እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት ነበር፣ ጥሩ ነበር አይደል? ወይስ ሥራ፣ ጥናትና ቤተሰብን ማገዝ በዝቶባችሁ ነበር? ከሆነ ሁሉም ጥሩ ስለሆነ ቢበዛባችሁም አትበሳጩ። ደሞ’ም እኮ ሥራ በጣም ጥሩ ነው። በተለይ ለጤናና ሰውነት አያያዝ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ።
ስለሆነም ሁሌም ለሥራ መትጋት አለባችሁ። በእርግጥ የእናንተ ሥራ አሁን ጥናት ነው። በቃ፣ በደንብ አጥንቶ፣ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ፣ 1ኛ መውጣት። አይደለም እንዴ ልጆች? አዎ፣ የእናንተ ቀዳሚ ሥራ እሱ ነው። ልጆች ለዛሬው ጽሑፌ የሰጠሁትን ርእስ አይታችሁታል? በጣም ጥሩ።
አዎ፣ ከሌላው ጊዜ ለየት ይላል። ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የዛሬው እንግዳዬ እስከ ዛሬ ሳቀርብላችሁ ከነበሩት እንግዶቼ ሁሉ ለየት ያለና በጣም ጎበዝ ስለሆነ ነው። አዎ ልጆች ተማሪ በየነ ነገደ በጣም ጎበዝ ነው።
በተለይ ለዛፎችና አጠቃላይ እፅዋት ያለው ፍቅርና የሚያደርገው እንክብካቤ ለየት ያለ እንደነበር አይቻለሁ። እንዲሁም በትምህርት ቤቱ የተማሪ ፖሊስና የአካቶ ተማሪዎች አስተባባሪ ነው።
ታዲያ ጎበዝ አይደለም ልጆች? “በጣም ጎበዝ እንጂ ….” ስትሉኝ ሰማኋችሁ ልበል። ተማሪ በየነ ነገደ የበላይ ዘለቀ ቁጥር 2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። በየነ ነገደን፣ ልክ እንደ ጉብዝናው ሁሉ፣ አሁንም ለየት የሚያደርገው ጉዳይ አለው። ይህ ጉዳይ የ”አካቶ” ተማሪ መሆኑ ነው። ልጆች አካቶ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? አካቶ ማለት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት (አካል
ጉዳተኞች፣ የአእምሮ ችግር ያለባቸው …)፣ ከሌሎች ጤናማ ከሆኑት እኩዮቻቸው ጋር በአንድ ትምህርት ቤት በማካተት፣ ከፍላጎታቸውና ከዕምቅ ችሎታቸው ጋር የተጣጣመ ትምህርት እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው።
እነሱን የሚያካትት ፕሮግራም በማዘጋጀት ማስተማርም ነው። ወደ ፊት ደግሞ ሌሎች መፃህፍትን በደንብ ታነቡና “አካቶ” የሚለው ስያሜ ከዚህ የበለጠ ትርጉም ያለው መሆኑን ትረዳላችሁ፣ አይደል ልጆች? እናንተ እኮ ጎበዞች እንደ ሆናችሁ በደንብ አውቃለሁ። ታዲያስ፣ ተማሪ በየነ ነገደ በጣም ጎበዝ አይደል፤ አዎ፣ በጣም ጎበዝ ነው። የተለያዩ ጥያቄዎች ሁሉ ጠይቀነው በሚገባ ነው የመለሰልን።
“ስምህ ማነው?” ስንለው ሁሉ በሚገባ መልሶልናል። “ምንድን ነው የሚያስደስትህ?” ላልነውም “ዛፍ መትከል” (ስናነጋግረው አበቦችን እየተንከባከበ ነበር) በማለት መልሶልናል።
“አንተ ፖሊስ ነህ፣ እንዴት ነው ተማሪዎች ያስቸግራሉ እንዴ?” ብለነውም “አዎ ፖሊስ ነኝ፤ ተማሪዎች ጥሩ ናቸው። አያስቸግሩም። ከረበሹ ይቀጣሉ።” በማለት መልስ ሰጥቶናል። ልጆች፣ ስለ በላይ ዘለቀ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፣ የአካቶ ፕሮግራም ተማሪዎች ምንም አልነገርኳችሁም አይደደል፣ ይቅርታ።
