የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን 11ኛውን የአፍሪካ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና ማዘጋጀቱ ይታወሳል። ለዓለም አቀፉ ቻምፒዮና አፍሪካን የሚወክሉ የሴት እና የወንድ ቡድንን ለመምረጥ እንደ ማጣሪያ በሚያገለግለው በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አልጄሪያ፣ ግብጽ ደቡብ አፍሪካ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተሳታፊዎች ነበሩ። ለአንድ ሳምንት በቆየው ውድድርም በደመቀ መልኩ ተካሂዶ በሳምንቱ መጨረሻ ተጠናቋል።
በውድድሩ በተለይ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ባታስመዘግብም ከፍተኛ ልምድ የተገኘበት መድረክ ነበር። የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ምክትል ፕሬዚዳንት እና የብሄራዊ ቡድኑ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሄኖክ ማስረሻም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ። ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት ስፖርቱን አስቀድመው የጀመሩት ሲሆን፤ በመሰል ውድድር ተሳትፎም ልምድ ያላቸውና የተሻለ ብቃት ያላቸው ናቸው። በአንጻሩ ስፖርቱ በኢትዮጵያ በአሶሴሽን ደረጃ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረና ቡድኑም በመሰል ቻምፒዮና ላይ ሲሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
በአጭር ጊዜ የአዘጋጅነት ዕድሉን ማግኘቱም እንደ ስኬት የሚቆጠርለት ነው። አሶሴሽኑ በዚህ ዕድሜው ስድስት ቻምፒዮናዎችን ሲያደርግ፤ በአህጉር አቀፉ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በመሆን በተሰጡ ስልጠናዎች አሰልጣኞች፣ የአካል ጉዳት ለዪዎች እንዲሁም ዳኞችንም ለማፍራት ችሏል። በቻምፒዮናዎቹ ላይ ሲሳተፉ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከልም ተመርጠው በአህጉር አቀፉ ቻምፒዮና ላይ ሃገራቸውን ሊወክሉ ችለዋል። በውድድሩም የታየው በሂደት እየተሻሻሉ እና ልምድ እያዳበሩ መምጣታቸውን መሆኑንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያመላክታሉ።
መሰል ዓለም እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲደረጉ ጎን ለጎን ስልጠናዎችን መስጠት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም አህጉር አቀፉ ፌዴሬሽን ለአራት አሰልጣኞች፣ አንድ የአካል ጉዳት ለዪ እና ኢንተርናሽናል ዳኞች (12 የጠረጴዛ እና 1የሜዳ ዳኛ) ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ስልጠናው በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ ሲሆን፤ ሁሉም በብቃት ማለፍ ችለዋል። ይህም ስፖርቱን ለማሳደግ እንዲሁም አገሪቷ በአፍሪካ ደረጃ ያላትን ሚና ልታሳድግ የምትችልበት ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት አላደገም። በመሆኑም እንደ ስፖርት ባሉ አካላዊ እንቅስቃሴ በሚፈልጉ ሁነቶች ላይ የሚኖረው ተሳትፎ አናሳ ነው። በመሆኑም ተሳታፊ እየሆኑ ያሉ ተጫዋቾች በምን መልኩ ስፖርቱን ይቀላቀላሉ ለሚለው ጥያቄ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ምላሽ አላቸው። የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት የአንድ አገር 16ነጥብ 85 ከመቶ የሚሆነው ዜጋ አካል ጉዳተኛ ነው። ይህም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከሕዝብ ቁጥሩ ከ16 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ማህበረሰብ አካል ጉዳተኛ ነው ማለት ነው። ይሁንና ለዚህን በርካታ ለሆነው ማህበረሰብ ትኩረት አልተሰጠም። በመሆኑም የተሳታፊዎች ቁጥርም አናሳ የሚባል በመሆኑ አሶሴሽኑ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ሌሎች ክልሎችም በስፖርቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመሆን ዊልቸር፣ የኳስ፣… ስጦታዎችን በማበርከት ጭምር ለማበረታታት ጥረት ይደረጋል። በዚህም እድገት እየታየበት ይገኛል።
አካል ጉዳተኝነት ነገሮችን በተለየ መንገድ መከወን መሆኑን ተከትሎ የስፖርት ቁሳቁሶችና የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ምቹ ማድረግ ይጠበቃል። ለአብነት ያህል በዚህ ስፖርት ለጨዋታ የሚያገለግሉት ዊልቸሮች ከተለመዱት የተለዩ ናቸው። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ካለው አቅም አንጻር ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የማይችል በመሆኑ በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ ይደረግለታል። አሶሴሽኑም በየክልሉ እንዲደርስ ያደርጋል። ሌላው ከማዘውተሪያ ስፍራዎች ጋር የተያያዘው ችግር ሲሆን፤ ይህ ውድድር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ተከትሎ ጂምናዚየም እና ተወዳዳሪዎች የሚቆዩባቸው ሆቴሎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸው በግልጽ ታይቷል። ውድድሩ የተካሄደበት የራስ ኃይሉ ጂምናዚየም መግቢያዎቹ እንዲሁም መጸዳጃዎቹ ለዊልቸር እንዲመቹ ለማድረግ አሶሴሽኑ በርካታ ስራዎችን መስራቱንም አቶ ሄኖክ ያስታውሳሉ።
አሶሴሽኑ ከሚጠበቅበት ስራ ባሻገር ስፖርቱን ለማሳደግ ከመንግስትና ሌሎች አካላት በርካታ ስራዎች ይጠበቃሉ። በመሆኑም አጋር አካላት አካል ጉዳተኞች ከማገዝ አንጻር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ የሚፈልጉ አካላት ወደ አሶሴሽኑ እንዲመጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014