ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‹‹ስለ ኢትዮጵያ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ›› አዘጋጅቶ ለህዝብ እይታ ክፍት ማድረጉ ይታወሳል።
ይህን፣ ከታህሳስ 25 እስከ ጥር 12/2014 ዓ.ም ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ የቆየውን አውደ ርእይ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የጎበኙት ሲሆን ወጣቶችም የእነዚሁ ጎብኝዎች አካል ነበሩ።
የመከላከያ ኃይሉ የከፈለውን ውድ የህይወት መስዋዕትነትና አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የፈጸመውን ቁሳዊና ሰብዓዊ ጉዳት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግ የአውደ ርዕዩ ቀዳሚ ዓላማ ነበር።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞቹን ግንባር ድረስ ልኮ ወቅታዊ መረጃን ለህዝብ ከማድረስ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት የፎቶግራፍ አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ነባራዊውን እውነት ለህዝብ ለማሳየት ጥሯል። ‹‹ስለ ኢትዮጵያ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ››ም የዚህ አካል ነበር።
‹‹ስለ ኢትዮጵያ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ›› በድርጅቱ ኤግዚቢሽን ማእከል (አ.አ) ለተመልካቾች ክፍት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖች፣ አርቲስቶች፣ ዲያስፖራዎች፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ ወጣቶች በአጠቃላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለተከታታይ አስራ ሰባት ቀናት ሲጎበኙት ሰንብተዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅቱ አውደ ርዕዩን ሲጎበኙ የነበሩ ወጣቶችን እንግዳ አድርጓል። ወጣቶች “ከአውደ ርዕዩ ምን ተማሩ? ባዩት ነገር የተሰማቸው ስሜት ምንድ ነው? የአውደ ርዕዩንስ አስፈላጊነት እንዴት ይመለከቱታል?” በሚሉትና በሌሎችም መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት ሰጥተዋል። በቅድሚያ ያነጋገርነው ወጣት ቃለአብ ብዙነህ ይባላል። በመዲናዋ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀውን የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በተለያዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሲቀርብ ተመልክቶ የማየት ጉጉት እንዳደረበት ይናገራል። ቃለአብ በግል ትምህርት ቤት በሰዓሊነት የሚሠራ ወጣት ነው። ሙያው ከፎቶግራፍ ጥበብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንዲህ አይነት አውደ ርዕዮችን መመልከት እንደሚያዘወትር ይገልጻል።
“ስለ ኢትዮጵያ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ”ን ከተመለከተ በኋላ ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ ስሜቱን ቆንጥጦ የያዘው የፎቶግራፉ ጥበብ ሳይሆን ከፎቶ ግራፉ ጀርባ ያለው ታሪክ እንደሆነ ያስረዳል። የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደት፤ እንዲሁም የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር ያደረሳቸውን ቁሳዊና ሰብአዊ ጥፋቶች በተጨባጭ የሚያስቀኝ እንደሆነ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ላይ ቆሞ የአሸባሪው ሕወሓትን ቡድን ጥቃት ለመመከት ያደረገውን ተጋድሎ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦችን ተጽዕኖ ለመመከት የተደረገውን ዓለማቀፍ ንቅናቄ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ግንባር ድረስ ገብተው በማዋጋት ያስመዘገቡትን ድልና የጥምር ኃይሉን ውጤታማነት ፎቶ ግራፎቹ ይናገራሉ ይላል። በንጹኋን ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ የህጻናት፣ የእናቶች እና የአያቶች መደፈርን፣ የወደሙ ፋብሪካዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ከሰማው በላይ በፎቶግራፎቹ የጉዳቱን መጠን እንዳየ ይገልጻል።
በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ጀብድ የፈጸሙ ግለሰቦች፣ ጥምር ሃይሉ የአሸባሪው ሕወሓትን ምሽጎች እየሰባበረ ከተሞችን ነጻ ያወጣበትን ፍጥነት፣ ተፈናቃዮች ሲፈናቀሉና ወደ መንደራቸው ሲመለሱ ፊታቸው ላይ የሚታየው ብርታትና ጽናትን፣ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ፣ ፎቶ ግራፎቹ በውስን ሰዓት ውስጥ የአንድ ዓመቱን እውነታ ሳይበጣጠስ በቅደም ተከተል ይዘው የቀረቡ መሆናቸውን ቃለአብ በአግራሞት ይናገራል።
ቃለአብ ፎቶግራፎቹን ሲመለከት ዝብርቅርቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደነበር ይገልጻል። አንዳንዶቹ የሀዘን፣ አንዳንዶቹ የመገረም፣ አንዳንዶቹ የሀፍረት፣ አንዳንዶቹ የንዴትና የቁጭት ስሜቶችን ፈጥረውበት እንደነበርም ተናግሯል።
ለአብነትም መከላካያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት እንዳናደደው እና እንዳስቆጨው፣ የተደፈሩ ህጻናትንና እናቶችን ፎቶግራፍ ሲመለከት እንዳሳፈረውና ማመን እንዳቃተው፣ በተለይም ወላጆቹ ትተውት ሄደው ወታደሩ ታቅፎ ይዞት የሚዞረው ህጻን ልጅ ታሪክ አሳዛኝ እንደሆነበት ገልጿል።
በግፍ የተገደሉ ንጹኋንን ሲመለከት ልቡ በሀዘን እንደተሰበረ፤ ጥምር ጦሩ ምሽጎችን እየሰበረ ከተሞችን ነጻ ሲያወጣና የተለያዩ ግለሰቦች የፈፀሟቸውን ጀብዶች ሲመለከት ደግሞ ደስታና ኩራት ይሰማው እንደነበር ነግሮናል።
የቁርጡ ቀን ሲመጣባቸው ቤት ንብረታቸውን ትተው ከጠላት ጋር የሚፋለሙ ግለሰቦች የሚሠሯቸው ጀብዶችም የኢትዮጵያውያን መገለጫ ናቸው ይላል። ቃለአብ አሁን ያለው ወጣትም ይሁን መጪው ትውልድ ከፎቶግራፎቹ የሚማሯቸው በርካታ ቁምነገሮች እንዳሉ ይናገራል። እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ያደረጓቸውን ተጋድሎዎች የአሁኑ ትውልድ በአመዛኙ የተረዳው ከተጻፉ ጽሁፎች ነው ያለው ቃለአብ፣ በዚህ አንድ ዓመት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተፈጸመውን ጥቃት በምስል አስቀርቶ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ትልቅ ዋጋ እንዳለውም ተናግሯል።
ጦርነቱ የእርስ በእርስ እንደመሆኑ የአገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን የገለጸው ቃለአብ መንግሥት ተገዶ በገባበት ጦርነት ወድመው ያያቸው ከባድ መሳሪያዎች ትናንት በሰሜን እዝ ሰራዊት እጅ የነበሩና ከፍተኛ ዋጋ የወጣባቸው ናቸውም ብሏል። እንደወጣት ቃለአብ አስተያየት ‹‹በጦርነት የሚጠቀም አካል የለም።
የሚጠቀመው የጦር መሳሪያ የሚሸጠው አካል ነው። በእርግጥ መንግሥት እንዲህ አይነት ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ የሰላም አማራጮችን ሲሞክር እንደነበር የሚታወስ ነው። አገራችን በተፈጥሮ የታደለች ነች።
