የአገር ፍቅር ቴአትር በመደበኛ ስሙ ቴአትር ቤት ነው። የአገር ፍቅር ቴአትር ግን በዚህ በመደበኛው አገልግሎቱ ብቻ አልተወሰነም፤ የአገርን ባህል፣ ታሪክና ጀግንነት የሚያሳዩ ጥበባዊ ሥራዎች ይቀርቡበታል። በመደበኛው አገልግሎቱ ብቻ አይደለም የአገር ፍቅር ስሜት እያጎለበተ ያለው።
ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ለአገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚጀመሩት በአገር ፍቅር ቴአትር ነው። ለምሳሌ በተለያየ አጋጣሚ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ የሚሰባሰበው አገር ፍቅር ቴአትር ነው። የበጎ አድራጎት አሰባሳቢ አካላት ቦታ የሚጠቁሙት አገር ፍቅር ቴአትርን ነው።
እንደ አልባሳትና ሌሎች የደረቅ ምግብ አይነቶች በዚህ ቦታ ላይ ይሰበሰባሉ። ይህም ለድጋፍ አድራጊዎች የአገር ፍቅር ነው ማለት ነው። እንግዲህ ይህ ሁሉ ሁነት ሲከናውንበት የቆየው አንጋፋው የአገር ፍቅር ቴአትር ለረጅም ጊዜ ሥራ ላይ አልነበረም። በእድሳት ላይ ቆይቷል፤ እድሳቱ ተጠናቆ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑ ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል። ቴአትር ቤቱም ማራኪ ሆኖ ታድሷል። በተለይም በሩ የክራር ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ በመሠራቱ የብዙዎችን ቀልብ እየሰባ ይገኛል።
የአገር ፍቅር ቀስቃሹን የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት መታደስ ምክንያት በማድረግ ስለቴአትር ቤቱ ታሪክና ክንውኖች ከቴአትር ቤቱ የማኅበራዊ ገጽ ላይ እና ከተለያዩ ሰነዶች ካገኘናቸው መረጃዎች በመነሳት የቀደም ማንነቱን እንወቅ። ለዛሬው ማንነቱ ደግሞ የቴአትር ቤቱን ዳይሬክተር አናግረናል። የቴአትር ቤቱ ታሪክ የአገር ፍቅር ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች የተቀዳ ነው።
የጣሊያን ወራሪ ዓድዋ ላይ የሽንፈት ማቅ ለብሶ መመለሱ ለ40 ዓመታት ያህል ሲከነክነው ኖሮ ዳግም ኢትዮጵያውያንን ሊወር መጣ። ዳሩ ግን ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ሲመጣም ያው ሆነው ጠበቁት።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ደምና አጥንታቸው በአገር ፍቅር የተሞላ ኢትዮጵያውያን፤ በተበታተነ አደረጃጀት አርባ ዓመት ሙሉ የታጠቀን ወራሪ ጠላት በቀላሉ ማሸነፍ እንደማይቻል ተረድተው ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ፍቅር ማኅበር››ን መሰረቱ።ማህበሩ ኢትዮጵያውያን አባቶቻቸው በደም እና አጥንታቸው ጠብቀው ያስረከቧቸውን ዳር ድንበር እንዲያስጠብቁ፣ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው አንድነታቸውን ከምን ጊዜውም በላይ እንዲያጠናክሩ፣ በተለይ ደግሞ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ያለው ሕዝብ በአርበኝነት ስሜት ተነሳስቶ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ማድረግን ዓላማው አድርጎ ተቋቋመ።
ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀሰቅስ እና አንድነትን ሲሰብክ የነበረው ይሄው ማኅበር፤ ከተቋቋመ ከዘጠኝ ወራት እጅግ ውጤታማ እንቅስቃሴ በኋላ በሚያዚያ ወር 1928 ዓ.ም፣ በፋሽስት ጦር አዲስ አበባን መቆጣጠር ምክንያት ለመፍረስ ተገደደ።
ከመስራቾቹ እና ዲስኩር አቅራቢዎቹ መካከል ግማሾቹ በውስጥ አርበኝነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰማሩ፣ ግማሾቹ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት በመሰደድ የአርበኝነት ሥራውን አጧጧፉ። ከንጉሡ ጋር የተሻለ ቀረቤታ እና እድል ያላቸው ደግሞ ወደ አውሮፓ ተሰደዱ። የማኅበሩም የመጀመሪያ ምዕራፍ በዚሁ ተደመደመ።
