ብዙ ሰዎች እንደሚሉት የሰላምን ዋጋ የምንረዳው ሰላምን ስናጣ ነው! “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ በመሆኑም የሰላም ዋጋው ለአገር የጋራ ጥቅምና ደህንነት በአንድነት መቆም ብቻ ነው፡፡
ሰላም የመኖር ዋስትና እና የህልውና ጥያቄ እንጂ አማራጭ አይደለም፡፡ ለአገር ህልውና ክብር ሰላም መሠረት ሲሆን ሰላም ከሌለ ሁሉም የለም፣ ሁሉም የከንቱ ከንቱ፣ የማይዳሰስ፣ የማይታይ ጉም መዝገን ይሆናል፡፡
ሰላም በገንዘብ የሚገኝ ቢሆን ኑሮ በዚች ምድር ላይ የሚገኙ እጅግ ብዙ ገንዘብ ያላቸው አገሮች እንዲሁም ሀብታም ግለሰቦች ለመግዛት ከሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ገንዘብ ይከፍሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰላም በዋጋ አይተመንም ፡፡
የሰላም ዋጋው ለአገር የጋራ ጥቅምና ደህንነት በአንድነት መቆም ብቻ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብን ደህንነትና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ሉዓላዊነት የመጠበቅ ግዴታም ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
መንግስት ያለ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ሰላምን ማስፈን አይችልም፡፡ ጭብጨባ በሁለት እጅ እንጂ በአንድ እጅ እንደማይደምቅ ሁሉ አስተማማኝ ሰላምም ያለዜጎች ተሳትፎ ማረጋገጥ ከንቱ ምኞት ነው።
የአገር ህልውና እና የሕዝብ ደህንነት ማስቀደም የለውጡ ዓላማና መነሻ በመሆኑ ከኢትዮጵያ በፊት ምንም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለም ማለት ያስፈልጋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ሰላምና ዴሞክራሲ ይቅደሙ ማለት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡
የሰላምን ዋጋ ባለመረዳትና ከሌሎች ዓለማት መማር ተስኖን ዛሬ በየአደባባዩ ስለ ልዩነት ስለ ዘር እየሰበክን በራሳችን ላይ የጥፋት ዘመቻ ለመክፈት ነጋሪት ስንጎስምና ስናስጎስም የምንውል እልፍ ነን ።
በሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች የሚደርሰውን እጅግ ሰቅጣጭ የመጠፋፋት የታሪክ ኩነት በግድ ጎትተን ወደ ቤታችን ለማስገባት ስንጥርም እንታያለን።
ስለሰላም አስፈላጊነት የሚያውቁት በሰቆቃው ሕይወት ውስጥ ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት ሕዝቦች ናቸው ፤ እኛ በሰላም አገር ውስጥ እየኖርን ስለሰላም እንዴት መስበክ ተሳነን፤ ስለፍቅር እንዴት መዘመር ተሳነን፤ ነገር ግን በሰላም ለመኖር ስል ስለአንድነት ድምፃችን ከፍ ብሎ ሊሰማ ፤ እርስ በእርስ እንድንጠፋፋ ሰርክ ከሚሰብኩን የጥፋት ዛሮች ራሳችንን ልናርቅ፣ ለሰላምም ዋጋ ልንስጥ ይገባል። መንግሥትም በተለይም እንደ አገር ከዚህ ቀደምም ያዝ ለቀቅ ስናደርገው የነበረውን አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በኮሚሽን ደረጃ በማቋቋምና ሕዝብን መንግሥትን በአንድ ለማግባባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል።
በዚህ መድረክ የተለያዩ አካላት የሚሳተፉ ከመሆኑም በላይ እንደ አገርም ሰላምና ደህንነታችንን ለማስጠበቅ የሚኖረው ሚና ቀላል አለመሆኑም ይገመታል። ከሚያለያዩን ጉዳዮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ እንድናተኩር ያለመው ይህ የምክክር መድረክ በኮሚሽን ደረጃ ተዋቅሮ ስራውን ለመጀመር የኮሚሽን ጥቆማ በመሰጠት ላይ ነው።
በእርግጠኝነት ዋጋ የማይተመንለትን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማግኘትና ሕዝብ እንደ ሕዝብ እርስ በእርስ ተግባብቶ ተስማምቶ ተረዳድቶ ልዩነቶቹን አጥብቦ ይኖር ዘንድም የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ ስለመሆኑ በርካቶች እየተናገሩም ነው።
እኛም አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን በዚህ ደረጃ ታስቦበት ሊቋቋም እየተሰሩ ያሉት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሁም ኮሚሽኑ እውን ሲሆን እንደ አገርና ሕዝብ ምን እናተርፋለን? ከማንስ ምን ይጠበቃል? ስንል ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ለፓስተር ጻድቁ አብዶ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሊቋቋም የተለየያዩ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነውና እርስዎ ይህንን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?
