እየተገባደደ ያለው የጥር ወር በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የተለመደ የሰርግ ወቅት ነው። በተለይም የመኸር አዝመራ በዚህ ወር ተሰብስቦ የሚያበቃት ነው። ይሄኔ ይህ አዝመራ በሚሰበስብባቸው አካባቢዎች ወሩ በጥጋብና በፍስሀ ያልፋል። እናም ወቅቱ የሰርግ ነው። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ልጅህ ለልጄ ተባብሎ አንድ የማድረጊያው ጊዜ በዚህ ወቅት ቢሆን ይመረጣል። ገበሬው የእረፍት ወቅቱ በመሆኑ የጎጆ መውጫው የልጆች መዳሪያ አድርጎታል። ይህ ልምድ ሰፊና እንደ አገር ከተሞች ላይም ተጋባ።
ጥር ሰርግ የሚበረክትበት ወቅት ሆነ። በዚህ ወር “ሙሽራዬ” የሚል ዜማ ይበረከታል። ተጣማሪዎች ወደ አንድ ጎጆ ለማቅናት በያዙት ቀጠሮ መሰረት ደምቀው ይታዩበታል። በሙሽራ ልብስ ይደመቃል። በተለይ ሙሽሪቷ በከተሞች በቬሎ፣ በገጠር በባህል አልባሳት ትንቆጠቆጣለች። ጎዳናዎች በሰርገኞች ጭፈራ በሙሽሮች ድምቀት ይዋባሉ። የመኪና ጥሩምቧ ተደጋግሞ ሙሽሮችን ለማጀብ ይሰማል። ሚዜዎች ተመሳሳይ ልብስ ለብሰው የእለቱ ንጉሶች ሙሽራና ሙሽሪትን አጅበው በሰልፍ ሲጓዙ ተደጋግሞ ይታያል። “ሙሽራዬ” ይዘፈናል አሁን ለመድሽ አበባዬ ይንቆረቆራል።
ወቅቱ ነውና በዛሬ ፋሽን አምዳችን ወቅታዊ የሆኑትን የሙሽራ አልባሳት የተመለከተ ፅሁፍ አሰናድተን ለእናንተ ልናደርስ ብዕራችንን አነሳን። በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ ቦታዎች የሙሽሮች እና የሚዜ ልብሶችን የሚሸጡ በአብዛኛውም የሚያከራዩ ሱቆች በርክተዋል። እነዚህ ሱቆች ለሙሽሮቹና ሚዜዎች በምን መልክና መንገድ እንደሚያቀርቡ አጠቃላይ በሙሽራና ሚዜ ልብሶች ላይ ባለው የገበያ እንቅስቃሴን አስመልክቶ አውርተናቸዋል።
ከሌሎቹ የከተማዋ ክፍሎች በተለየ 22 አካባቢ እጅግ በርካታ የሙሽሮችና የሚዜ አልባሳት መሸጫና ማከራያ ሱቆች ተሰልፈው ይገኛሉ። እኛም ወደነዚህ ሱቆች አምርተን የተወሰኑ ጥያቄዎች ለባለሱቆች አቀረብን።
ሜላት አየልኝ ትባላለች። በሙሽሮች እና ሚዜ አልባሳት ሽያጭና ኪራይ እንዲሁም ማስዋብ /ዲኮር/ ስራ ከ5 ዓመት በላይ ሰርታለች። ወሩ የሰርግ ወቅት ከሌሎች ወራት በተለየ ስራ የሚሰሩበት ነውና በሱቆቿ ውስጥ አዳዲስና ያማሩ ዲዛይኖች ሙሽሮች ሊመርጡዋቸው የሚያስችሉ የሚሽራ አልባሳት ቬሎና የሙሽራው ሙሉ ልብስ /በተለምዶ ሱፍ ይባላል/ በተለያየ አይነትና የጥራት ደረጃ አሰናድታ እንግዶችዋን እየጠበቀች ትገኛለች።
