በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ለ21ኛ ጊዜ ትናንት ተካሄደ። በሩጫው ላይ አትሌቶች እና የውጪ ዜጎችን ጨምሮ 25ሺ ሯጮች ተሳትፈውበታል።
መነሻና መድረሻውን በመስቀል አደባባይ አድርጎ 10 ኪሎ ሜትርን በሸፈነው ውድድር በርካታ የክለብ እና በግላቸው የሚሮጡ ታዋቂና ጀማሪ አትሌቶች፣ የውጪ ዜጎችና አትሌቶች(ኬንያውያን እና ኡጋንዳውያን)፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ 25ሺ ሰዎች ተካፍለውበት በሰላም ተጠናቋል።
በውድድሩም ላይ በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊዎች ሆነዋል። በወንዶች የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለቡ አትሌት ገመቹ ዲዳ፣ የመከላከያ ክለቡ አትሌት ጌታነህ ሞላ እንዲሁም የግል አትሌቱ ቦኪ ድሪባ አሸናፊዎች ሆነዋል።
በሴቶች ደግሞ በግሏ የምትሮጠው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ አትሌቷ ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር እና የንግድ ባንኳ መልክናት ውዱ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በሴቶች አሸናፊዋ አትሌት ያለም ዘርፍ የኋላው ስትሆን፤ በውድድሩ አሸናፊ በመሆኗ የተሰማትን ደስታ ገልጻለች።
‹‹ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ውድድር እንደመሆኑ ጥሩ ዝግጅት አድርጌ ተሳታፊ በመሆን ለማሸነፍ ችያለሁ፤ በዚህም ተደስቻለሁ። በዚህ ውድድር ስሳተፍ ይህ ለሶስተኛ ጊዜዬ ነው፤ ሁለት ጊዜ አሸናፊ ነበርኩ። ይህንን ውድድር ካለፉት ውድድሮች
ልዩ የሚያደርገውም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቤ ነው። በቀጣይም እንደ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባሉ ውድድሮች አገሬን ለማስጠራት እፈልጋለሁ›› ስትል ሃሳቧን አንጸባርቃለች።
አትሌቷ አሸናፊ በመሆን የተሸለመችውን የወርቅ ሜዳሊያም ኢትዮጵያን በበጎ ጎን አስተዋውቃለች ላለቻት ጋናዊት ሞዴል ዶክተር ሴቶር ኖርግቤ ሜዳሊያዋን በማስታወሻነት አበርክታለች። ይህን አስመልክቶም ‹‹የእኛን ባህል በዓለም አደባባይ አስተዋውቃለች።
እኔም በዚህ ምክንያት ከማሸነፌ በፊት ቃል ገብቼላት ስለነበር፤ ሜዳሊያዬን ልሰጣት ችያለሁ›› ብላለች። አትሌቷ ሃሳቧን ስታጠናክርም ‹‹አፍሪካውያን እርስ
በእርስ በመተሳሰብና በአንድነት መሥራት ይገባናል›› የሚል መልዕክቷን አስተላልፋለች። በወንዶች ውድድር አሸናፊ የሆነው አትሌት ገመቹ ዲዳ በበኩሉ፤ እንደ እነ ጌታነህ ሞላ ያሉ ተፎካካሪ አትሌቶች ያሉት ውድድር ቢሆንም አሸናፊ በመሆኑ የተሰማውን ደስታ ገልጻል።
‹‹ለዚህ ውድድር አምስት ወራትን አስቀድሜ ዝግጅት ሳደርግ ስለቆየሁ አሸንፋለሁ የሚል ግምት ነበረኝ። ወደ ውድድሩ ከገባን በኋላም የነበረው ዳገትና ቁልቁለት ሩጫውን ከባድ ቢያደርገውም የሠራሁት ልምምድ አግዞኝ በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችያለሁ።
በዚህ ውድድር ወርቅ እንዳጠለቅኩት ሁሉ በቀጣይም በዓለም አቀፍ ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የአገሬን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ እሠራለሁ›› ሲልም እቅዱን ጠቁሟል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለጀማሪ አትሌቶች መልካም ዕድልን የሚፈጥር ሲሆን፤ በማናጀሮች የመታየት ሁኔታንም ያሰፋል። በመሆኑም አትሌቶች በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆን አቅማቸውን እንዲፈትሹም መልዕክቱን አስተላልፏል።
አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችም ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የውድድሩ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አባል አትሌት ብርሃኔ አደሬ፣ ከውድድሩ ስፖንሰር ቶታል ኢነርጂስ ማናጀር አኔ ሶፌ እጅ የሜዳሊያ፣ ዋንጫ እንዲሁም የ100ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ ለታላቁ ሩጫና ለመስራቹ ለአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ ሩጫ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያውያን መካከል የሰላምን፣ አንድነትና ወዳጅነት መገለጫና ማጠናከሪያ በመሆን ማገልገሉን ትናንት በፌስ ቡክ አካውንታቸው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላቁ ሩጫ መስራቾችን በተለይም የኢትዮጵያ ተምሳሌት ያሉትን አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን አድንቀዋል።
ኃይሌ ገብረስላሴ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ እንድትኮራ ማድረግ የቻለ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለበርካታ ወጣት አትሌቶች ምሳሌና ሞዴል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አትሌቱ በተለያዩ ጥረቶች የተገኘን ገንዘብ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ በማዋል በኩልም ሞዴል መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ኢትዮጵያ ካሏት ክፍለ አሕጉራዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ መድረኮች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚልም አስታውቀው፣ ለታላቁ ሩጫ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።
በአትሌቲክስ ስፖርት በምትታወቀው ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአሕጉሩ በትልቅነቱ ቀዳሚ እንዲሁም በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጁ ከሚባሉ 10 የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ ነው። በዓለም አቀፉ የማራቶንና ረጅም ርቀት ሩጫዎች ማኅበር (AIMS) እውቅና ያለውና በርካታ አትሌቶችም ራሳቸውን የሚፈትኑበት ዓለም አቀፍ ውድድር ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014