ፓስተር ጻድቁ፦ አገራዊ የምክክር መድረኩ ሃሳቡም ሲነሳ እንድካፈልበት ተደርጌያለሁ፤ ከዛም በኋላ አዋጁን የማንበብ እድሉንም አግኝቼ በደንብ አይቼዋለሁ፤ እስከ አሁንም እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶችንም እንደ ሃይማኖት አባትም እንደ ዜጋም ሆኜ እየተመለከትኩ ነው። እዚህ ላይ እንግዲህ በመጀመሪያ ደረጃ አብሮን የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማንግባባቸው ነገሮች እየበዙ መጥተዋል።
በመሆኑም እኛ አሁን ያለንበት ሁኔታ ሆን ብለን ላለመግባባት እየሄድን ያለን ሁሉ ይመስለኛል፤ ሽንቁር እየፈለግን ጠብና ጭላቻ እንዲሁም ቂም በቀል ውስጥ ከመግባት የሚያግባቡንን ነገሮች እየፈለግን ብንግባባ ይሻላል ባይ ነኝ።
በሚገርም ሁኔታ እኮ እኛ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን አንድ አይነት አረዳድ የለንም፤ በሰንደቅ ዓላማችን ላይ ባለ አርማ መግባባት አቅቶን ስንት ጊዜ ወደጸብ ለማምራት እንሞክራለን ፤ ነገር ግን ሰንደቅ አላማችንን ብናይ ብቻ እንኳን ከትላንት ጀምሮ እየተለዋወጠ እዚህ የደረሰ ነው፤ ባለው ሕገ መንግስት ላይም የአርማው ጉዳይ በግልጽ ተቀምጧል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ያስፈልጋል አያስፈልግም በማለት ሙግት ይገጥማል፤ እስኪ መፍትሔ አምጣ ተብሎ ሜዳው ሲሰጠው ደግሞ የሚያመጣው ሃሳብ ከዚህ በፊት ችግር የፈጠረ ነገርን ወይም ሃሳብን ነው። ይህ ደግሞ አገርን ወደኋላ የሚመልስ ይሆንና ተቀባይነት አያገኝም፤ በዚህ መካከል ልዩነትን በማስፋት አንድነትን ለማጥፋት ብሎም ጸብን ለማራገብ ከፍተኛ የሆነ ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል።
በመሆኑም ማንኛውም ሃሳብ ብንይዝ መጀመሪያ ወደጠረጴዛ አምጥተን መወያያት አለብን፡፡ ይህ ውይይታችን ደግሞ ጸባችንን ለማባባስ የሌለ ታሪክ እየፈጠርን ተቧድነን አገርንና ሕዝብን ሌላ ችግር ውስጥ ለማስገባት ሳይሆን ለመግባባት ሊሆን ይገባል።
አሁንም ቢሆን ላለፉት 45 ዓመታት እንዳንግባባ በችግር ላይ ችግር እየጨመርን ስንጓተት እንድንኖር ያደረጉን ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ እኔ የሚገርመኝ ነገር ድሮ እኛ ተማሪ ሆነን ሀሳቡ ሶሻሊዝም ኮሚኒዝም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እንጣላ የነበረው በሃሳብ ነበር፤ ነገር ግን እነዛ የሃሳብ ልዩነቶቻችን ዛሬ ላይም በኢትዮጵያ ምድር ላይ እያጣሉ እያነታረኩ ነው።
ይህ ሊሆን ፈጽሞ አይገባም ነበር። በመሰረቱ ችግሮቹ እዚህ ሊደርሱ የቻሉትም ወቅታዊ ምላሽን ስለተነፈጉ ይመስለኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ቀድሞ ልዩነታችን ለምሳሌ መሬት ላራሹን መውሰድ ትችያለሽ እሱ ነበር ፤ ዛሬ ላይ ደግሞ ይህ ሁኔታ ግልብጥ ብሎ ሀብታሞቹ መሬት ለምን የግለሰብ አይሆንም ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩን ችግር ላይ የሚጥል ነው። በመሆኑም አገርን ወደተሻለ ሁኔታ ለመውሰድ እንደ ሌሎች አገሮች በእድገት ጎዳና ለማራመድ ብዙ ሥራ ይጠይቀናል።