አሁን ልንገራችሁ። የበላይ ዘለቀ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አካቶ ተማሪዎች በጣም ጎበዞች ናቸው። ይገርማችኋል የማይሰሩት ሥራ የለም። ከቀለም ትምህርታቸው በተጨማሪ ዛፍ ይተክላሉ፤ ሥዕል ይሥላሉ፤ የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ ምንጣፍ ወዘተ ሁሉ ይሠራሉ። ብታዩዋቸው የማይሠሩት ነገር የለም። መምህሮቻቸውን ሁሉ ይወዷቸዋል። ለምን መሰላችሁ የሚወዷቸው፣ ጨዋ ስለሆኑና ታታሪ ሰራተኛ፣ ጎበዝ ተማሪ ስለሆኑ ነው። ልጆች ስለ አካቶ ተማሪዎች ስነግራችሁ አንድ ያልነገርኳችሁ ጉዳይ ቢኖር የትምህርት ቤቶችና የመምህራን ጉዳይ ነው።
አዎ፣ አካቶ ፕሮግራምን ከመደበኛው ትምህርት ፕሮግራም ጋር አካትተው የሚሰጡና በላይ ዘለቀ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን የመሳሰሉ ትምህርት ቤቶች፤ እንዲሁም የአካቶ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መምህራን በጣም የሚመሰገኑና ወደ ፊትም ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው። በሁሉም ትምህርት ቤቶች እና መምህራን ዘንድ ይህ አይነቱ ተግባር በሥራ ላይ ሊውል ይገባል።
ምክንያቱም በአካቶ ጀምረው ጤናቸው የተስተካከለና በትምህርታቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በጣም ብዙ ልጆች አሉ። ማንኛውም ነገር በአግባቡ ከተያዘ፣ እንክብካቤና ክትትል ከተደረገለት ወደ ጤናማነት መመለሱ አይቀርም። አይደለም ልጆች፣ አዎ፤ ይመለሳል። ልጆች አንድ ሀሳብ አለኝ። ትቀበሉኛላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ።
ምን መሰላችሁ፤ በየአካባቢው፣ በየ ሰፈሩ … አካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆች አሉ። ታዲያ የእነዚህ ልጆች ቤተሰቦች ወይም አሳዳጊዎቻቸው በቃ አይድኑም፣ ትምህርትም መማር አይችሉም ወዘተ በማለት ተስፋ በቆረጠ ስሜት ወደ ትምህርት ቤት ወስደው አያስመዘግቧቸውም። ወይም እንዲማሩ አያደርጓቸውም። ከነጭራሹ ከቤት ሁሉ እንዲወጡ አያደርጓቸውም።
አያችሁ ልጆች፣ ይህ ስህተት ነው። ሊደረግ ሁሉ አይገባውም። በወላጆች አማካኝነት መደረግ ያለበት በአካባቢው የሚገኝ አካቶን የሚሰጥ ትምህርት ቤት ወስዶ ማስመዝገብ ነው።
ልጆች፣ ከዛሬ ጀምሮ በአካባቢያችሁ እንደዚህ አይነት ልጆች ካሉ ወላጆቻቸው ወስደው ትምህርት ቤት እንዲያስመዘግቧቸው ንገሯቸው። እሺ ልጆች፣ ወላጆቻቸውን ትምህርት ቤት ወስዳችሁ አስመዝግቧቸው ትሏቸዋላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ የዛሬ ልዩ እንግዳዬን ተዋወቃችሁልኝ አይደል? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ። የዛሬ ሳምንት በሌላ ፕሮግራም እስከምንገናኝ ድረስ ደህና ሁኑ ልጆች፣ ደህና ሁኑ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014