ከስምንት አመት በኋላ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆን የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ቢያንስ ከምድቡ የማለፍ እቅድ ይዞ ወደ ካሜሩን ቢያቀናም ሁለት ጨዋታ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ ወደ አገሩ ተመልሷል። ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከትናንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ ባህሩ ጥላሁን “እንዳቀድነው ያሰብነውን ማሳካት ባለመቻላችን ሕዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን” በማለት ተናግረዋል።
የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ እቅድ ምድቡን ማለፍ ነበረ። አቶ ባህሩ በተጨዋቾች በኮሮና መጠቃት እና ጉዳት፣ በቂ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አለማድረግ፣ የተከላካዩ ያሬድ ባየህ ቀይ ካርድ መመልከት ፣ የተገኙትን የግብ እድሎች አለመጠቀም ለተመዘገበው ውጤት ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀው ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል ።
“ማሳካት አለብን ተብሎ በታሰበው ነጥብ መሠረት ማለፍ የምንችልበት አጋጣሚ ነበር። ሆኖም ተጨዋቾች በትክክለኛ አቋም ካለመገኘታቸው እስከ ኮቪድ ድረስ ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ያም ሆኖ ውድድሩ ብዙ አዎንታዊ ነገሮች ነበሩት።” ያሉት የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ ሙሉ ለሙሉ በአፍሪካ ሊጎች ውስጥ ብቻ የሚጫወት ስብስብ ይዛ የቀረበችው ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗንም አብራርተዋል።
ውድድሩ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አስቆራጭ ነበር ማለት እንደማይቻልም ተናግረው፣ “በጣም በቅርብ ጊዜ የሚፈለገው የተፎካካሪነት ደረጃ ላይ መገኘት እንደምንችል ራሳችንን ያየንበት ነው።”ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም “ከሌሎች አንፃር ያለንን ድክመት አይተናል። እነዚህ ድክመቶች በ13 ቀናት ልምምድ የሚስተካከሉ አይደሉም። በአጠቃላይ ከነጥብ አንፃር የያዝነው ማሳለፍ የሚችል አይደለም።” በማለት አቶ ባህሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው “በኮቪድ መታመስ ተጨምሮበት በምድብ ጨዋታዎች ላይ እንደነበረው የቡድናችንን የመጨረሻ አቅም አውጥተናል ብለን አናስብም፣ በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ዕቅድ ባናሳካም መልካም ቆይታ ነበረን ብዬ መናገር እችላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከምድብ የማለፍ እቅድ ነበረን። እንዲሁ ህልም ብቻ ሳይሆን ለማሳካት የሚያስችል አቅምም ነበረን። ይሁን እንጂ እዛ ስንሄድ በገጠሙን ነገሮች ሳይሳካ ቀረ።” ያሉት አሰልጣኙ፣ “በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ ነች ብዬ መናገር አልችልም።” ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ለነበረን ጉዞ ድጋፍ ላደረጉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለሚዲያውና ሌሎች አካላት ምስጋና አቀርባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ከወዳጅነት ጨዋታ እጥረት ጋር በተያያዘ ቡድኑ ስለነበረበት ክፍተት ሲያስረዱም “ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የለችም፤ ነገር ግን ከዩክሬን፣ ኢራቅና ቱርክ ጋር እየተጫወተች ቡድኗን እየገነባች ነው፤ እኛ ግን ራቅ ብለናል፣ የወዳጅነት ጨዋታ ባለመኖሩ ማግኘት ያለብንን ያህል አልተጠቀምንም ፣ በዚህም በቀጣይ እያስተካከልን መሄድ አለብን” ሲሉ አስረድተዋል።
የዝግጅት ቀን ስለማጠሩና ስለ ቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ የመካፈል ዕድላችን የተጠየቁት አሰልጣኝ ውበቱ “13 የዝግጅት ቀን ብቻ ልምምድ መስራታችንና ጊዜው ማነሱ ከምድቡ እንዳናልፍ አድርጎናል ብዬ አላምንም ፤ ቀኑ ማጠሩ ግን ተጽዕኖ ነበረው” ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ እራሳቸውም ይሁኑ ሌላ አሰልጣኝ ዋልያዎቹን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚመለሱበት ትልቅ ተስፋ በውድድሩ እንደተመለከቱ አስልጣኙ ተናግረዋል፡፡ ዋና ጸሃፊው አቶ ባህሩ በበኩላቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኮንትራታቸው ባለመጠናቀቁ ከቡድኑ ጋር እንዲቀጥሉ ፌዴሬሽኑ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል።
አሰልጣኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድናቸው ቢያካትቱ ስብስቡ የተሻለ ጠንካራ እንደሚሆን ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡ የሚደመጥ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን የማትፈቅድ አገር መሆኗ በዚህ ረገድ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ውዝግብ ሲፈጥር የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
አቶ ባህሩ “ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ፓስፖርት ይዘው የተጫወቱ ነበሩ፣ ይሄ ስህተት ነው፤ መጠየቅ ያለበት ወገን መጠየቅ አለበት፣ ያኔ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫውቷል ተብሎ አሁን የሚጠየቀው ያኔ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በመፈጸሙ ነው፣ ሚዲያው ይህን ሊያየውና ፕሮግራም ሊሰራበት ይገባል” በማለት አስረድተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ባሉ ታላላቅ መድረኮች ጠንካራና ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ በአገር ውስጥ ጠንካራ ሊግ መፍጠር አንዱ አማራጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወይም ከአገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በቡድኑ ማካተት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማንሳት አብራርተዋል።
ዋልያዎቹ አሁን ባላቸው የአካል ብቂት መጠን ራሳቸውን ጠንካራ ማድረግ እና ጫና መቋቋም ላይ መስራት እንዳለባቸው ያስገነዘቡት አሰልጣኙ፣ የአንድ በአንድ ግንኙነቶችና በአየር ላይ ፍልሚያዎች ላይ አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ ስራ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል። ይህ ግን በሳምንት ስራ የሚስተካከል እንዳልሆነና በሒደት የሚመጣ መሆኑን አስታውቀው፣ ተጫዋቾች ራሳቸው ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 19/2014