የታሪክ መዛግብት እያጣቀስን ከትውስታ ማህደራችን እየቀነጨብን በየሳምንቱ ወደ እናንተ በምናደርሰው የታሪክ ትውስታችን ዛሬም አንድ ታሪክ ለመዘከር በዚህ ገፅ ላይ ብዕራችንን አሳረፍን።
በያኔዋ የኢትዮጵያ ግዛት፤ በአሁኗ የኤርትራ ምድር ከምጽዋ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዶጋሊ/ በአካባቢው አጠራር ተድአሊ እንደሚባል መረጃዎች ያመለክታሉ/ በዚህ ሳምንት ጥር 17 ቀን 1879 ዓ.ም /ቀኑ በተለያየ ቀን ተብሎ ስለተፃፈ ሦስተኛው ሳምንት ያስማማናል/ አንደ ገድል ተፈጸመ።
በጥር ወር ሦስተኛው ሳምንት የዛሬ 135 ዓመት ኢትዮጵያ ከጣልያን ወራሪ ሀይል ጋር ገጥማ በዶጋሊ የጦር ሜዳ ውሎ ድል ተቀዳጀች። እአአ 1854 ጣልያኖች ከውህደታቸው በኋላ በአፍሪካ የራሳቸውን ቅኝ ግዛት የመያዝ ፍላጎት ስለነበራቸው የኤርትራን ጠረፋማ አካባቢዎች መያዝ ጀመሩ፤ ዘግይቶም በ1878 ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ገጠሙ።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 በሚለው መጽሐፋቸው ጣልያኖች ምጽዋን ከእንግሊዝ እንደ ገጸ በረከት ካገኙ በኋላ እዚያው ሐሩራዊ የባህር ጠረፍ ላይ ዝም ብለው ከመቀመጥ፤ ወደ ደጋው ክፍል ግዛታቸውን ለማስፋፋት ተጣደፉ።
ተለያይተው የነበሩት የጣልያን ግዛቶች ተዋሕደው በአንድ መንግሥት ሥር መተዳደር የጀመሩት በ1863 በመሆኑ የኢጣልያ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የአፍላ ጎረምሳን ትኩስ ስሜት የሚያንፀባርቁ ነበሩ።
መጣደፉ የመጣውም እንደ እንግሊዝና ፈረንሳይ ያሉ የደረጁ ቅኝ ገዥዎች ዓለምን ተቀራምተው ሲንሠራፉ እኔ ከዚህ ቡራኬ ሳልቋደስ ጀምበር ትጠልቅብኛለች የሚል ስጋት ነው።
ጣልያን ጥረቷ ሁሉ መና እንዳይቀር እንግሊዝን የመሰለ አጋር ጣለላት። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት የሌላት ጣውንቷ ፈረንሳይን ግን ለማገድ የምትፈልገዋ እንግሊዝ
ኢጣልያንን ተጠቅማ ጥቅሜን ታስከብርልኛች በሚል ስሌት ማደፋፈር ቀጠለች። በወቅቱ ዘይላና በርበራ በእንግሊዞች ፣ ታጁራ በፈረንሳይ፣ አሰብና በኋላ ምፅዋ በኢጣልያ ሥር ነበሩ። ልዩነቱ ግን ፈረንሳይና እንግሊዝ ሶማሌ ላንድ ተብለው በሚታወቁት አገሮች ሲታገሱ የኢጣልያ ዐይን ወደ ኢትዮጵያ ማማተሩ ነበር።
ጣልያኖች ሰሐጢና ዊአ የሚባሉ ከጠረፍ 20 ኪሎ ሜትር ገባ ያሉ ቦታዎችን ይዘው ነበር፤ ዐፄ ዮሐንስ ጣልያኖቹ ምጽዋን በመያዛቸው ቢከፉም፣ ታግሰው ይቀመጣሉ የሚል ከንቱ ተስፋ አድሮባቸው እንደ ነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የመረብ ምላሽ ገዥ ራስ አሉላ ጣልያኖች የያዙትን የኢትዮጵያ ምድር እንዲለቁ ለኢጣልያው አዛዥ በተደጋጋሚ ቢጽፉም ከቁም ነገር አልቆጠረላቸውም።
የደብዳቤው ልውውጥ ውጤት አልባ መሆኑን ያዩት አሉላ ፈረሳቸውን ጭነው ጥር 20 ቀን 1879 ዓ.ም ሰሓጢ መሽጎ በተቀመጠው የጣልያን ጦር ላይ ዘመቱ። ሆኖም መሽጎ የሚዋጋን ጦር ማጥቃቱ ቀላል ባለመሆኑ አሉላ ብዙ ሰው ካለቀባቸው በኋላ አፈገፈጉ።
በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎቻቸው የተገደሉ ሲሆን፤ ከጣልያንዎቹ ወገን አራት ሰዎች ብቻ ናቸው የቆሰሉት፤ በዚህም አሉላ የተረፉትን ተዋጊዎቻቸውን ይዘው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ተገደዱ።
በማግስቱ ግን ተዋጊዎቻቸው የሰሐጢውን ጦር ለመርዳት ከምፅዋ የተላከው 500 ገደማ ሠራዊት ያለበትን የኢጣልያን ጦር ዶጋሊ ላይ ገጥመው ዶግአመድ አደረጉት።
የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በ1950ዎቹ በጣሊያን ሲካሄድ ኢትዮጵያዊ አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ እንዳሉት፤ አሉላ ሰሐጢ የነበረውን የጣሊያን ጦር ጭፍራን ከበውት ሳለ ለእርዳታው ከምፅዋ ይጓዝ የነበረውን የአምስት መቶ ወታደሮች ጭፍራ ተዳዕሊ (ዶጋሊ) በተባለው ኮረብታ ላይ ከበው ጨረሱት።
የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ጦርነቱ የ15 ደቂቃዎች ብቻ ሆነ። በራስ አሉላ ሰዎች በሰሀቲ መልሶ ማጥቃት 500 ጣልያኖች ከ7ሺ ኢትዮጵያውያን ጋር ቢዋጉም በጦርነቱ ከቆሰሉ ስምንት ሰዎች በስተቀር ሁሉም መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያውያን በዶጋሊ ላይ የተቀዳጁት ድል ዜና በኢጣልያ አገር በተሰማ ጊዜ ታላቅ ሽብር ፈጠረ።
የበቀል ጩኸት በኢጣልያ ጎዳናዎችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካባቢ ተሰማ። የኢጣልያ ፓርላማ ለምፅዋና ለአካባቢው መከላከያ ማጠናከሪያ የሚውል ሃያ ሚሊዮን ሊሬ በጀት መደበ። ሌሎች እርምጃዎችንም ወሰደ።
ጣልያን ለእነዚህ ለተሰው ወታደሮቿ በሀገሯ ሀውልት አቁማለች። ከሮም ጎዳና የአደባባይ ሀውልቶች አንዱም ይሄው በ”ፒያዛ ዴ ቺኴንቶ” የተባለው ሀውልት ነው፤ የአምስት መቶዎቹ አደባባይ ማለት ነው፤ በሐውልቱ ላይ ለዶጋሊ ጀግኖች የሚል ትርጉም ያለው ጽሁፍ በኢጣልያንኛ የተጻፈበት መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህን ድል ሲያስቡት ኖረዋል። ከዚህ የጦር ሜዳ ገድል ጋር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ገድሎችም ራስ አሉላ ይታወሳሉ።
ዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያ ራስ አሉላ አባ ነጋ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ጀግና (Ras Alula Abba Nega: An Ethiopian and African Hero) በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው የራስ አሉላ የጦር ሜዳ ጀግንነትና የአመራር ክህሎት የተረጋገጠው እ.ኤ.አ. በኅዳር 18 ቀን 1875 እና በመጋቢት 1876 በጉንደትና በጉራዕ በቅደም ተከተል በተካሄደ ጦርነት ነው ይላሉ። በነዚህ ጦርነቶች ግብጻውያን ተጠራርገው ተደምስሰዋል።
ራስ አሉላ በዚህም ጦርነት ለፈጸሙት ጀግንነት የ35 ዓመት ጎልማሳ ሆነው የራስነት ማዕረግ በዐፄ ዮሐንስ ያገኙ ሲሆን ዘግይቶም ቱርክ ባሻ የሚል ማዕረግ ተጨምሮላቸዋል። ስያሜውም የተሰጣቸው በወቅቱ በነበረው የባህር ጠረፍ አካባቢ የሚያንዣብቡትን የቱርክ ኃይል ይመክታል በሚል እምነት ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014