ሻምፒዮኗን አልጄሪያን ጨምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ገናና ስም ያላትን ጋናን ገና በጊዜ ከምድብ ጨዋታዎች ያሰናበተው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያልተጠበቁና ያልተገመቱ ክስተቶችን እያስተናገደ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ደርሷል።
በጊዜ ሄዶ በጊዜ ከተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ በአፍሪካ ዋንጫ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ አገራት ታላላቆቹን ጥለው የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ የሆኑበት የዘንድሮው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ከሃያ አራት አገራት ወደ አራት አገራት ፍልሚያነት ተቀይሯል።
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ አገራት ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሃያ አራት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ለመድረኩ እንግዳ የሆኑት ኮሞሮስ፣ጋምቢያና ሴራሊዮን የምድብ ጨዋታቸውን ከነጋናና አልጄሪያ በተሻለ በጀብድ ፈጽመው የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ የሆኑበት የአፍሪካ ዋንጫ ለታላላቆቹ አገራት ብቻ ሳይሆን ለዳኞች ጭምር ፈተና ሆኖ ታይቷል።
አርቢትሮች በርካታ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ከማሳለፍ ባለፈ በርካታ ቀይ ካርዶችን የመዘዙበት የዘንድሮ አፍሪካ ዋንጫ ገና ከጅምሩ ባሳዩት ደካማ አቋም የትም አይደርሱም የተባሉ አገራትን የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ አድርጎ አሳይቶናል።
በምድብ አንድ ከኢትዮጵያ፣ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድላ ይህ ነው የሚባል ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ያልቻለችው የውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ በአንጻራዊነት የተሻለች ሆና
በመቅረብ የግማሽ ፍጻሜውን ፍልሚያ ቀድማ መቀላቀል ችላለች። ለአፍሪካ ዋንጫው እንግዳ የሆነችው ጋምቢያ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቤልጂየማዊው ቶም ሴንትፌንት እየተመራች የውድድሩ ክስተት ብትሆንም በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ የማይበገሩት አንበሶችን መቋቋም ሳትችል ቀርታለች።
ይህም ካሜሩንን በቀላሉ በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት ዋንጫውን ለማስቀረት የምታደርገውን ግስጋሴ አሳምሮላታል። በዚህም ካሜሩን ነገ በግማሽ ፍጻሜ ግብጽን የምትገጥም ይሆናል። ፈርኦኖቹ ሞሐመድ ሳላን የመሳሰሉ የዓለማችን የወቅቱ ከዋክብት ተጫዋቾችን ይዘው በምድብ ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ ማሳየታቸው በውድድሩ ሩቅ ይጓዛሉ ተብሎ አልታሰበም ነበር። ይሁን እንጂ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ የሩብ ፍጻሜው ተፋላሚ ሆነዋል።
በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ ፈርኦኖቹ የገጠሟት ሞሮኮ የመጣችበት መንገድ የተሻለ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ ለዋንጫ ከታጩ አገራት አንዷ ነበረች። ይህም የፈርኦኖቹን ግስጋሴ ይገታል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር። ይሁን እንጂ ለመገመት አዳጋች የሆነው የዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ የሁለቱን የሰሜን አፍሪካ አገራት ጨዋታ ውጤት ወዳልታሰበ አቅጣጫ ወስዶታል።
በሁለቱ አገራት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የአትላስ አንበሶች የተገመቱትን ያህል ለፈርኦኖቹ ስጋት ሳይሆኑ ቀርተዋል። ምትሃተኛው የሊቨርፑል አጥቂ መሐመድ ሳላህ በነገሰበት የከትናንት በስቲያ ምሽት ፍልሚያ ፈርኦኖቹ የመቶ ሃያ ደቂቃ ፍልሚያውን በድል ተወጥተው የግማሽ ፍጻሜውን ትኬት ቆርጠዋል። በነገው ምሽትም ፈርኦኖቹ ለስምንተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ለማንሳት በሚጓዙበት መንገድ ለስድስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለመሳም ካሰፈሰፉት የማይበገሩት አንበሶች ጋር ተገጣጥመዋል። ሁለቱ አገራት ከአራት አመት በፊት ጋቦን አዘጋጅታው በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ተገናኝተው ካሜሩን ማሸነፏ አይዘነጋም።
ሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታና ያልተጠበቀ ውጤት ቡርኪናፋሶን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ሲወስድ ብዙ ተጠብቃ የነበረችው ቱኒዚያን በአጭር ያስቀረ ነበር። ቡርኪናፋሶ ኢትዮጵያ በነበረችበት ምድብ አንድ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳየች አገር እንደመሆኗ ቱኒዚያን ጥላ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ትሆናለች ተብሎ አልታሰበም ነበር።
ይሁን እንጂ የተሻለ ግምት የተሰጣትን ቱኒዚያን አንበርክካ ካለፉት አራት የአፍሪካ ዋንጫዎች በሶስቱ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ የሚያደርጋትን እድል እጇ ማስገባት ችላለች።
በዚህም ከነገ በስቲያ የቴራንጋ አንበሶቹን ሴኔጋልን በግማሽ ፍጻሜው ፍልሚያ የምትገጥም ይሆናል። የቡርኪናፋሶ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሴኔጋልም ከማንቸስተር ሲቲው የፊፋ የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ አንስቶ እስከ ሊቨርፑሉ የግብ ማሽን ሳዲዮ ማኔ ድረስ በከዋክብት የተሞላ ስብስብ ይዛ በምድብ ጨዋታ ተንጠልጥላ ማለፍ ብትችልም የኋላ ኋላ ግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሆናለች።
ሴኔጋል በዚህ አፍሪካ ዋንጫ አስደናቂ ጉዞ የነበራትን ኢኳቶሪያል ጊኒን ሶስት ለአንድ በመርታት የደከመች ብትመስልም በወሳኝ ጨዋታ የዋዛ እንዳልሆነች አሳይታለች።
ከነገ በስቲያ ሁለቱ አገራት ቡርኪናፋሶና ሴኔጋል ለዋንጫ ለማለፍ በሚያደርጉት ፍልሚያ ቡርኪናፋሶ እድል ከቀናትና ካሜሩንም ፈርኦኖቹን ማንበርከክ ከቻለች ታሪክ ራሱን ይደግማል።
ዋልያዎቹ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ እኤአ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ በተሳተፉበት ወቅት ለዋንጫ የደረሱት ከዋልያዎቹ ጋር በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበሩት ናይጄሪያና ቡርኪናፋሶ እንደነበሩ ይታወሳል። ዘንድሮም ካሜሩንና ቡርኪናፋሶ ለፍጻሜ የሚደርሱ ከሆነ ዋልያዎቹ ከነበሩበት አንድ ምድብ ተመሳሳይ አገራት ለፍጻሜ ደረሱ ማለት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014