ለሰርግ ወቅት የሚሆኑ ሙሉ አልባሳትና ዲኮር አገልግሎት ትሰጣለች፤ በሽያጭና በኪራይ መልክም ለደንበኞቿ አልባሳትን ታቀርባለች። በሱቁዋ ውስጥ የሙሽሮችና የሚዜ አልባሳት በሰርግ ወቅት የሚያስፈልጉ የአበባና ልዩ ልዩ ማጌጫዎች እጅግ ባመረ መልኩ ተደርድረው ይገኛሉ።
የሰርግ ወቅት እንደመሆኑ ገበያው መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የምትናገረው ሜላት፣ ከሽያጭ ይልቅ በቀንና በሰዓታት ተከራይተው የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን የሚፈፅሙ ጥንዶች መበራከታቸውን ታስረዳለች።
በየዘመናቱ የዲዛይን ለውጦች እየተፈጠሩና ለሰዎች አይነ ግቡና እጅግ ውብ በሆነ መልኩ የተሰሩ በተለይ የሴት ሙሽራ አልባሳት እንደሚገኙና ሙሽሮችም በየዘመናቸው አዳዲስ ዲዛይኖች አምረው እንደሚሞሸሩ ታብራራለች። በሱቆቹ ውስጥ ያሉት የሙሽራ ቬሎዎች ከውጭ አገር ያስመጡዋቸው ናቸው።
እዚያው 22 ጎላጎል አካባቢ ባለው ሱቋ የሙሽራና የሚዜ ልብስ እንዲሁም የባህል አልባሳት በመሸጥና በማከራየት የምትተዳደረዋ ማያ በሪሁንም እንደሌሎቹ ሱቆች ወቅቱን ያገናዘበና ፋሽንን የተከተሉ የሙሽራ አልባሳት ለኪራይ አዘጋጅታ ደንበኞቿን እየተጠባበቀች ትገኛለች። በመሸጫ ሱቋ ውስጥ የሚገኙት ቬሎዎች ሙሉ በሙሉ የውጭ አገር መሆናቸውን የምትገልፀው ማያ፤ በአገር ውስጥ ለመስራት ቢሞከርም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር በተጠቃሚዎች እንደማይመረጥ ትናገራለች። የውጭዎቹ ይበልጥ በሙሽሮች እንደሚመረጡ ነው የምታስረዳው።
ሙሽሮች በኪራይ መልክ ሲመጡ እንደሚፈልጉት አገልግሎት የዋጋ ልዩነት እንዳለ የምትገልፀው ማያ፣ የሙሽራ ልብስ ወይም ቬሎ በኪራይ ከ10 እስከ 13 ሺ ድረስ ለ3 ቀን ክፍያ ትቀበላለች። ለፎቶና ለመስክ ደግሞ ከ2ሺ 500 እስከ 7ሺ ድረስ እንደ ቬሎው የኪራይ ተመን ወጥቶላቸው ተጠቃሚ ጋር ይደርሳሉ።
የሙሽሮቹ አልባሳት ከጊዜና ከወቅት ጋር የቅርፅ እና የዲዛይን ለውጥ አላቸው የምትለው ማያ፣ በአብዛኛው በአሁኑ ወቅት በሙሽሮች የሚመረጡ ፋሽን ቬሎ አልባሳት ለሰርግ ሲሆን እጀ ሙሉና የሆኑ ቬሎዎች ይመረጣሉ፤ የምትለው ማያ እነዚህ አልባሳት በነጭና ነጣ ባለ ክሬም መልክ የተዘጋጁ ወቅታዊ ፋሽን ቬሎዎች መሆናቸውን በሽያጭ እስከ 60 ሺ ብር ድረስ ገበያ ላይ እንደሚገኙ ታብራራለች።
