ፍጥነትና ቅልጥፍናን ከሚፈልጉ ስፖርቶች መካከል አንዱ ስፖርት ነው። በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች የተለመደ መዝናኛ ሲሆን፤ እንደ ስፖርት እንቅስቃሴ ሲታይ ግን የተቀዛቀዘ የሚባል ነው፤ የጠረጴዛ ቴኒስ።
ይሁንና በጥቂት ክለቦች የተያዙ ስፖርተኞች በጥረታቸውና በግል ውጤታቸው በምስራቅ አፍሪካ የተሻለ ብቃት እንዳላቸው አስመስክረውበታል። በውጤታቸው ኢትዮጵያን ጭምር እያስጠሩ ካሉት የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርተኞች መካከል አንዷ ማርታ መሸሻ ናት፤ ማርታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ የጠረጴዛ ቴኒስ አሰልጣኝና ተጫዋች፣ በምስራቅ አፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ማህበር ስራ አስፈጻሚ አባልና የስፖርተኞች ተወካይ ናት።
እንደ ዘበት የጀመረችውን የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ ከማዘውተር አልፋ ወደ ስፖርተኝነት በመግባት አሁን ካለችበት መድረሷን ትናገራለች። በተለያዩ ውድድሮች ተሳታፊነትም በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ተጫዋች ለመሆን በቅታለች።
አሁን በአሰልጣኝነት እያገለገለች ሲሆን፤ ለሁሉም ክፍት በሆነ ውድድር በተወዳዳሪነትና በአሰልጣኝነት ተሳታፎ ታደርጋለች። በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ውድድር ላይም ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።
ይህ የረጅም ጊዜ ልምዷም ለምስራቅ አፍሪካው ማህበር ኢትዮጵያን የምትወክል አባል እንድትሆን አድርጓታል። በየዓመቱ በውድድሮች ላይ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶችና ተሳትፎዎች ሊያስመርጧት መቻላቸውን ነው ማርታ የምትገልጸው። በአሰልጣኝነቷ እንዲሁም በተጫዋችነቷ ለአገር
ከምታበረክተው ጠቀሜታ ባለፈ የማህበሩ አባልነቷ በቁሳቁስ፣ በስልጠና እና ሌሎች በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ እድሎች ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል። ለኢትዮጵያ እውቅና እንዲሰጥ ከማድረግ ባለፈ በስፖርቱ በኩል ያሉ ችግሮችንም በማሳየት መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችል መድረክም ነው። ማርታ እንደምትለው፤ በርካቶች ወደ ስፖርቱ የሚገቡት ለመዝናኛ ብለው ነው፤ ትኩረት ቢሰጠውና በታዳጊዎች ላይ በትኩረት ቢሰራበት አገሪቷ ውጤታማ ልትሆንባቸው ከምትችላቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ እንደሚሆንም እምነቷ ነው።
ስፖርቱ በርካታ የሰው ኃይል የማይፈልግ መሆኑን ተከትሎም ተቋማትና ባለሃብቶች ቢያተኩሩበት ከምስራቅ አፍሪካም አልፎ በአፍሪካም ጭምር ተፎካካሪ ለመሆን እንዲሁም ለኦሊምፒክ ለማለፍ የሚያስችል እድል አለ።
ስፖርቱ በዋናነት የቁሳቁስ፣ የትኩረት፣ የሰው ኃይል ችግር ያለበትና ስፖርተኞቹም በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚያልፉ መሆናቸውን ማርታ ጠቅሳ፣ በውድድር ላይ ግን በተፎካካሪዎቻቸው አድናቆት እንደሚቸራቸውም ትጠቁማለች። ከተሰራበት ግን በቀላሉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ታረጋግጣለች።
እርሷ ያለችበት የንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ይታወቃል።
ጠንካራ ክለብ ሲሆን፤ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ጂምናዚየም በመገንባትም ጭምር ይደግፋል። የጠረጴዛ ቴኒስ ከሌሎች ስፖርቶች እኩል ትኩረት እንደሚሰጠው ትጠቅሳለች። ሌሎች የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ክለብ በማቋቋም ስፖርቱን በጥቂት ገንዘብ በመደገፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ትጠቁማለች። ‹‹ሌሎች አገራት ጥለውን ከሄዱ በኋላ እነሱ ላይ ለመድረስ ብዙ ጥረት ውስጥ ከምንገባ ከወዲሁ መስራት ይገባናል›› ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014