ከነፃነት በኋላ በግንቦት ወር 1934 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ፍቅር ማኅበር በቀድሞ መሥራቹ በአቶ መኮንን ሀብተወልድ በድጋሚ ተቋቋመ። በዚህ ጊዜ ሲቋቋም እንደ ቀድሞው በማኅበርነት ብቻ ሳይሆን እንደ ኪነ ጥበብ ቤትነትም ጭምር ነበር። መቀመጫውም ታዲያ እንደመጀመሪያው በራስ ኃይሉ ሕንፃ፣ በዛፍ ጥላ ስር ወይም ደግሞ ሜዳ ላይ ሳይሆን፣ ሕዝቡንና ሥነ ጥበብን ባከበረ መልኩ በትክክለኛ አዳራሽ ውስጥ እንዲሆን አቶ መኮንን በእጅጉ ደክመዋል።
በዚህም በጠላት ወረራ ጊዜ የጣሊያን መኮንኖች ይዝናኑበት የነበረው በአሁኑ የአገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ግቢ ውስጥ የሚገኘው፣ ከ200 እስከ 300 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው ‹‹ኪው ክለብ›› እንዲሰጠኝ ሲሉ ጥያቄያቸውን ለቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አቀረቡ።
ጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ በኋላ እንደቀድሞው ዲስኩር የሚያቀርቡ ሳይሆን፣ ለዘፈን የሚሆን ድምጽ እና የውዝዋዜ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ሆቴሎችና መሸታ ቤቶች ከባልደረባቸው በሻህ ተክለማሪያም (ከጠላት ወረራ በፊት ከአርመናዊው ኬቮርክ ናልባንዲያን ጋር በመሆን ሙዚቃ ያስተምሩ ነበር) ጋር በመሆን አሰባስበው ዝግጅቶቻቸውን ማቅረብ ጀመሩ።
እንዲህ እንዲህ እያለ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በ1947 ዓ.ም በአሜሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ። ከጉብኝታቸው መልስም የአሜሪካ ቆይታቸውን የሚያሳይ መጠነ ሰፊ አውደ ርዕይ እንዲዘጋጅ አዘዙ። ከዝግጅት መርሐ ግብሮቹ አንዱ ለአውደ ርዕዩ የሚመጥን ትልቅ አዳራሽ ማስገንባት ነበር። የአዳራሹ ግንባታ ሙሉ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የቴአትር ቤት አዳራሾች ግንባታ ላይ አሻራቸው በጉልህ የተቀመጠው ጣሊያናዊው መሐንዲስ ቢያንካ ላይ ወደቀ።
ቢያንካም በተለመደው ጥራት፣ ታማኝነት እና ፍፁም ታዛዥነት በተሰጠው ዲዛይን መሠረት ከፊት ለፊት መድረክ፣ ከኋላ ደግሞ ለንጉሣውያኑ ቤተሰብ መቀመጫ የሚሆን ሰገነት ያለው ግዙፍ አዳራሽ ሰርቶ አስረከበ። ከአውደ ርዕዩ በኋላ አዳራሹ ከቴአትር በስተቀር ለሌላ አገልግሎት መዋል የማይችል በመሆኑ ለኢትዮጵያ አገር ፍቅር ማኅበር ሳምንታዊ ትርዒት አቅርቦት እንዲውል ተደረገ። አገር ፍቅር ቴአትርም የዛሬ አዳራሹን ለማግኘት በቃ።
ይህ አዳራሽ አሁን ያለውን ቅርፅ የያዘው ግን በ1994 ዓ.ም አርቲስት ስዩም አያና ቴአትር ቤቱ ኪነ ጥበብን ብሎም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚያንፀባርቅ ይዘት ሊኖረው ይገባል ብሎ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት የተሀድሶ ግንባታ ከተደረገለት በኋላ ነው። የኢትዮጵያ አገር ፍቅር ማኅበር(ከድል በኋላ አገር ፍቅር ቴአትር) እንደ አዲስ ሲቋቋም በቂ ሀብት አልነበረውም፤ በዚህ የተነሳም ለሠራተኞቹ ደመወዝ እንዲሁም ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ምንም አይነት ገቢ የሌለው ነበር። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረትም በቅድሚያ በንጉሡ ትዕዛዝ ከመርካቶ ነጋዴዎች ለማኅበሩ በሚል በሚሰበሰብ ገቢ እንዲተዳደር ተደረገ። በኋላም ቋሚ የገቢ ምንጭ አስፈላጊ በመሆኑ በእቴጌይቱ ድጋፍ በግቢው ውስጥ ከሚሠራ የስጋጃ ምንጣፍ ገቢ፣ ከጠንቋዮች ግብር (ጠንቋዮች ፈቃድ አውጥተው ግብር እየከፈሉ ይተዳደሩ ነበር።
ግብሩም በቀጥታ ለአገር ፍቅር ቴአትር ገቢ ይደረግ ነበር)፣ ከአዝማሪዎች የሚገኝ ቀረጥ፣ ከእስልምና ኃይማኖት የጽሕፈት ቤት ኪራይ (በወቅቱ የእስልምና እምነት ማስተዳደሪያ ጽሕፈት ቤት በአገር ፍቅር ቴአትር ቅጥር ውስጥ ነበር)፣ ለተለያዩ በዓላት ከሚደረግ ድግስ ከሚገኝ ገቢ፣ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አገር ፍቅር ማኅበር ስር ነበር ከሚታተሙት የመነን መጽሔት እና የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ ሽያጭ ለትአትር ቤቱ ገቢ ይሰብሰብ ነበር።
