በተፈጥሮ፣ በህመም አሊያም በአደጋ ምክንያት በአካላቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በዊልቼር እገዛ የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች ለህክምና በሚል ስፖርት እንዲሰሩ መደረጉን ተከትሎ የፓራሊምፒክ ስፖርቶች መጀመራቸውን ታሪክ ያመለክታል።
አካል ጉዳተኞቹ ቀስበቀስ ስፖርቱን ከማዘውተር ባለፈ ውድድሮችን እርስ በእርሳቸው በማካሄድ አሳድገውታል። በአሁኑ ወቅት ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል አንዱ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ነው።
ውድድሩ በመላው ዓለም በአጭር ጊዜ በመስፋፋቱ ምክንያትም አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማድረግ በቅቷል። በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ከተቋቋመ አጭር እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ስፓርቴን ለማስፋፋት እየሰራ ይገኛል። የተሳታፊዎቹን ቁጥር በማሳደግ በኩል አበረታች ተግባራትን ሲሰራ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ 11ኛው የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና አስተናጋጅ ለመሆን በቅቷል። ውድድሩ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄድ ከጀመረም ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገራት የሚሳተፉበት ውድድሩ በራስ ኃይሉ ትምህርትና ስልጠና ተቋም በሚገኘው ጂምናዚየም እየተካሄደ ይገኛል። በመክፈቻው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስኮች ከጉዳት አልባዎች እኩል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ ስፖርት ሲሆን፤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ይህውድድር በኢትዮጵያ በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ይህንን ውድድር ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እድል የሰጠውን የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን አመስግነዋል።
መድረኩ ከስፖርታዊ ፉክክር ባለፈ አፍሪካዊያንን የሚያገናኝ፤ ግንኙነታቸውንም የሚያጠናክር እንዲሁም ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑንም ገልጸዋል። የአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጎጆ፤ አሶሴሽኑ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ቢያስቆጥርም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስሩ የተለያዩ ቡድኖችን አዋቅሮ ውድድሮችን በማዘጋጀቱ እና ለስፖርቱ ዕድገት ባደረገው አስተዋጽኦ ይህን ውድድር ለማዘጋጀት በቅቷል።
አህጉር አቀፉ ፌዴሬሽንም ይህንን በመገንዘብ የአስተናጋጅነት ዕድል በመስጠቱም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 14ኛ ጊዜ በዱባይ ለሚካሄደው የዓለም ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄደው በዚህ የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አልጄሪያ፣ ግብጽ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሁለቱም ጾታ ተሳታፊ ናቸው። ለዓለም አቀፉ ቻምፒዮና አፍሪካን ወክለው የሚሳተፍ አንድ ቡድንን ለመምረጥ በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ፤ ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታ ተጫውታለች።
ጠንካራ ፉክክርና ማራኪ እንቅስቃሴ በታየበት የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ 26 ለ30 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፋለች። በወንዶች በኩል በነበረው ፉክክርም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግብጽ አቻው 25 ለ92 ተረትቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014