ከስምንት ምዕተ ዓመታት በፊት የኖረውን የብሉያዊውን የሞንጎል ንጉሥ የገናናውን የጄንጂስካንን (1167-1227) ተረክ ማስቀደሜ ለምሰድራቸው ሃሳቦች ማገናዘቢያነትና ማዋዣነት ይረዳ ስለመሰለኝ ታሪኩን አሳጥሬ አስታውሳለሁ። የሞንጎልን ኢምፓየር የመሠረተው ንጉሥ ጄንጂስካን ከአጠገቡ የማይለየው አንድ ለማዳና ምሥጢራዊ አሞራ ነበረው ይባላል። ንጉሡ ይህንኑ ለማዳ አሞራውን እንዳስከተለ ብቻውን ከቤተ መንግሥቱ ርቆ በሚገኝ ደን ውስጥ እየተናፈሰ ስለ ሀገሩ መፃኢ ዕጣ ፈንታ የጥሞና ጊዜ ወስዶ በማሰላሰል ረጅም ሰዓታትን ያሳልፍ ነበር ይባላል። አንድ ዕለት እንደለመደው በደኑ ውስጥ ሲንሸራሸር የውኃ ጥም እርር ስላደረገው አሞራውን እንዳስከተለ ምንጭ ያለበትን ቦታ ለመፈለግ ሽቅብ ቁልቁል እያለ መባዘኑን ተያያዘው።
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዕድል ቀንቶት ከአንድ ቋጥኝ ሥር የዕንባ ያህል የሚንጠባጠብ «ውኃ» ስላገኘ በእልህ አስጨራሽ ትዕግሥት ዋንጫውን ደቀኖ ካጠራቀመ በኋላ ለመጠጣት ወደ አፉ ሲያቀርብ ከየት መጣ ሳይባል ያ ስልጡን ለማዳ አሞራ ዋንጫውን በክንፉ ይቀመስልህ በማለት ከእጁ አስጥሎ ነፍስ አድን «ውኃውን» ደፍቶ አሳቀቀው።
ጄንጂስካን የአሞራውን ያልተገባ ድርጊት እንደ መቃበጥ ቆጥሮት ቁጣውን ዋጥ በማድረግ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ «ውኃው»ን ለማጠራቀም ዋንጫውን ከመሬት ላይ አንስቶ ቋጥኙ ሥር ደቀኖ ለሰዓታት ያህል ታግሶ ካጠራቀመ በኋላ ሊጠጣ ወደ አፉ ሲያስጠጋ ጣጠኛው አሞራ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን ከእጁ አስጥሎ ደፋበት።
በዚህን ጊዜ ጄንጂስካን መታገስ ተስኖት ሰይፉን ከሰገባው በመምዘዝ በቀኝ እጁ እንደጨበጠ፤ በግራ እጁ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ደቅኖ የሚንጠባጠበውን «ውኃ» ካጠራቀመ በኋላ እንደለመደው ሊጠጣ ወደ አፉ ሲያስጠጋ ልማደኛው አሞራ እየበረረ መጥቶ የሞላውን ዋንጫ በክንፉ ይቀመስልህ ብሎ «ውኃውን» ሲደፋበት ቀድሞውኑ ቆሽቱ እርር ብሎ የነበረው ንጉሥ ተወዳጅ አሞራውን በመዘዘው ሰይፍ ሁለት ቦታ መትሮ አስትንፋሱን አጨለመ።
በበቀል ድርጊቱ የረካው ንጉሥ ጄንጂስካን የአሞራውን ሬሳ በእግሩ ገፍቶ ከወረወረ በኋላ የሚንጠባጠበውን «ውኃ» ለአራተኛ ጊዜ ከመደቀን ይልቅ የእንጥብጣቢው ፍጥነት እንዲጨምርለት በማሰብ የምንጩን መፍለቂያ ጉድጓድ በመቆፈር ውኃውን ለማንፎልፎል ቋጥኙን ሲፈነቅል አንድ መርዘኛና ተናዳፊ ኮብራ እባብ በድንጋዩ ሥር ተጠቅልሎ ተኝቷል። ለካንስ ሲንጠባጠብ የነበረው ውኃ ሳይሆን የእባቡ መርዝ ኖሯል።
