ፀሀይ መትቶን፣ በጉንፋንና ሌላ ህመም መነሻነት አሊያም በተለያዩ ምክንያቶች ለራስ ምታት ህመም ልንዳረግ እንችላለን። ታዲያ እንዲህ ሲያመን እረፍት በማድረግ፣ ቡና በመጠጣት፣ መድሃኒት በመውሰድና እንደየልምዳችን መፍትሄ የምንለውን በማድረግ እንድናለን። ከዚህ አልፎ ያልተሻለን ከሆነ ግን በአፋጣኝ ወደ ሃኪም እንድንቀርብ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ከዚያ ባሻገር የሚከሰተው ነገር ግን አስደንጋጭና ግራ አጋቢ ሊሆን እንደሚችል ከሰሞኑ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያሳያል።
የሉዚያና ነዋሪዋም ያደረገችው ይህንኑ ነበር፤ የ56ዓመቷ ኪም ዴኒኮላ የተሰኘችው ሴት በምትኖርበት አካባቢ በሚገኝ ቤተክርስቲያን በመጽሃፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ነበረች። ድንገት ግን ከፍተኛ የራስ ምታት ህመም ይገጥማታል፤ እይታዋም ደብዛዛ ስለሆነባት በአቅራቢያዋ የነበረውን ባለቤቷን ለእርዳታ ትጠራለች። ባለቤቷም ህመሟ አጣዳፊ መሆኑን በመመልከቱ ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ ያደርጋል። እነርሱ ባሉበት አቅራቢያ የነበሩት የዴንኮላ ጓደኞችም እየረዷት ነበር ጉዞ የጀመሩት፤ ከዚያ በኋላ ግን ራሷን ያወቀችው በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆና ነበር።
በድንገተኛ ወደ ሆስፒታል የገባችው ወይዘሮዋ ስትነቃ አንዲት ነርስ አብራት ነበረች፤ እናም ጥያቄዎችን አቀረበችላት። አስደንጋጩ ነገር የተከሰተውም ይሄኔ ነበር፤ ነርሷ «ያለንበትን ዓመተ ምህርትና ዕለት ታስታውሺዋለሽን?» በሚል ላቀረበችላት ጥያቄ ያገኘችው መልስ «1980» የሚል ነበር። በነገሩ ግራ የተጋባችው ነርስም ሌላ ጥያቄ አስከተለች፤ «አሁን ያሉት ፕሬዚዳንት ማን እንደሆኑ ታውቂያለሽ?» ወይዘሮዋም በእርግጠኝነት፤ «አዎ፤ ሮናልድ ሬገን ናቸዋ» ስትል ነበር የመለሰችላት። ይሄኔ ነርሷ አንድ ነገር በመረዳቷ ጥያቄና መልሷን አቆመች።
ከቆይታ በኋላም አንድ ሰው ታካሚዋ ወዳለችበት ክፍል ገባ፤ ዴኒኮላ ግን እያነባ ያለውን ሰው ተመልክታ አንድ ነገር እንደሆነ ገመተች እንጂ ለ17ዓመታት በትዳር የተጣመሩ ባለቤቷ መሆኑን ለማስታወስ አልቻለችም ነበር። እንዲያውም በእድሜ በብዙ ከእርሷ የሚበልጥ ሰው እንደሆነ ነበር የተሰማት። ምክንያቱ ደግሞ የ38ዓመታት ትውስታዋ በሙሉ ጠፍቶ ወደ18ዓመቷ መመለሷ ነው። አእምሮዋ እአአ ወደ1980 በመመለሱ ስለ ማግባቷና ሁለት ልጆች ስለ መውለዷ አንዳችም ነገር ማስታወስ አልቻለችም።
በነገሩ ግራ የተጋቡት ሃኪሞችም በቅርቡ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ አሊያም አደጋ ገጥሟት ይሆናል የሚል መላምት ላይ ቢደርሱም ወይዘሮዋ ግን አንዳችም ነገር አላስተናገደችም ነበር። በመሆኑም እጅግ አነስተኛና በብዙ ሰዎች ላይ ከማይከሰቱ የበሽታ ዓይነቶች በአንዱ የተጠቃች መሆኑን ይረዳሉ። «ከትውስታዋ የጠፋው ጊዜ በጣም ረጅም ነው፤ የምታውቀው በ1980ዎቹና 90ዎቹ ያሉትን ብቻ ነው። ይህ የረጅም ጊዜ መዘንጋት ደግሞ ያልተለመደ ነው» ሲሉ ዶክተር ታሻ ሻምሊን ገልጸዋል።
የወላጆቿን እንዲሁም የወንድሟን ሞት ከዚያም ባለፈ በአሻራ የሚሰሩ ዘመንኛ ስልኮችን፣ ኮሚፒዩተሮችን እና ፍላት ቴሌቪዥኖችም ለእርሷ አዲስ ነገር ነበሩ። በመሆኑም ቤተሰቦቿ ለአምስት ወራት ያህል ፎቶዎችንና ሌሎች ሊያስታውሷት የሚችሉ ነገሮችን በማሳየት ትውስታዋን ለመመለስ ሙከራ አድርገዋል፤ የተሳካላቸው ግን አይመስልም።
የግራ አጋቢው ህመም ተጠቂ የሆነችው ዴኒኮላ፤ «ቤተሰቦቼ ሞተዋል፤ ምን እና እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ የሚያስተምሩኝ ሌሎች ግን አሉ። ቢሆንም በ18ዓመቴ እንዴት ነው የእነርሱ እናት ልሆን የቻልኩት?» በማለት ከህመሟ እንዳላገገመች የሚያሳብቅ ገለጻ አድርጋለች። ወደ ውጪ ስትወጣም የምትመለከተውና የሚሆነው ነገር ግራ የሚያጋባት ሲሆን፤ «ትውስታዎቼ አልተመለሱም፤ ቢሆንም አዲስ ነገር መፍጠር እችላለሁ» ስትልም ተናግራለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
ብርሃን ፈይሳ
Hey! Do you know if they make any plugins to assist with
SEO? I’m trying to get my website to rank for some targeted keywords but
I’m not seeing very good gains. If you know of any please share.
Appreciate it! I saw similar blog here: Eco product