁሉ በብሔራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ አለበት። ዜጎች ወይም ማናቸውም ቡድኖች በራሳቸው ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ መንግሥት ፍላጎት ያለውና ይህ ተግባር በመንግሥት ፍላጎት ብቻ እንዳይወሰን በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ኃይሎችም ብሔራዊ ምክክር እንዲኖር ሲጠይቁ ነበር።
መንግሥት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወንጀል ሰርተው በእስር ላይ የሚገኙ ዋና ዋና የፖለቲካ አመራሮችና ተከታዮቻቸው ክሳቸው እንዲቋረጥ በማድረግ ተሳትፏቸው ወሳኝነት እንዳለውና እውነትም አካታች ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ታልሞ የተወሰነ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ለዚህም ነጻና ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም አዋጅ ወጥቶ በርካታ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ለዚህ ብሔራዊ ውይይት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውና ለተግባራዊነቱም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ አበረታች ነው። በሌላ በኩልም አንደ አገር የመጣንበት መንገድ እጅግ የተወሳሰበ ከመሆኑ አንጻር በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ መፍትሔ ሳንሰጣቸው የመጡ በርካታ ችግሮችም አሉብን።
በመሆኑም እነዚህ ችግሮች ደግሞ አመለካከታችን ላይ ራሱ እያሳደሩ ያሉት ተጽዕኖ ላቅ ያለ በመሆኑ በየጊዜው በጥቃቅን ችግሮች እየተነሳን ጦርነት ውስጥ እየገባን ነው። ለጎስቋላው ኑሯችንም ምክንያት እየሆኑ ነው። አሁን ሰዎች ያላቸውን ማንኛውንም አመለካከት ወደ ጠረጴዛ አውርደው ውይይት አድርገውባቸው ተመካክረውባቸው የጋራ አድርገው ጎጂ የሆኑ አመለካከቶችን ወደጎን አስቀምጠው፤ ሀገራችንን ለማዘመንና በለውጥ ሂደት ማስኬድ በጣም አስፈላጊ ነው።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የምክክር መድረኩ አይነተኛ ጠቀሜታ ያለው ከመሆኑ አንጻር እንደውም ዘግይቷል ብንል ማጋነን አይሆንም። በመሆኑም ያሉብንን የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ የውይይትና የመግባባት መድረክ መከፈቱ በጣም አስፈላጊና ለእድገታችን እንዲሁም ለሰላማችን ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ኮሚሽን መቋቋሙ ብቻ እንደሀገር የምናስበውን መግባባትና ብሔራዊ እርቅ ያመጣል ብለው ያስባሉ ?
ዶክተር አረጋዊ ፦አዎ ያመጣል። እዚህ ላይ እኮ ሰዎች በችግሮቻቸው ወይም ደግሞ በማያግባቧቸው ነገሮች ላይ መወያየት ከቻሉና ከጀመሩ የማይጠቡ ልዩነቶች አይኖሩም ። ነገር ግን አንዳንድ ግዜ ጥቂቶች ምናልባትም ለግል ጥቅማቸው በማሰብ ብቻ በጭፍን ልዩነቶች በሌሉበት ልዩነት እንዳለ አስመስለው በማቅረብ ችግር ለመፍጠር ይሞክራሉ።
ይህንንም ሁኔታ ቢሆን ማስቀረት ወይም መቋቋም የሚቻለውና እነዚህን የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ ሲሉ የልዩነት መንፈስን በአገር ደረጃ የሚዘሩትን አደብ ለማስገዛት መሰል ውይይቶች የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች (የፖለቲካ ሰዎች ) ወደ ግጭትና አለመግባባት የሚያመሩት በአግባቡ መደማመጥ ስለማይችሉ ነው።
በዚህ ዘመን ደግሞ ከግጭትና ከአለመግባባት ወደጦርነት ከሚያመሩ አካሄዶች ይልቅ መነጋገርና መደማመጥ ትልቅ ዋጋ አለው። በመሆኑም ይህንን ማድረግ ነገ ለልጆቻችን መልካም ሀገር በመደማማጥና ችግሮች በጋራ በመፍታት ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ ማስረከብ እንችላለን።