ንጉሥ ጄንጂስካን ይህንን ያልተጠበቀ መርዘኛ እባብ በድንጋጤ ፈጦ እያስተዋለ ሕይወቱን ከሞት ለመታደግ አሞራው የከፈለውን መስዋዕትነት ሲያስታውስ ነፍስ አልቀረለትም። ስቅስቅ እያለ በማልቀስ የዘላለም ፀፀቱን በልቡ በማርገዝ የዚያን ነፍስ አድን መልካም አሞራውን በድን ታቅፎ እያነባ ቤተመንግሥቱ ተመልሶ ሃዘን ተቀመጠ ይባላል። (ከበደ ሚካኤል ይህንን መሳጭ ታሪክ በተረትና ምሳሌ መጽሐፋቸው ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተርከውታል።)
ከንጉሥ ጄንጂስካን ታሪክ አንዳንድ ሰበዞችን እየመዘዝንና ከራሳችን ሀገራዊ እውነታ ጋር እያዛመድን ጥቂት ቆይታ እናድርግ። መቼም ታሪክም ሆነ የሥነቃል ውርስ «በምን አሉ» ቅብብሎሽም ሆነ በጽሑፍ የሚተላለፍልን ለትውልድ ማስተማሪያ እንዲሆን ታስቦ ስለሆነ ትውፊቶቹን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋሉ አግባብ ይመስለኛል።
እናት ዓለም ሀገራችን በዴሞክራሲ ጥም እየተሰቃየች ለዘመናት ኖራለች። ይሄው የዴሞክራሲ ጥም መንስዔ ሆኖም የንጉሡንም ሆነ የደርግ ሥርዓተ መንግሥታትን በአመጽና በነፍጥ ጉልበት በማንበርከክ የሕዝቡን «የነፃነት ጥማት እናረካለን፣ የነገውን የሀገራችንን መፃኢ የዴሞክራሲ ዕጣ ፈንታ በትግላችን እንወስናልን» በማለት «ጥራኝ ጫካው፣ ኧረ ጥራኝ ዱሩ!»ን እየዘመሩ በረሃ የከረሙ የሀገራችን «ነፃ አውጭ ቡድኖች» ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ዛሬም ቢሆን ጥቂት የማይባሉ ቡድኖች በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ በተቃዋሚነት ጎራ እንደተሰለፉ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በፊት ባወጡት የነፃ አውጭነት ስማቸውና መታወቂያቸው ፀንተው «እንዳገነገኑ» አሉ።
የንጉሡን ዙፋን በከስክስ ጫማው ገፍትሮ መንበረ መንግሥቱን የተቆጣጠረው ዕብሪተኛው ደርግም ሆነ በሸበጥ ጫማው ከተማ የገባው በረኸኛና «ነፃ አውጭ» ነኝ ባዩ ቡድን፤ በዴሞክራሲ ጥም እየተሰቃየች ለዘመናት ለኖረችው ሀገሬ ያወረሱት ቃሉን እንጂ ተግባሩን እንዳይደለ ውጤቱ ምስክር ነው። ከተሜውም ሆነ ባለ ሀገሩ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘመረለት ይሄው ስመ መልካም ዴሞክራሲ ቢያንስ በቀዳሚዎቹ የኢትዮጵያ የመንግሥታት ሥርዓቶች ውስጥ «ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተቷንም አላይ» እንዲሉ በአንደበት እየተተረከልን፣ በውይይት እየተቆላመጠና በጽሑፍ እየደመቀልን በሥርዓቱ ፊትአውራሪዎች የሽንገላ ቋንቋ እንቁልልጮሽ እየተባልን እነሆ የዴሞክራሲ ጥም እንዳቃጠለን የዕድሜያችን ፀሐይ «ከልጅነት እስከ ሽበት» አኩርፋ ወጥታ፤ አኩርፋ ልትጠልቅ ዳር ዳር እያለች ነው።
መቼም ሕዝብ ተስፋ አይቆርጥምና «እውነተኛውን የዲሞክራሲ ምንጭ» ያገኘ እየመሰለው በየሥርዓተ መንግሥታቱ ውስጥ ለውጥ ፈላጊ ልጆቹን እያስቀደመ እንደ ጄንጂስካን አሞራ ጥሙን ለማርካት «ያቀረቡለትን ዴሞክራሲ» በዋንጫው ቀድቶ ሊጎነጭ ሲሞክር የጓጓለት ውኃ የእፉኝት መርዝ እየሆነበት ብዙ ዜጋ በጨቋኞች ስራዬ እየተነደፈ ሕይወቱን ገብ ሯል።
ሺህ በሺህ የሚቆ ጠሩ የየትውልዱ ሰማዕታ ትም በስሙ የሚሉት ሕዝብ ጥሙን ለማርካት ሲል ብቻ በየዋህነት ድንጋዩን ፈንቅሎ «የውኃውን» እውነትነት ሳያጣራ በአምባገነኖች የሽንገላ መርዝ እንዳይመረዝ ሲታገሉና ሲተጉ እንደ ጄንጂስካን አሞራ የሰይፍ እራት መሆናቸውን ለማስታወስ ጊዜው መሽቶበታል አያሰኝም።
ሕዝብ በመርዘኞች መርዝ እንዳይነደፍ አምርረው በመታገ ላቸው የክላሺንኮፍ ሰለባ የሆኑ፤ በግርፋትና በኢሰብዓዊ ማሰቃያ አስትንፋሳቸውን የተነጠቁ፤ አካላቸውና ኅሊናቸው ላይፈወስ የቆሰሉ ዜጎችን ቤታቸው ይቁጠራቸው ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል። ከአምባገነኖች ባህርያት መካከል የሕዝብን ጥያቄ ማፈን፣ ማስደንገጥ፣ ማዘግየትና ማዘናጋት አዘውትረው ይጠቀሳሉ። ስለዚህም ነው ለመርዘኛው ዕቅዳቸው ማስፈፀሚያ እንዲረዳቸው «የዴሞክራሲ ዋንጫ ተትረፍርፎ የሚፈሰው እንደ ጄንጂስካን የቋጥኝ ሥር ‘ውኃ’ ዘመን በሚያስቆጥር ትዕግሥት እንጂ እንደ ቤታችን የቡና ሲኒ በፍጥነት ጢም ብሎ አይሞላም» እየተባልን ስንሸነገል የኖርነው።
በሕዝባዊ የእምቢተኝነት ቁጣ አሻፈረኝ ብለው ስመ ዴሞክራሲ የተላበሰውን ቋጥኝ ለመፈንቀል የሞከሩ ፅኑዓን የሕዝብ ልጆችም አምባገነኖች በቋጥኛቸው ሥር በሠወሩት የኮብራ እባብ እየተነደፉ እንዲወገዱ ተደርገዋል። «እንቁልልጮሽ» እየተባልን ስንሸነገል የኖርነውና ዕድሜውን ያደለን ዜጎችም ወጭ ወራጁን እየታዘብንና የየድርሻችንን የግፍ ዋንጫ እንደየአቅማችን እየተጎነጨን ለሁለት ፀጉር በቅተን ለምስክርነት ቆመናል።
ለመሆኑ «ፋታ! ፋታ! ገና ጀማሪዎች ነን» እየተባልን የምንሸነገልበት ዴሞክራሲ ከእንጭጭነት ወደ ፍሬነት የሚለወጠው በስንት ዕድሜው ላይ ሲደርስ ነው? ቢያንስ በሃያ ሰባት ዓመት ውስጥ በስሎ ሕዝቡን ለማጥገብ በወፍጮ ባይሰለቅ እንኳ ለእሸትነት ደርሶ ያንገበገበንን ጊዜያዊ ርሃብ ለማስታገስ እንደምን ተሳነው? የዴሞክራሲን የእንፉቅቅ ጉዞ እያወራንስ ምን ያህል ዘመን መጓዝ ይቻላል?
