የአፍሪካ ዋንጫ በመጣ ቁጥር የአህጉሪቱ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ እንዳለፉት አመታት በውድድሩ ደብዛዋ ሳይጠፋ ብዙ የሚነገርላት ታሪክ ሰርታለች። በእግር ኳሱም አለም ጀግኖችን ፈጥራም በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ የተባለላቸው ታሪኮችን የሰሩ ኮከቦችን አበርክታለች።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሆነንም ከታሪካዊ ኢትዮጵያውያን ኮከቦች መካከል በአፍሪካ ዋንጫ ገናና ስም ያለውን ኢትዮጵያዊውን የእግር ኳስ ንጉስ በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ለማንሳት ወደድን። ‹‹የእግር ኳሱ ንጉስ›› መንግስቱ ወርቁ በተለይ ከሚታወስባቸው ታሪኮች መካከል በ1954 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተከናወነው የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታነሳ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑ ነው።
እስከ 1998 ዓ.ም. በተደረጉት የአፍሪካ ዋንጫዎች አስር ግቦችን በማስቆጠር እስካሁን ድረስ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ግቢ አግቢ በመባል የሚታወቅ ኮከብ ተጫዋችም ዛሬ ላይ በመድረኩ ከነገሱት የሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ አገራት ሳይሆን ተሳትፎ ብርቅ ከሆነባት ኢትዮጵያ ነው የተገኘው። ይህም ተጫዋች ታሪካዊው መንግስቱ ወርቁ ‹‹የእግር ኳሱ ንጉስ›› ነው።
በአፍሪካ ዋንጫ ከ2ኛው እስከ 7ኛው ድረስ በአጥቂ መስመር ተሰልፎ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል። 98 ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ 68 ጐሎችን አስቆጥሯል። በኢትዮጵያ በተዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መንግስቱ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ከመመረጡም በተጨማሪ በፍጻሜው ጨዋታ በግብጽ ብሄራዊ ቡድን ላይ 4ኛውን ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያ የዋንጫው ባለቤት እንድትሆን ለቡድኑ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። መንግስቱ ወርቁ ከወርቃማ የተጫዋችነት ዘመኑ
ባሻገር በአሰልጣኝነት ዘመኑ በርካታ ክለቦችንና ብሔራዊ ቡድኑንም ጭምር በማሰልጠን ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንድትሳተፍ ያደረገና በአፍሪካ ደረጃም የአሰልጣኞች አሰልጣኝ እስከ መሆን ደርሷል።
መንግስቱ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሰለፈ የጀመረው በ1951 ዓ.ም በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ ነው። ለአስራ ሶስት ዓመታት ከ1951 እስከ 1963 ዓ.ም ዘጠና ስምንት ጊዜ ለብሄራዊ ቡድን ተሰልፎም ተጫውቷል። ስልሳ አንድ ግቦች ለብሄራዊ ቡድኑ በማስቆጠርም ለረጅም ዓመታት ክብረወሰኑን ይዞ ቆይቷል።
መንግስቱ በ1954 ዓ.ም. በኢትየጵያ በተከናወነው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሶስት ግብ በማግባት ከግብጹ አብዱልፈታ በዳዊ ጋር የኮኮብ ግብ አግቢነት ክብር አግኝቷል። እስከ 26ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስም 10 ግብ በማግባት የሚስተካከለው አልተገኘም።
በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ የስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሲያነሳ ተክሌ፤ ጌታቸውና ኢታሎ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3ለ 2 የግብጽ ቡድንን እየመራ የነበረ ቢሆንም የአንድ ግብ ልዩነት ስለማያስተማምን ተመልካቹ እጅግ በተጨነቀበት ሰዓት መንግስቱ አራተኛውን ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያ በታሪኳ የአፍሪካ ዋንጫ እንድታነሳ በማድረጉ ሁሌም ይታወሳል።
መንግስቱ በመጨረሻ የጨዋታ ዘመኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹ላሳደገኝና ለወደደኝ ሕዝብ ውለታውን ሳልመልስ ከኳስ ተጫዋችነት መገለሌ እየጸጸተኝ ነው። ነገር ግን አገራችን ጥሩ ተጫዋቾች እንዲኖሯት በአሰልጣኝነትና በአማካሪነት ለማገልገል ከመጣር አልቦዝንም›› ብሎ ነበር።