በተለይም ዛሬ የተጣላንባቸውን ነገሮች በሙሉ ዛሬውኑ ጨርሰን እልባት ሰጥተን ልጆቻችን ከጸብና ከቁርሾ ከንትርክ የጸዳ አገር ይዘው እንዲኖሩ በተለይም ካለፈው አንድ አመት ወዲህ የገባንበት አይነት ምስቅልቅሉ የወጣ አይነት ነገር ውስጥ እንዳንገባ በአገራችን ላይም እንዳይደገም ለማድረግ ይህ የምክክር መድረክ ወይም ኮሚሽን ለእኔ እጅጉን ወሳኝነት ያለው ነው። ማንኛውንም ነገር በጉልበት የመፍታት ፍላጎት እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል አጉል እልህ የትም እንደማያደርሰን ማወቅ ደግሞ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም እኛ ብዝኃነት ያለባት አገር ላይ የምንኖር ሕዝቦች እንደመሆናችን የወንድም እህቶቻችንን ስሜት መረዳት በተቻለ መጠን እንደ አንድ አገር ህዝብ ተግባብተን ለመኖር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ ስለ ራሴ ብነግርሽ ልጅ ሆኜ አጼ ቴዎድሮስን እጅግ በጣም ነበር የምወዳቸው፤ ታሪካቸውንም በጣም ነበር የማነበው፤ እያደኩ ስመጣ ደግሞ እዚህ ላይ ተሳስተዋል ይህችን ባያደርጓት የምለው ነገር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን የዛሬ መቶና ሁለት መቶ አመት ባለፈው ታሪክ ግን መጣላት አስፈላጊ ነወይ ? ይልቁንም እኛ ባለፈ በአባቶቻችን ታሪክ እየተጣላን ሌላ ችግር ውስጥ ከምንገባ ለምን የራሳችንን አዲስ ታሪክ አንሰራም።
በዚህ ውስጥ ደግሞ የምንሰራው ታሪክ የሚካሰውን ክሰን ሕግና ደንብን በተከተለ ሁኔታ የሚሄድ አድርገነው ብናልፍ በእውነት ነው የምልሽ ከራሳችን ከአምላካችን እንታረቅ ነበር። እኛ ዛሬ ከራሳችንም ከአምላካችንም የተጣላንበት ሁኔታ ስለሆነ ያለው ይህ ጉዳይ ቢታሰብበት የሚልም ሀሳብ ማንሳት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ አንዳንድ ጊዜ ግን የጸባችን መንስኤ እኔ ብቻ ልደመጥ የሚል ግትርነት አይመስልዎትም እንደው በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፓስተር ጻድቁ፦ አዎ ይህማ ትልቁ ችግራችን እኮ ነው። እኔ ብቻ ልደመጥ ከኔ ብሔር ወይም ሃይማኖት ውጪ ያለ ማንም ቢሆን መብለጥ የለበትም ማለት ነው እዚህ ያደረሰን የሚመስለኝ፤ ግን ይህ አካሄዳችን በችግር ላይ ችግር እየደረበ ቁርሾ እያባባሰ መጣ እንጂ በዚህ አካሄድ ከፍም ዝቅም ያለ ብሔርም ሆነ ሀይማኖት ለእኔ አይታየኝም።
በነገራችን ላይ ይህች አገር የአክቲቪስቶች ወይም የፖለቲከኞች ብቻ አይደለችም ፤ይልቁንም ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር እናት መጠጊያ መኖሪያችን ናት። ይህንን ደግሞ አክቲቪስቱም ፖለቲከኛውም ነጻ አውጪውም ብሔርተኛውም መንግሥትም ሁሉም ሊረዳው ሊገነዘበው ይገባል።
በመሆኑም የጮሁ ወይም ደግሞ የሚጮህላቸው ያላቸው ሕዝቦች ብቻ የሚሰሙበት ሊሆንም አይገባም፤ በጣም ዝም ያሉ ግን ደግሞ አገርን ሊያሻግር የሚችል ሃሳብ ያላቸው ብዙ ሚሊዮኖች አሉን፤ እነሱ ጋር ወረድ ብሎ ማየት መስማት መወያየት ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ የሚበቃ ጥሩ ባህልና ወግ ያለንም ሕዝቦች ነን። በመሆኑም መንግሥት ይህንን የምክክር ሃሳብ በግልጽ ሲያመጣው በግንባር ቀደምትነት ከደገፉት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ። ምክንያቱም ለእኛ የሚያስፈልገን ነገር የሰላምና የሰላም መንገድ ብቻ በመሆኑ ነው። አባቶቻችንን የሚሉት እኮ ከተመካከሩበት በጣም መጥፎ የነበረን ነገር እንኳን ቀና አድርጎ ማስኬድ ይቻላል ነው።
በመሆኑም አሁንም የምንመካከረው የምንነጋገረው እነዚህ መጥፎ ሆነው በውስጣችን ገንግነው ያስቸገሩንን የመለያየት ሀሳቦች ድባቅ ለመምታት ሊሆን ይገባል።
አልያ ግን አሁንም በምክክር ሰበብ አጀንዳ ቀርጸን እርስ በእርሳችን ለመፋጀት ከሆነ ያሳንሰናል፣ ያጠፋናል፤ በመሆኑም ለማንም የማያደላውና ብሔር የሌለውን አምላካችንን ተከትለን የተጀመሩ ነገሮች ፍሬያማ እንዲሆኑ የበኩላችንን ማድረግ አለብን።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ቀደም መሰል መድረኮች እየታሰቡ አንዳንዴም እየተዘጋጁ ግባቸውን ሳይመቱ የቀሩበትን ሁኔታ አስተውለናልና እንደው ለዚህ ምክንያቱ ምን ነበር አሁንስ እንዴት ነው ሊታረም የሚገባው?