በበረሃ ውስጥ ተፀንሶና ተወልዶ በመንግሥታዊ መርሆነት በመጽደቅ የተጫነብንን የአይዲኦሎጂ ቋጥኝ ፈንቅለን እርግጠኛና የሚያረካ የዴሞክራሲ ምንጭ መሆኑን እንዳናጣራ እንኳ «በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀር የፍልስፍናችንን ቋጥኝ መፈንቀል አይቻልም» እየተባለ በአስከሬናቸው ሲምሉብን ባጅተዋል። ከአንድም ሁለት፣ ሦስትና አራት ቡድኖች። አንዳንዶች የአፋቸውን ፍሬ እየበሉ መሆናቸው ሳይዘነጋ።
ዛሬም ቢሆን ሁኔታው እየባሰበት እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አይመስልም። ለምን ቢሉ አንዳንድ አክቲቪስትና ፖለቲከኞች ነን ባዮች «የዴሞክራሲን ጠበል ለኢትዮጵያ የምናፈልቀው ቋጥኙን ፈንቅለን በሚንጠባጠበው ውኃ ዋንጫችሁን በመሙላት ሳይሆን ቋጥኙን ራሱን በጨበጥነው የሙሴ በትር በመምታት ውኃው እን ዲፈልቅ በማድረግ ነው» እያሉ የሚጮኹ «የዴሞክራሲ ጠበቆች ነን» ባዮች የተበራከቱበት ወቅት ነው። የካሁን ቀደሙ ታሪካችን እንዲህ አይነት ተሞክሮ አስተናግዶ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።
እነዚህ የዴሞክራሲ ጠበቃ ነን የሚሉ ሰሞንኛ ቡድኖች በፈርዖን ሠልፍ ከሚመሰለው የግብፅ ሠራዊት «እግሬ አውጭኝ ብለው በመሸሽ» አርባ ዓመታት ሙሉ ቃዴስ ለቃዴስ በተንከራተቱት መጻተኛ እስራኤላዊያን ይመሰላሉ። እንዴታውን ላብራራ፤ «የሀገራችን በረኸኛ ፖለቲከኞችም» ያለ አንዳች ፋይዳ በረሃ ለበረሃ ሲንከላወሱ ከከረሙ በኋላ ዛሬ ለምናጣጥመው የለውጥ አየር ውለታ ይግባውና ሀገር ያቀረበችላቸውን ግብዣ ተቀብለው ወደ እናታቸው ቤት ተመልሰዋል። «ግብራቸው ሳይሆን ቃላቸው ገንኖ» በሺህዎች አጀብና ሆታ ዕልል እየተባለላቸው ነዎሩ ተብለው አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ተደላድለው መቀመጣቸ ውን ካረጋገጡ በኋላ ግን የሕዝቡን የልብ ትርታ ከማዳመጥ ይልቅ ተሽቀዳድመው የስልጣና ችንን ወንበር ካልተረከብን በማለት በፈጠሩት አታካራ መንስዔነት በሞትና በመፈ ናቀል ጭዳ የሆነውን የወገን ቁጥር ለመገመት ይከብዳል።
ይሄው ድርጊታቸው አነሰ ብለውም ጭንጫ መሬት እየጫሩ «ምንጭ አፍልቀን ከዴሞክራሲ ጥማችሁ የምናረ ካችሁ እኛ ብቻ ነን» በማለት በሽንገላ ቃል ሊያባብሉን መሞከራቸው አጃኢብ የሚያሰኝ ይሉኝታ ቢስነት ነው። ያውም በግላጭና በአደባባይ።
አንዳንድ ቡድኖችም እንዲሁ በከፋ መልኩ የእባብ መርዝ ወደሚያንጠባጥብ ቋጥኛቸው እየመሩን በስመ ዴሞክራሲ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያጋጩ፣ ሲያፈናቅሉና ሲገድሉ እያስተዋልን ነው። አንዳንድ «ፖለቲካዊ ጉተናቸው ያልጠና» ቡድኖችም ዋኝተን ከማንወጣበት የተስፋ ባህር ውስጥ እየዘፈቁን ዴሞክራሲ ማለት ይሄ ስለሆነ ቀድታችሁ ተጎንጩ እያሉ ያማልሉናል። ዓይኑን በጨው ያበሰው ደፋር ቡድንም እንዲሁ ዝናብ አልባ ደመና ተስፋ እንድናደርግና ዋንጫችንን በእምነት ከፍ አድርገን በመያዝ «ዋንጫ ነዎር! ወይንም ቺርስ!» እያልን በማንጋጠጥ እንድንጠብቅ ይሰብኩናል።