ዲዛይነር ህሊና ይታየው ቀድማ ከጀመረችው የባህል ልብስ ዲዛይን ስራ በተጨማሪ ገቢዋን ለማሳደግና ይበልጥ ደንበኞቿ ጋ ለመድረስ በአሁኑ ወቅት አየር ጤና አካባቢ በሚገኝ ሱቋ ውስጥ ቬሎና ዲኮር ስራ በመስራት ላይ ትገኛለች። ለ2 ዓመታት በስራው ላይ የቆየችው ዲዛይነር ህሊና፣ የተለያዩ መርሀ ግብሮች የሚሆኑ የተለያየ አይነት ቬሎዎች፣ የሙሽራው ልብስ፣ የሚዜዎችና አጃቢዎች ልብስ በሱቋ ውስጥ በማዘጋጀት ለደንበኞቿ አገልግሎት ትሰጣለች።
እንደ የአካባቢውና ወቅቱ እንዲሁም የሙሽራ ልብሶቹ የጥራትና ተፈላጊነት መጠን የኪራይ ዋጋ ልዩነት አለ። ዲዛይነር ሄለን በራሷ ዲዛይን ተደርገው የሚዘጋጁ የአገር ባህል አልባሳትን ሙሽሮች ለመልስና ለእራት ግብዣ ለመልበስ እንደሚከራዩ ትገልፃለች።
እንደ ሌሎቹ ሱቆች ሁሉ በአገር ውስጥ የተሰራ ቬሎ አለመኖሩን የምትገልፀው ሄለን፣ ተጠቃሚዎች የሚመረጡት የውጭ አገር የሙሽራ አልባሳትን መሆኑን ነው የምትናገረው። ዲዛይነርዋ ከቬሎና ሙሉ የሰርገኞች አልባሳት ኪራይ አገልግሎት በተጨማሪ ባህላዊ አልባሳትንም በራሷ ዲዛይን በመስራት ለተጠቃሚዎች ታቀርባለች።
አሁን ላይ በተለምዶ ሙሽሮች ሙሉውን አገልግሎት በአንድ ስፍራ ማግኘት የሚፈልጉ መሆኑን የምትገልጸው ሄለን፣ እንደስዋ የምሽራ ልብስ አቅራቢ ሱቆች ውስጥ የአበባና ዲኮር ስራ ሙሉ የወንድና የሴት የሙሽራ አልባሳት እና ሌሎች አገልግሎቶች በአንድ ላይ የመስጠት ልምድ እየዳበረ መሄዱን ታስረዳለች። እርሷም ለደንበኞችዋ መሰል አገልግሎቶችን በአንድነት ታቀርባለች።
እንደ አልባሳቱ ዲዛይን አዲስነትና ተፈላጊነት በኪራይ የምታቀርባቸው አልባሳትም በሱቋ እንዳላት የምትገልፀው ዲዛይነሯ፣ የሙሽራ አልባሳት ለሰርግ ስነ ስርዓት ለስቱዲዮና ለመስክ የተለያየ የዋጋ ተመን እንዳላቸውም ነው የምታብራራው። ለሰርግ ስነስርዓት ኪራይ እስከ 7 ሺህ ለመስክና ለፎቶ መርሀ ግብር ደግሞ ከ2500 እስከ 4500 ድረስ እንደ አልባሳቱ የተለያየ የኪራይ ዋጋ ተተምኖላቸዋል ነው የምትለው።
እንደ ሙሽራዋ ምርጫ ለሰርግ ዘመናዊ የሆኑ እጅ ሙሉ ቬሎዎች በብዙዎች ተመርጦ እንደሚለበስና ለመስክ ሲሆን ደግሞ ስፓጌቲ ወይም መርሜድ ሻምፓኝ ሆኖ ተጎታች የቬሎ አይነት በበርካታ ሴት ሙሽሮች ተመርጠው የሚለበሱ የወቅቱ ፋሽኖች መሆናቸውን ትጠቁማለች።
በሱቆቹ ውስጥ የወንድ ሙሽራ ልብሶች በተጨማሪ የሴትና የወንድ ቤተሰብ የሰርግ አልባሳት፣ የሴትና የወንድ ሚዜዎች አልባሳት በኪራይና በሽያጭ መልክ ለደንበኞች የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የወንድና የሴት ሚዜ አልባሳት ከ500 ብር እስከ 1500 ብር ድረስ እንደ አልባሳቱ ጥራትና ፋሽንነት በኪራይ መልክ ለተጠቃሚዎች ይቀርባሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014