የትኛውም የስፖርት ቡድን ሊኖሩት ከሚገባቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱና መሠረታዊው የስነልቦና አማካሪ ነው። ስፖርተኞች አቅማቸውን አውጥተው በልበ ሙሉነት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ በውድድር ወቅት አስቀድመው የአሸናፊነት መንፈስ እንዲላበሱ፣ ከጉዳትና በሽንፈት ከሚመጣ ድብርት በቶሎ እንዲላቀቁ፣ በተደጋጋሚ የውድድርና ስልጠና ሂደት እንዳይሰላቹ፣ወዘተ በማድረግ ረገድ የስነልቦና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ግን እነዚህን ባለሙያዎች በስፖርቱ እምብዛም አይስተዋሉም። በዚህ ምክንያት ሽንፈትን አስቀድሞ በመቀበል እንዲሁም በተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሲደርስ ይስተዋላል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ይህ ችግር ከምን ይመነጫል? ምን ቢሰራስ ሊፈታ፣ ሊስተካከል ይችላል? በሚሉትና መሰል ጥያቄዎች ላይ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ መምህርና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በስፖርት ሳይኮሎጂ ከሰሩት ዶክተር ሃብታሙ ደመላሽ ጋር ቆይታ አርጓል።እሳቸው ባለፉት ዓመታትም በዚሁ የስፖርት ስነልቦና ላይ በተለያዩ የስፖርት ማኅበራት በመገኘት ስልጠናዎችን ሰጥተዋል።
ዶክተር ሀብታሙ እንደሚሉት፤ ስነልቦና ከአዕምሮ ጋር ይያያዛል፤ በስፖርቱ ደግሞ ከአቅም ጋር ይገናኛል፤ ለአዕምሮ ዝግጁነት የሚያስፈልግ ሳይንስ ነው። የትኛውም ስፖርት በዋናነት አራት ምሰሶዎች አሉት፤ እነርሱም የአካል ብቃት፣ ቴክኒክና ታክቲክ፣ ስነልቦና እንዲሁም ስነምግብ ናቸው።
ካደጉት አገራት ተሞክሮ ለመመልከት እንደሚቻለው፤ ሶስቱ ምሰሶዎች ተቀራራቢ ሁኔታ ላይ ይደርሱና አንዱ ተወዳዳሪ ሌላኛውን ይረታል። የዚህ ምክንያት ደግሞ በስነልቦና ያላቸው ልዩነት ነው።
ብቃትን ለማሳደግ 20 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ስነልቦና እንደሚይዝ ዶክተር ሃብታሙ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ያመላክታሉ። የግል እና የቡድን ስነልቦና የየራሳቸው ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ እነዚህ ተዳምረው በቡድኖች ውጤት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ከፍተኛ የስፖርቱ ፍቅር ያላቸው፣ ዝግጅት የሚያደርጉ፣ ለስፖርቱ ዋጋ የሚከፍሉ እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩ በማይገባቸው ስፍራ የሚገኙ ስፖርተኞችም ይኖራሉ የሚሉት ዶክተር ሀብታሙ፣ ለእዚህም ብራዚላዊውን አንጋፋ ተጫዋች ሮናልዲኒሆ ጎቾን በአብነት ይጠቅሳሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከፍተኛ የእግር ኳስ ተሰጥኦ የነበረው ይህ ኮከብ ተጫዋች ሰላሳዎቹን ከመጀመሩ ያለ ዕድሜው ስፖርቱን አቁሟል።
በተቃራኒው ሌሎች ተጫዋቾች እስከ 40 ዓመታቸው ድረስ ይጫወታሉ። ይህም ተጫዋቾቹ ያላቸውን የስነልቦና ዝግጅት በግልጽ የሚያመላክት ነው። ወደ ክለብ ሲመጣም ክለቦች ተቀራራቢ በሆነ ስልጠና እና የቴክኒክና ታክቲክ እውቀት ካለፉ እንዴት ሊሸናነፉ ይችላሉ ለሚለው ምላሹ የሰነልቦና ጉዳይ ይሆናል።
በእግር ኳስ ስፖርት ስነልቦና ከልጅነት አንስቶ ሊያድግ እንደሚገባው የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ይገልጻሉ። የቡድን ስፖርት እንደመሆኑ ተጨዋቾቹም የተለያየ የኋላ ታሪክ ያላቸው ስለሚሆኑ ነው በሜዳ ላይ ልዩነት ሲታይ የሚስተዋለው።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ነባራዊ ሁኔታ ስነልቦና አለ ለማለት አያስደፍርም የሚሉት ዶክተር ሀብታሙ፣ ከታዳጊዎች ስልጠና ጀምሮ እስከ ትልቅ ቡድን ከስነልቦና ማማከር ጋር በተያያዘ እንዳልተሠራም ያመለክታሉ።
የብሔራዊ ቡድኑን የአሰልጣኞች ቡድን ማሟላት ብቻ ትርጉም እንደማይኖረውም ተናግረው፣ ከላይ የተሠራ ነገር ከታች መሠረት ከሌለው ለውጥ ማምጣት እንደማይችልም ነው ያብራሩት።
የኋላ ታሪካቸው የተለያየ የሆኑ ተጫዋቾች ለመግባባትም ይቸገራሉ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በእግር ኳሱ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጠራል ይላሉ። የኢትዮጵያ ሊግ ውድድር ተኮር፣ የተወሰኑ ተጫዋቾች ብቻ ጎልተው የሚወጡበት፣ በታዳጊዎች ላይ ስለማይሰራ አዳዲስ ተጫዋቾች የማይታዩበት መሆኑንም አብራርተው፣ በእርግጥ ስነልቦናው ላይ ብቻ ሳይሆን አካል ብቃትም ሆነ ስነ ምግብ ላይ በደንብ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።
እንደ ዶክተር ሀብቱ ገለጻ፤ ይህንን ሁኔታ ለማረምም በመሠረታዊ ክህሎት ስልጠናዎች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤ በየደረጃው የሚገኙ አሰልጣኞችም የስነልቦና ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል።
ሁሉም ክለቦች የስነልቦና ባለሙያዎች እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ስነልቦና ከትምህርት ዓይነት ባለፈ ራሱን ችሎ እንዲሰጥ በማድረግ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባም ይጠቁማሉ። እስከዚያው ግን ባሉት ባለሙያዎች አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን በመጋበዝም በስፖርት ስነልቦና ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል።
የስፖርት ባለድርሻ አካላትም በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ውጤቱ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ቢያደርጉ መልካም ነው።
ከስፖርቱ የስልጠና ቡድን ጋር በስፖርት ስነልቦና ዙሪያ መድረኮች ቢመቻቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለውን የስነልቦና ክፍተት ለማረም እንደሚረዳ ዶክተር ሃብታሙ ያስገነዝባሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014