የእግር ኳስ ችሎታና ልምድ ብቻውን ጥሩ አሰልጣኝ እንደማያደርግ የተረዳው መንግስቱ ፊፋ በ1965 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ተካፍሎ አንደኛ በመሆን አጠናቋል፤ በ1968 ዓ.ም በግብጽ አሌክሳንደሪያ ፊፋ በሰጠው የአሰልጣኝነት ስልጠናም አንደኛ በመውጣት ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተቀብሏል፤ በ1969 ዓ.ም በምእራብ ጀርመን የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ለአራት ወር የተሰጠውን ስልጠና ከፍተኛ ውጤት በማግኘት አጠናቋል።
በ1970 ዓ.ም በጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ዲአፍሪካ ስፖርት ኮሌጅ በተሰጠው ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ትምህርት ተከተትሎ በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል፤ በ1972 ዓ.ም ፊፋ ኮካኮላ አካዳሚ በኬንያ ባዘጋጀው የአሰልጣኝነት ስልጠናም አንደኛ በመውጣት የብር ዋንጫ ተሸልሟል።
መንግስቱ በክለብ ደረጃ ካሰለጠናቸው ቡድኖች አንጋፋውና ያደገበት ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ መብራት ሐይል፤ ኢትዮጵያ መድህን ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህን ክለቦች በያዘበት ወቅት ባስመዘገባቸው ውጤቶችና የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን በሰራው ስራ የተዋጣለት አሰልጣኝ መሆኑን አስመስክሯል።
መንግስቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማሰልጠን የጀመረው በ1968 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ነበር።
በ1973 ዓ.ም ሊቢያ ለምታዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሚጫውተውን ቡድን የማዘጋጀት ኃላፊነት በዋና አሰልጣኝነት ተረከበ። በወጣቶች የተገነባ ቡድን የፈጠረው መንግስቱ በ1973 ዓ.ም ባደረጋቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ከአገር ውጪ በሶስቱ ሲያሸንፍ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቶ ያለሽንፈት ጨረሰ።
በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያው ማጣሪያ በደርሶ መልሱ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር እኩል ነጥብ በማግኘታቸው በተሰጠው የመለያ ምት የኢትዮጵያ ቡድን 5-4 አሸንፎ ወደቀጣዩ ዙር አለፈ። በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በወቅቱ በምዕራብ አፍሪካ በኳስ የሚታወቀውን የጊኒን ብሔራዊ ቡድን ኮናክሪ ላይ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2-2 ተለያየ።
ሁለቱ ግቦች የተቆጠሩበት ሴኒጋላዊው ዳኛ ለጊኒ አላግባብ በሰጡት ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮናክሪ ላይ ባሳየው የጨዋታ የበላይነት 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማንሳት ተስፋ እንዳለው ብዙዎች ተነበዩ። ይሁንና ስድስት ተጨዋቾች ከቡድኑ ተለይተው በመቅረታቸው አዲስ አበባ ላይ የመልስ ጨዋታ የሚጠበቀውን ቡድን እንደገና ማዘጋጀት ግድ ሆነ።
መንግሰቱ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ያዘጋጀውን ቡድን ይዞ ጥቅምት 22 ቀን 1974 ዓ.ም ከጊኒ ቡድን ጋር ባደረገው ጨዋታ 1-1 በመለያየቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ከሆኑት ስምንት አገሮች አንዱ ሆነ። በሊቢያ ቤንጋዚ ከተማ ተመድቦ የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ12ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በወሰደው ናይጄሪያ 3-0፤ በዛንቢያ 1-0፤ ከአልጀሪያ ጋር 0-0 በመለያየት ከውድድሩ ቢወጣም ስድስት ቋሚ ተሰላፊዎቹን ያጣ ቡድን እንደመሆኑ ያስመዘገበው ውጤት አስከፊ የሚባል አልነበረም።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ፤ ስሙ ከኳስ ጋር ሁሌም የሚጠራው መንግስቱ ወርቁ፤ በተወለደ በ70 ዓመቱ እኤአ በ2010 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የአፍሪካ ዋንጫ በመጣ ቁጥር ግን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እግር ኳስ ባበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ሲታወስ ይኖራል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014