ፓስተር ጻድቁ፦ ለዚህ ንግግሬ ይቅርታ እየጠየኩ ሆኖም ግን ለመድረኮቹ እርስ በእርስ ለምናደርጋቸው ምክክሮች ፍሬ አለማፍራት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ባህላችን ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ያደግንበት የኖርንበት ባህል ያስተማረን ደግነት ሩህሩህነት አብሮ መብላት መጠጣት በችግር በደስታ ጊዜ መረዳዳት ቢሆንም በተቃራኒው ደግሞ ግትርነትና እልኸኝነትም መገለጫችን ነው።
ይህ ደግሞ በንግግር እንዳንሸነፍ እንዳንረታ እንዳንስማማ የራሱን አስተዋጽዖ አበርክቷል። በአንድ ነገር ላይ ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ሁላችንም ጀግኖች እምቢተኞች አንበሶች ነን። ነገር ግን ያልተረዳነው ነገር ጀግንነት እኔ ያልኩትን ሃሳብ ብቻ ተቀበል ብሎ በሌሎች ላይ በመጫን የሚመጣ አይደለም።
የእኔን ተሞክሮ ብነግርሽ በቅርብም በሩቅም እርቀ ሰላምን እናወርዳለን ብለን የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ጨምረን ወደብዙ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰን እናውቃለንና በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን የታዘብኩት ነገር ይቅር መባባልን ብንፈልግና ብናስብ እንኳን አብሮን ሲወረድ ሲዋረድ የመጣው እልኸኝነት ለምን ተነካሁ አይነት ስሜት ወደኋላ ይጎትተናል፤ ብዙዎቹ የእርቀ ሰላም መንገዶችም ላለመሳካታቸው ምክንያቱ ይህ ነው።
አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ልምዳችንም እንዳየነው ሰዎች ሲጣሉ እርቅ ያለ አይመስላቸውም፤ በመሆኑም ሰዎች መጣላትም መታረቅም ከዚያም በኋላ አብሮ መኖርም እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል ፤ የአንድ አገር ሕዝብ ስንሆን ደግሞ እንለያይ ብንል እንኳን በቀላሉ መለያየት አንችልም።
ቀላሉ ምሳሌ ኤርትራና ኢትዮጵያን ማየት በቂ ነው። በመሆኑም ተለያይተን መለያየት ላንችል መጣላቱ ምን ያደርጋል ተግባብተን የምንኖርበትን ዘዴ መቀየሱ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ የምክክር መድረክ በታሰበው ልክ ሄዶ ውጤት ያመጣ ዘንድ ከአዘጋጆቹም እንዲሁም ከተሳታፊዎቹ ምን ይጠበቃል? ሚናቸውስ ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ፓስተር ጻድቁ ፦ አዎ ሃሳቡ ጥሩ ነው፤ በእርግጠኝነትም በውጤት ይታጀባል የሚል ተስፋም እምነትም አለኝ። ነገር ግን ይህንን መድረክ የሚመሩት አካላት ገለልተኝነት ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። ለአንድ ሕዝብም ይሁን ሃይማኖት።
ለተማረ ላልተማረ በሚል ምንም ዓይነት የተዛባ ግምት ውስጥ መግባት የለባቸውም ነው የምለው። በመሆኑም እነዚህ አካላት ገለልተኛ ለመሆን መወሰን ብሎም ለህሊናቸው ብቻ ተገዢ እንደሚሆኑም እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል።
ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ለራሳቸው ወይም ለሚፈልጉት ብሔር ሃይማኖት ግለሰብ ወይም ሌላ ለማድላት አስበው ከመጡ ከዚህ ቀደም ካሳለፍናቸው የውይይት መድረኮች የተሻለ ውጤትን ካለማግኘታችንም በላይ እንደውም ለከፋ ችግር ሊያጋልጡን የሚችሉበት እድል የሰፋ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ይህ የውይይት መድረክ አሁን አገራችን ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር አውጥቶ እንደ አገር የምናስበውን ብሔራዊ መግባባት በማምጣት በኩል የሚኖረውን ሚና እርስዎ እንዴት ገመገሙት?