ይህቺ መከረኛ ሀገራችን ፈርዶባት ከዴሞክራሲ አሰሳና ጥማት ለመርካት ዛሬም እንደ አምና ካቻምና «እሰይ ስለቴ ሠመረ» እያለች ለመዘመር የታደለች አይመስልም። መሽቶ በጠባ ቁጥርም አንገት የሚያስደፉ ትዕይንቶች እያስተዋልንም እየሰማንም ነው። ሀገር ማህፀኗ ለምለም ቢሆንም የምትወልዳቸው ብዙዎቹ ልጆቿ ለእናትነቷ ክብር የሚሰጡ፣ ሁሉም ለፍሬ የሚበቁ፣ ሁሉም ለምርቃት የታደሉ ሊሆኑ አልቻሉም።
የታሪካችን ገፆች ለምስክርነት ከትበው ከያዟቸው ጉዳዮቻችን መካከል በወርቅ ቀለም የተጻፉ በርካቶች መኖራቸውን ባንክድም፤ በእንባችንና በደማችን ተበጥብጠው በጥቁር መቃ ብርዕ የከተብናቸው አንገት አስደፊ ገጠመኞቻችን ግን እልፍ ጊዜ የሚበልጡ ይመስለኛል። በአንዳንድ ዘመን ሀገሬ ዕልል የተሰኘላቸውን ፍሬዎች አምጣ ብትወልድም የምኞቷ ሳይሞላላት እየቀረ ልጆቿ በእርባና ቢስ ሾተላይ እየተነደፉ የወላድ መካን ሆና ቀርታለች። በአንዳንድ ዘመንም እንዲሁ ሀገሬ ጭንጋፎችን ወልዳ ለመከራ እንደዳረጓት አብነት መጥቀስ አይገድም።
በዛሬ ጀንበር ግን ከሀገራችን ምጥ የምንጠብቀው ሀገሪቱ ራሷ ሀገሬ ብላ የምታከብራቸውን በርካታ ልጆች እንድትወልድ እንጂ የሥልጣን ምች የመታቸው ጭንጋፎች እንዲፈለፈሉ አይደለም። የጅምሩ አበረታች ጉዞና ትሩፋቶች የሚያመለክቱ ግን ሀገሬ ያረገዘችው የለውጥ ፅንስ ተስፋ ያለውና የሚያጓጓ ልጅ እንደሚወለድ ነው። ምንም እንኳ የምጥ ጣሯ ቢበዛም።
እርግጥ ነው ይህ የተፋፋመው የሀገሬ ምጥ በእስካሁኑ ጉዞው ሀገሬን ራሷን የተሸከሙ ጥቂት ደንዳና ትከሻ ያላቸውን ፊት መሪ ልጆችን አስገኝቶልናል። ቁጥራቸው ኢምንት ቢሆንም። እነዚህ ዘመናት ካስቆጠረ የሀገሬ የጣር ምጥ የተወለዱ ልጆቿ የዴሞክራሲ ማህተም በልባቸው ውስጥ ተቀርፆ መወለዳቸው ብቻ ሳይሆን ድክ ድክ ከሚለው መልካም የዳዴ ጅማሯቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ አበጃችሁ የሚያሰኝ ውጤቶችንም እያስተዋልን ነው።
እነዚሁ በጣር የተወለዱ ጥቂት የብዙኃን ልጆች ተመሪው ሰፊ ሕዝብ የልቡ ስለደረሰለት «ወፌ ቆመች» እያለ በማበረታታት ጠንክረው እንዲወጡለት በተስፋ እየጠበቃቸው ነው። የዓለም ማኅበረሰብም ቢሆን ከአጽናፍ አጽናፍ ድምፁን እያሰማ በእስከ ዛሬው የዳዴ ጉዟቸው መርካቱን እየገለጠ ብቻ ሳይሆን ለነገውም የመንግሥት አስተዳደር ጉዟቸው ከጎናችሁ ነን በማለት እየደገፋቸው ይገኛል።
ለመሆኑ ይህ በሀገራችን ብልጭ ያለው የዴሞክራሲ ብርሃን እንዳለፉት ዘመናት በአምባ ገነኖች ትንፋሽ ጠፍቶ እንዳይዳፈን ከማን ምን ይጠበቃል?
በቀዳሚነት የአደራ ሸክሙ በጫንቃው ላይ የሚወድቀው ሕዝቡ ራሱ ነው። እንዴት? ከጄንጂስካን ተረክ አሁንም አንዲት ሰበዝ ደግሜ ልዋስና ሃሳቤን ላጎልብት። ይሄኛው ወይንም ያኛው ብሔረሰብ ብለን ፍረጃ ውስጥ ሳንገባ፤ በጥቅሉ ሕዝበ ኢትዮጵያ በሙሉ በዴሞክራሲ እጦት፣ በአስተዳደራዊ አድሎ፣ በኢሰብዓዊ ግፎች በጅምላ ሲቀጣና ሲዋረድ መኖሩ እርግጥ ነው። ሕዝባችን መከራ ቻይ ብቻ ሳይሆን፤ መከራን ተቋቁሞ የማለፍ ብልሃትም የታደለ ምስጉን ሠራዊት ነው። ስለዚህም ለጥምህ እርካታ የሚሆን የዴሞክራሲ ምንጭ የምናፈል ቅልህ እኛ ብቻ ነን እያሉ ግራ በማጋባት የፍልስፍናቸው መርዝ ወደሚንጠባጠብበት ቋጥኛቸው ሊነዱት የሚሞክሩትን ቡድኖችም ሆነ የፖለቲካ ካባ የደረቡትን ማንነት በጥንቃቄ ሊመረምር ይገባል።