በተጨማሪም ከባካራ እና ሮሌት ቁማር ገቢ (ማህበሩ ቁማርን በሕጋዊነት ያጫውት ነበር)፣ ከቀረጥ ድጎማ፣ ከሐረር የኢትዮጵያ አገር ፍቅር ማኅበር ቅርንጫፍ፣ ከኦርኬስትራዎች፣ ከድርሰት ክፍያ፣ ከዝክረ ኪነጥበባት ቀረጥ፣ ኪው ክለብ ለመዝናናት ከሚገቡ ሰዎች የሚሰበሰብ የክራቫት ኪራይ (የምሽት ክለብ ገብቶ ለመዝናናት ክራቫት ማድረግ የግድ ነበር) የሚገኙ ገንዘቦች የቴአትር ቤቱ ገቢ ማስገኛዎች ነበሩ።
የአገር ፍቅር ማኅበር አገር ፍቅር ቴአትር የሚለውን ስያሜ ያገኘው በታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በ1961 ዓ.ም ነበር። ቴአትር ቤቱ ከአዲስ አበባ የጥበብ አቅርቦቶቹ በተጨማሪ ተጓዥ የቴአትር ቡድን በማቋቋም በፈረስ እና በቅሎ በየክፍላተ አገራቱ በመዘዋወር የቴአትር ትርኢት ያቀርብ ነበር። በዚህም የቴአትር ጥበብን ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉም በላይ ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘትም ችሏል።
አገር ፍቅር ቴአትር ለዘመናዊ ተውኔት አፃፃፍና ዝግጅት ጥርጊያ ጎዳና መክፈት ከጀመረበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በኢፍትሐዊነት፣ በምዕራባውያን ባህል ወረራ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ላይ በእርግጥም የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ የቀየሩ በርካታ የጥበብ ሥራዎችን አቅርቧል። ቴአትር ቤቱ የታላላቅ የጥበብ ፈርጦች መገኛ ሆኖም ቆይቷል፤ ከእነዚህ የጥበብ ፈርጦች መካከልም ተስፋዬ አበበ፣ አበራ ደስታ፣ ዘነበች ታደሰ፣ የሺ ተክለወልድ፣ ሙናዬ መንበሩ፣ በላይነሽ አመዴ፣ በቀለ ወልደፃዲቅ፣ እና ግርማ ብስራት በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በአገር ፍቅር ቴአትር በተለይም ከ1940 ዓ.ም እስከ 1960 ዓ.ም ይቀርቡ የነበሩ ሥራዎች በአብዛኛው መልካም ሥነምግባርን ለማስተማር ገፀ ባህሪያቱ በመልአክ እና ሰይጣን ተምሳሌትነት የተፃፉ ነገር ግን ቴክኒካዊ የአቀራረብ ጉድለት የነበረባቸው ስለመሆናቸው የቴአትር ባለሙያዎች መረጃዎች ይጠቁማሉ። የመድረክ ግንባታ አቅማቸው እጅግ ደካማ እንደነበረም በመጥቀስ፣ ለአንድ ቴአትር የተገነባ መድረክ ለሌላ ተውኔትም ያገለግል እንደነበርም ያመለክታሉ። እንግዲህ ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ ያሳለፈው የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከ20 ዓመት (1994 ዓ.ም) በኋላ ዕድሳት ተደርጎለታል።
የቴአትር ቤቱ ዳይሬክተር አቶ አብዱልከሪም ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ የለቀማ ሥራዎች ናቸው የቀሩት፤ እነዚህም በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃሉ። በግንባታ ሥራው ውስጥ ግን ወንበር እና መጋረጃ አልተካተተም።
ለወንበርና መጋረጃውም ጨረታ ወጥቶ ከአሸናፊው ድርጅት ጋር ውል ተፈጽሟል፤ ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ወንበርና መጋረጃው ያልተጠናቀቀው የትልቁ አዳራሽ እንጂ ትንሿ አዳራሽ አሁንም አገልግሎት መስጠት ትችላለች። ትልቁ አዳራሽ ከዚህ በፊት 835 ወንበሮች የነበሩት ሲሆን፣ አሁን 610 እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞው የወንበር አቀማመጥ ምቹ አለመሆኑ ነው። የወንበሮቹ አቀማመጥ በጣም የተጠጋጋ፣ ለመተላለፍም የሚያስቸግር ነበር።
አሁን ግን በስታንዳርድ እንዲቀመጥ መደረጉን ያብራራሉ። የቴአትር ቤቱ መታደስ የኪነ ጥበቡን መንፈስም እንደሚያድሰው አቶ አብዱልከሪም ተናግረዋል። ምቾት በሌለውና ለዓይን ማራኪ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ታዳሚን መሳብ እንደማይቻል ተናግረው፣ ለዕይታ ጥሩ መሆኑም ለታዳሚውም ለከያኒውም አነሳሺ ይሆናል ብለዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014