ፓስተር ጻድቁ፦ እኔ እንደ ሃይማኖት አባት ለአገሬም ሆነ ለሕዝቦቿ ካለንበት ችግር ወደፊትም ሊመጣብን ከተዘጋጀው መዓት አውጣን እያልኩ እየለመንኩ በመሆኑ ይህ መሰሉ የውይይት መድረክ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ በግሌ ይሰማኛል። ወደቀናው መንገድ እንደሚመራንም ከፍተኛ የሆነ እምነት አለኝ።
ከላይ እንዳልኩት ግን መድረኩ ቀና እንዲሆን የታለመለትን ግብ እንዲመታ በተቻለ መጠን የኮሚሽነር ምርጫው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ኋላም በሥራው ላይ የሚመደቡ አካላትን ከማንኛውም ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋም ቢሆን የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ምክረ ሀሳቦች እንደ አገርና ሕዝብ ማክበር በተቻለ መጠንም ለተፈጻሚነታቸው የራስን ጥረት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፦አገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ በዘላቂነት ለመውጣትና ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና እንዲኖር ከኮሚሽኑ ባሻገር የመንግሥትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደ ሃይማኖት አባቶች። የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ሌሎች ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ፓስተር ጻድቁ፦ ወደዚህ ኮሚሽን የሚቀላቀሉ ሰዎች ከተወለዱበት ፣ ካደጉበት ማህበረሰብ ፣ ከተማሩት ትምህርት፣ ከኖሩበት የኑሮ ደረጃና የግንኙነት መጠን የራሳቸው ባህርይ ይኖራቸዋል ፤ በተቻለ መጠንም ራሳቸውን ከተሳሳተ ቅድመ ግምት ጠብቀው መነሳት ይኖርባቸዋል።መጀመሪያም ሲነሱ ምን ለመሥራት ነው ቁጭ ያልኩት በሥራዬ ምን ዓይነት ውጤትን ማምጣት አስባለሁ አገሬን እንዴት አድርጌ አሻግራታለሁ የሚለውን ቁልጭ ባለ መልኩ ሰንደው አዘጋጅተው መነሳት ቢችሉ ጥሩ ነው።
እስከ ዛሬ ድረስ በጉልበት ሞክረናል። በንትርክም ያሳለፍነው ጊዜ ቀላል አይደለም፤ እስከ አሁን ያልሄድንበት መንገድ ምክክርና ንግግር ብቻ ነው፤ አሁን ደግሞ እስቲ እሱን እንሞክረውና ውጤቱን እንየው የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፤ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶችም ሌላውም ቢሆን ሃሳቡን ተቀብለን ለተፈጻሚነቱ የምንጥር ከሆነ ውጤት የማናመጣበት የማይሳካበት ምክንያት የለም። ብዙ ነገሮች የተፈጠሩበት ደቡብ አፍሪካ እንኳን በዚህ መንገድ ሄደው ስኬትን ተጎናጽፈዋል።
በመሆኑም እኛም እናሳካዋለን። እስከ አሁን በተለያዩ አካላት ላይ መጠናቸው ቢለያይም ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል። ነገር ግን በዚህ መቀጠል ጥፋቱን እጥፍ ድርብ የሚያደርገው ስለሆነ ችግሮችን ባሉበት አቁሞ ሁሉም እንደ ጥፋቱ ቢክስ የሌላው ችግርና ቁስል እንዲሰማው ቢሆን ጥሩ ነው። ከዚህ በኋላም በሚያጋጥሙን በእያንዳንዱ ክስተት ውስጥ መርጦ አልቃሽነታችንን ትተን መጥፎ ነገሮችን በሙሉ በማውገዝና በመኮነን ኃላፊነታችንን ብንወጣ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ፓስተር ጻድቁ፦ እኔም አመሰግናለሁ::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥር 12/2014