የፖለቲካ አመራር ፍልስፍናችን ይሄንና ይሄንን ይመስላል እያሉ በፈጠሩት የአይዲዮሎጂ ሽፋን ግራ ሊያጋቡት የሚሞክሩትንም «እስቲ ቆዩኝ፤ ቋጥኛችሁን ፈንቅዬ እስክፈትሻችሁ ድረስ ጊዜ ስጡኝ» በማለት አስታግሶ ለጥሙ ያቀረቡለትን የውኃ እንጥብጣቢ ወደ አፉ ከማስጠጋቱ በፊት ሊያጠናቸው ይገባል።
የሕዝብ ልጆች የሆኑ ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ቡድኖች፣ የሚዲያ ተቋማትና የሃሳብ አፍላቂ (Think Tank) ስብስቦችም በነፍሳቸውም ቢሆን ተወራርደው ለሕዝብ የስጋት ጥያቄ የሆኑ ጉዳዮችን በቸልታ ሳያልፉ «መርዙን መርዝ፤ ጤነኛውን መልካም!» በማለት መፍትሔ ሊያመላክቱ ይገባል። እነዚሁ ሕዝባዊ ቡድኖች የፖለቲካ ምርጫና ሥልጣን ብቻ ህልምና ቅዠት ለሆነባቸው ወበከንቱዎች በሕዝብ ጫንቃ ላይ እንኮኮ ለማለት ጎንበስ በሉ የሚሉንን ቡድኖችንም በቃላቸው ብቻ ሳይሆን በጽሑፍ ሰነዳቸው እማኝነት ጭምር የአይዲዮሎጂ ፍልስፍናቸውን ቋጥኝ እንድንፈነቅል መድረኮችን ለውይይት ክፍት ሊያደርጉልን ይገባል። የየቡድኖቹን የምንጭ ጥልቀትና ጣዕምም ለመመርመር መጀገን ይገባቸዋል። በዚህ ረገድ ሃሳብ አመንጪ የተባሉ ገለልተኛ ቡድኖቹ በሙሉ ሳይታክቱ የአደባባይ የውይይት መድረክ በማመቻቸት የሙግቱ አስተባባሪ መሆን እንደሚገባቸው አበክረው ሊገነዘቡ ይገባል።
በተለይም ሁለት መልክ ያለው ጃኬት ለብሰው በሌሊት ወፍ ባህርይ ሕዝቡን የኮሜዲና የትራዤዲ ተውኔት ሊተውኑበት የሚሞክሩትን ፊት ቀደሞችንም በድፍረት ሊያጋልጧቸው ይገባል። ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን በአደባባይ ላይ አቁመው ለጀማው ፍርድ እንዲቀርቡ የአቃቤ ሕዝብነት ግዴታቸውን ሊወጡ ግድ ይሏል።
የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ «መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው» የሚለውን የሕገ መንግሥቱን «ዓለማዊ ቀኖና» እንደ መሸሻ ምክንያት በመጥቀስ እውነትን ከመጋፈጥ ሊርቁ አይገባም። ይልቁንስ የሕዝብን ዕጣ ፈንታና የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት በማስጠበቅ ረገድ በተግባር የኮሰመኑ፣ በሽንገላ የተካኑና በሕዝብ መካከል ጠብን የሚዘሩ ምዕመናኖቻቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍታቸው እየጠቀሱ በየዐውደ ምህረታቸው ላይ ሊያስተምሯቸውና አደብ ሊያስገዟቸው ይገባል። እንዲያው ለነገሩስ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ እውነታ ከሆነ፤ «ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃ ጣፋጭ ውኃ ሊወጣ ይችላልን።» ጥያቄው ሁላችንንም ይመለከታል።
የዚህ ጽሑፍ የማጠቃለያ ኃይለ ቃል «በስመ ዴሞክራሲ ከተለያዩ ቡድኖች በዋንጫችን እንድንሞላ የሚቀርብልንን ውሃ ከመጠጣታችን አስቀድሞ የየፖለቲካ ቡድኖቹን የፍልስፍናና የርዕዮተ ዓለማቸውን ምንጭ በአግባቡ ለመረዳት ቋጥኛቸውን ፈንቅለን በመፈተሸ አጥብቀን እንመርምር። የሚያንጠባጥቡልንን ውኃ መሰል ማዘናጊያ ለመጎንጨትም አንፍጠን” የሚል ነው። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