ከሚያለያዩን ይልቅ አብሮነታችንን የሚያዳብር የሚያስማማ ነገር ማድረጉም ለማንም የሚጠቅም ነው። በነገራችን ላይ እንደ አገር የምንፈልገውም ሆነ የምንጠላው ነገር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም እነዚህን መሰረት በማድረግ የሚጠሉትን ነገሮች ለማስወገድ የሚፈለጉትን ነገሮች ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ ለማቅረብ ተቀራርቦ መነጋገርና መወያየት ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ መድረኩ ነፍጥ አንግበው መንግስትን እየተፋለሙ ያሉ ሀይሎች የማይካተቱበት ከሆነ በሀገሪቱ ዘላቂ መግባባትና እርቅን ለመፍጠር ያስቸግራል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
ዶክተር አረጋዊ ፦ አንዳንድ ወገኖች ፍላጎቶቻቸውን በሌላው ላይ ለመጫን ሀይል ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ ምናልባትም በተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን ጫናው የበዛበት ህዝብ ቆይቶ የሚወስነው ውሳኔ ደግሞ ከባድ በመሆኑ ከዚህ ሁሉ የሚሻለው ነፍጥ ያነገቡትም ወደ ውይይቱ መምጣታቸው ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም። ነገር ግን ችግራቸውን ወደ ጠረጴዛ አምጥተው መፍታት የማይፈልጉ ፍላጎታቸውን ግን በሀይል መጫን የሚያስቡ ወገኖች ካሉ ወደ ውይይቱ ቢመጡም የሚኖረው ትርጉም በጣም አናሳ ከመሆኑም በላይ ውጤታማ አያደርገውም።
በመደማመጥ በመወያየት የማይለወጥ ነገር ካለመኖሩም በላይ አገር ለማስተዳደር ብቁ ሀሳብ ያላቸውም ሀሳባቸውን ወደፊት በማምጣት የአመክንዮ የበላይነት አለኝ ብለው የሚያምኑ ከሆነ ወደ መድረኩ መምጣትን መጥላት አያስፈልግም። በመሆኑም ምክንያታዊነትን ተጠቅመን ችግሮቻችንን እንደ አገር መፍታት ስለምንችል ለዚህ ሊተባበሩ የሚችሉ ሀይሎችን ወደመድረኩ ማምጣት ጠቃሚ ነው።
ከዚህ መድረክ የሚቀሩ ካሉ ደግሞ እነሱ ለሀገር ወግነናል ለሚሉት ህዝብ ደንታ ቢሶች በመሆናቸው ምንም ማድረግ አይቻልም።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ቀደም የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በሚል የተቋቋመ ኮሚሽን አለ ? አሁን ደግም ይኸኛው ኮሚሽን እየተቋቋመ ነውና ልዩነት ይኖራቸዋል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ እንግዲህ እርቀ ሰላም ኮሚሽንና “የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን” ልዩነት አላቸው። እርቀ ሰላም ኮሚሽን ዋና ሚናው የነበረው ሁለት የተጣሉ አካባቢዎችን ወደ አንድ በማምጣት ችግሮቻቸው ላይ ውይይት እንዲያደርጉ መድረክ መፍጠር ነው። “የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን” የውይይት መንገድ ደግም አጠቃላይ የአመለካከት ችግሮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ነው። ችግሮችን በሰላም በውይይት የመፍታት አካሄድን የምንተዋወቅበትና የምናዳብርበት ሂደት ስለሆነ ከእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ለየት ያለ ሚና ያለው ነው።
ዞሮ ዞሮ ግን ሁለቱም ለሰላምና ለሰላማዊ ኑሮ መንገድ የሚጠርጉ በመሆኑ በተለይም የሰላምን የእርቅ እንዲሁም የውይይት መድረኩን በአግባቡ መጠቀም ለሚፈልግ ሀይል ጥሩ አጋጣሚ ነው። በእነዚህ መድረኮች ላይ ሁሉም አካል ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየት ይኖርበታል። ይህ ከሆነ ደግሞ የታለመለትን ግብ ይመታል።