ያልተጠቀምንበት እምቅ ሃብት አለን። መግባባት ብንችልና ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ልምድ ቢኖረን በአጭር ጊዜ ማደግ የምንችል ነን። ከጦርነት ውድመት እንጂ ልማት እንደማይገኝ ተምረናል። ይህን ስል ግን መንግሥት የወሰደው ርምጃ ትክክል አልነበረም ማለቴ አይደለም። መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና ህግ የማስከበር ሃላፊነት ስላለበት ነገም ቢሆን ተመሳሳይ ርምጃ ሊወስድ ይችላል። ፍላጎታቸውን በጠመንጃ አፈሙዝ ማስፈጸም የሚፈልጉ አካላት ግን ቆም ብለው ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ ፍላጎት አላቸው፤ እንዲህ አይነቱን የእርስ በእርስ አለመግባባት በማጦዝ መጠቀሚያ ለማድረግ ይፈልጋሉ። በፎቶ አውደ ርዕዩ እንደተመለከትነው የውጭ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞቻቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያስተላልፉት የእነዚህን አካላት ፍላጎት ለማስጠበቅ ነው። ስለዚህ መለያየታችን ለውጭ ጠላቶቻችን ደስታቸው እንደሆነ በሚገባ ተረድተናል። ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ካልተያዙ የአፍሪካ አገራትአንዷ ነች።
ይሄ ታሪኳ የሚቀጥል መሆን አለበት። ወጣቱ ዛሬ የአገሩን ሉዓላዊነት ማስከበርና የውጭ ጣልቃ ገብነትን መመከት ካልቻለ ወደ ፊት ነጻነት የሚሰማው ትውልድ አይኖርም። ስለዚህ አንድ ሆነን መቆም በሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን። ጦርነት የኋላ ቀርነት አንዱ መገለጫ ነው። አገር ከሌለች ማንም አይኖርም፤ አንድ ወጣት የሚኖርባትን አገር ለማፍረስ ከሚፈልጉ ሃይሎች ጋር ተባባሪ ሲሆን ያሳፍራል።
ይልቁንም ወጣቱ የጥፋት ተልእኮ ካነገቡ አካላት ጋር ከመተባበር የራሱን ህይወት ለመቀየር አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚሄደበትን አማራጭ መፈለግ ነው ያለበት። ከአውደ ርእዩ ማለትም ከፎቶ ግራፎቹ እንደተረዳውት የትግራይ ወጣቶች ካለማወቅ ወይም በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ምክንያት ውጊያ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። አንዳንዶቹም ጦርነቱ እራስን ከጠላት መከላከል እንደሆነ ተሰብከው በተነገራቸው መሰረት የሚዋጉ ናቸው። ምርኮኞች ምግብ ሲሰጣቸው አንበላም ሲሉ የነበረው እኮ አንድ የተነገራቸው ነገር በጭንቅላታቸው ውስጥ ስላለ ነው። ለትግራይ ወጣቶች የምመክራቸው ለጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ብለው ውድ ሕይወታቸውን እንዳይሰጡ ነው። በሚሰበኩት ሳይሆን ባላቸው እውቀት እውነታውን ለመረዳት ቢሞክሩ እራሳቸውንም የትግራይ ህዝብንም መታደግ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ።›› የኢትዮጵ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞቹን ግንባር ልኮ እንዲህ አይነት ታሪኮች ሰንዶ ማስቀመጡ ያስመሰግነዋል። ፎቶዎቹ ያለምንም ጽሁፍ መናገር የሚችሉ ናቸው። በአንዴ አይተናቸው የሚጠፉ ምስሎች አይደሉም፤ ሁሌም በተመለከታቸው ቁጥር ህሊና ውስጥ የሚመላለሱ ናቸው። ሌላው አስተያየቱን የሰጠን ወጣት ቴዲ አለሙ ይባላል። የትውልድ አካባቢው ሐዋሳ ነው። አዲስ አበባ በሥራ ጉዳይ መጥቶ አውደ ርዕዩን ለመጎብኘት ጎራ እንዳለ ነግሮናል። ቴዲ ፎቶግራፎቹን ከተመለከተ በኋላ በአመዛኙ የልብ ስብራት እንደገጠመው ይገልጻል። አንዳንዶቹ እንኳንስ በኢትዮጵያ በየትኛውም ዓለም ይፈጸማሉ ተብለው የማይታመኑ ናቸው ይላል። እንደርሱ አስተያየት ‹‹ፎቶግራፎቹ አገርን በከዱና ለአገራቸው በቆሙ ወገኖች መካከል የተደረገውን ትግል የሚያሳዩ ናቸው። ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጀምሮ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ አሻፈረኝ በማለት የአፋርና የአማራ ክልሎችን በመውረር ያደረሳቸውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች የሚያስቃኙ ናቸው። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያሉ ታሪኮች በዚህ መልክ መቀመጣቸው ሁኔታውን በቀላሉ ለመረዳት ያስችላሉ። ለአገራቸውና ህዝባቸው ፍቅር ሲሉ ህይወታቸውን ለመስጠት በግንባር የሚፋለሙ ሴትና ወንድ ወታደሮችን ማየት ያኮራል። ንጹሀንን በግፍ የሚገድሉና ተቋማትንየሚያወድሙ ከሀዲዎች ጭካኔ ግን ያስገርማል። እንዲህ አይነቱን የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ተማሪዎችና ወጣቶች እንዲጎበኙት ቢደረግ በርካታ ፋይዳ ይኖረዋል። አውደ ርዕዩ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ቢቀርብ በርካቶች ሊማሩበት ይችላሉ።
ምን አይነት መስዋዕትነት ተከፍሎ አገርን ማዳን እንደተቻለ ፎቶ ግራፎቹን በማየት ሰዎች የበለጠ ሊረዱ ይችላሉ። እያንዳንዱ ፎቶግራፍ የያዘው ታሪክ በጽሁፍ ይቅረብ ቢባል ብዙ መፃህፍት ሊወጣው የሚችል ነው።
አውደ ርዕዩ በአንድ ዓመት ህግ የማስከበር ዘመቻ የተፈጸሙ ድርጊቶችን በውስን ሰዓት የማስረዳት አቅም አለው። ወጣቱ እንዲህ አይነት የፎቶግራፍ አውደ ርዕዮችን ቢሚመለከት የአጥፊ ቡድኖችን ዓላማ ተረድቶ አገሩን ከጠላት የመከላከል አቋሙን ለማጠናክር ይረዳዋል። ወጣቱ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነች፤ ምን አይነት ዋጋ ተከፍሎባት አገር ሆና እንደምትቀጥል ከፎቶግራፎቹ መረዳት ይችላል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ክስተት በምስል አስቀርቶ እንዲህ ማስመልከት መቻሉ የሚያስገርም ነው። ለዚህ ሥራው በግሌ ምስጋና አቀርባለሁ። ›› “የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩን ልመለከት የገባሁት በአጋጣሚ ነበር።
በጉብኝት ላይ ሳለሁ ግን በከፍተኛ የስሜት መረበሽ ውስጥ ሆኜ ነው የጨረስኩት” ያለን ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት ነዋሪ የሆነው ወጣት ሱራፌል በላይ ነው። ሱራፌል አስተያየቱን እንዲህ ገልጿል።
‹‹ባየሁት ነገር በሙሉ ውስጤ ተረብሿል፤ በተለይም ህጻናትና እናቶች ላይ የተፈጸመው አስገድዶ መድፈር እጅግ አሳዝኖኛል። በርካታ ንብረትም ወድሟል፣ ንብረቱ እንኳ ሊተካ የሚችል ነው ብለን ልናስብ እንችላለን። በየቦታው ንጽኋን ተጨፍጭፈዋል። ህጻናት ያለ ወላጅ ቀርተዋል።
እነዚህ ወላጆቻቸው አጠገባቸው የተገደሉባቸው ህጻናት ወደ ፊት የሚገጥማቸው የስነልቦና ችግር ቀላል አይሆንም። እንዲህ አይነት ጭካኔ አይተው እንዴት መልካም ሰው ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ሳስብ መልስ አጣለሁ። እኔ እራሱ ባየሁት ነገር “የሰው ልጅ ይህን ያህል ይጨክናል እንዴ?” እንድል አድርጎኛል።
ከዚህ አውደ ርዕይ ወጣቱ ብዙ ነገር መማር ይችላል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ ጦርነት ለየትኛውም ወገን የሚጠቅም አለመሆኑን ይረዳል። በመቀጠል ለአገር ሲባል የሚከፈለውን መስዋዕትነት እስከምን ድረስ እንደሆነ ይገነዘባል።
በተረፈ ግን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መጥፎውንም ጥሩውንም ታሪክ ሰንዶ በማቅረብ ሰዎች እንዲማሩበት ማድረጉ ያስመሰግነዋል። ከዚህ በፊት የነበሩ ታሪኮች በዚህ መልክ ተደራጅተው ሲቀርቡ አላየሁም፤ ይህ አዲስ ተሞክሮ ነው። ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ። አመሰግናለሁ።››
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014