በሌላ በኩል የክስ መቋረጡ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በመንግሥት የተወሰደ እርምጃ ነው። ክሳቸው የተቋረጠላቸው እስረኞችም በሰጥቶ መቀበል የሚያምኑና በቀጣይም ሰላምን አንግበው ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያውያን አስበውና ተቆርቁረው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የክስ ማቋረጡም ሆነ አሁን እሱን ተከትሎ እየመጣ ያለው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ውጤት ይኖረዋል። በነገራችን ላይ ይህ የመንግሥት ውሳኔ በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም አመለካከቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹ በር የሚከፍት ነው።
በተለይም እነዚህ ሀይሎች ሊረዱት የሚገባው ነገር በጉልበት ሐሳብን በሌላ ሰው ላይ የመጫን አካሄድ ጊዜ ያለፈበት ማንም የማይቀበለው የዓለም አካሄድም ከዚህ ፍጹም የተለየ መሆኑንም ነው። ሀገር ሰላም ትፈልጋለች፤ ሰላም የሚመጣው ደግሞ ሰላማዊ ትግልን በሰለጠነ ምክክር ታጅቦ ሲመጣ ነው። ሀገራችንን ወደ ሰለጠነ ፖለቲካዊ መንገድ ልንወስዳት የምንችለውም ይህንን የሰለጠነ አካሄድ መከተል ስንችል ብቻ ነው። አዲስ ዘመን ፦ በመድረኩ የሚሳተፉ አካላትስ ሚናቸው ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፦ እውነት ለመናገር የመድረኩ ተሳታፊዎች ትልቅ ኃላፊነትና የቤት ስራ ያለባቸው ናቸው። ሀገር ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ የውይይት መድረክ ከመፍጠር ጀምሮ በመድረኩ የሚነሱ ሀሳቦችን ወደ አንድ እስከ ማምጣት የደረሰ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማኛል። ከምንም በላይ ደግሞ ሊያስቀድሙ ወይንም ደግሞ አሰራራቸውን ሊያደርጉ የሚገባቸው አገራቸውን ያስቀደመ አንድነታችንን የጠበቀ በዛው ልክ ደግሞ ከአድሏዊ አሰራር የጸዳ መንገድን መከተል እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን ያሉ ዋና ዋና መሰረታዊ ችግሮችን በተለይም እንዳንግባባ አድርገው ያሰሩንን ምናልባት የታሪክ አረዳድ፣የፖለቲካ አካሄድ እንዲሁም የድንበርና የወሰን ችግሮችን ሳይቀር ነቅሰው በማውጣት በነዛ ላይ መልክ ባለውና በበሰለ እንዲሁም በሰለጠነ መንገድ ወይይት እንዲደረግባቸው ማድረግ ይገባቸዋል። በመሆኑም ለዚህ ስራ የሚመለመሉ ሰዎችም እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል።
ምክንያቱም ስራው ቀላል ካለመሆኑም በላይ ጥልቅ እውቀት የማመዛዘን ችሎታ ነገሮችን የማሳመን ብቃት በተለይም ደግሞ ንጹህ ህሊናና ከተለጣፊነት የጸዳ ስብዕና ያላቸው ሰዎች ይፈልጋል። በመሆኑም እነዚህ አካላት ገለልተኛ ለመሆን መወሰን ብሎም ለህሊናቸው ብቻ ተገዢ እንደሚሆኑም እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ለራሳቸው ወይም ለሚፈልጉት ብሔር ሃይማኖት ግለሰብ ወይም ሌላ ለማድላት አስበው ከመጡ፤ ከዚህ ቀደም ካሳለፍናቸው የውይይት መድረኮች የተሻለ ውጤትን ካለማስገኘታቸውም በላይ ለከፋ ችግር ሊያጋልጡን የሚችሉበት እድል የሰፋ ነው። እኔ ይህንን መሰሉ የውይይት መድረክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ በግሌ ይሰማኛል። ወደቀናው መንገድ እንደሚመራንም ከፍተኛ የሆነ እምነት አለኝ።
ከላይ እንዳልኩት ግን መድረኩ ቀና እንዲሆን የታለመለትን ግብ እንዲመታ በተቻለ መጠን የኮሚሽነር ምርጫው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እና በስራው ላይ የሚመደቡ አካላትን ከማንኛውም ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላም ቢሆን የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ምክረ ሀሳቦች እንደ ሀገርና ህዝብ ማክበር በተቻለ መጠንም ለተፈጻሚነታቸው የራስን ጥረት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014