ጥር አንድ ቀን 2014 ዓ.ም፣ ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆቿን ሸልማለች፤እውቅና ሰጥታለች፡፡ ለክብሯና ለነፃነቷ ሲፋለሙ በክብር የተሰዉላትን ልጆቿን ጭምር ስማቸው በሥራቸው ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ እንዲታወስ በክብር ጠርታቸዋለች:: የአገር ዘብ የሆነው ጀግናው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት አባላቱ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት እና በ‹‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› ላሳዩት ጀግንነት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሽልማቶቹ በመከላከያ ደረጃ በአዋጅ የተፈቀዱትን ያካተቱ ሲሆን፤ በሦስት ደረጃዎች ተለይተው የቀረቡ ናቸው፡፡ የሜዳሊያ (የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ አንደኛ ደረጃ፣ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ እና የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ) ይባላሉ፡፡ ለላቀ የሥራ ውጤት የሚሰጠውን ሽልማትን፣ የዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ሽልማትን እንዲሁም ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ሽልማት ለጀግኖቹ ተሰጥቷል፡፡
በርካታ ጀግኖች እንደየሥራ አፈፃፀማቸው ከላይ የተጠቀሱትን ሽልማቶች ያገኙ ሲሆን፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጄኔራል ባጫ ደበሌ እና ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ደግሞ ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡ ለዛሬ ከእነዚህ በርካታ ጀግኖች መካከል ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ የሆኑ ባለውለታዎቻችንን የጀግንነት ጀብዱ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
በአሁኑ ወቅት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው አገራቸውን እያገለገሉ የሚገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለልቻ፣ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች የአገር ውስጥ ግዳጆችንና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በውጤታማ የአመራር ብቃትና ብስለት ፈፅመዋል፡፡ በለውጡ ወቅት ‹‹የሕዝብ ጥያቄ በኃይል መገታት የለበትም›› የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ በወቅቱ ሕዝቡን ለማፈን የተዘጋጀውን እቅድ በግልፅ ተቃውመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአደናቃፊነት ተፈርጀው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ግፊት የሚያደርጉ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እርሳቸው ሥርዓትን ለማቆየት ሲባል በሕዝብ ላይ የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎችን መቃወማቸውን ቀጥለው ነበር፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አሸባሪው ሕወሓት ትንኮሳዎችን ሲጀምር ወደ ጠላት ወጥመድ ላለመግባት በትዕግሥት የታጀበ የበሰለ አመራር ሰጥተዋል፡፡ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅሞ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ አረመኔያዊ ተግባር ሲፈፅም ልባቸው በኃዘን ቢሰበርም የማይደፈሩ የሚመስሉ የውጊያ እቅዶችን በመንደፍ የሠራዊቱን የመፈፀም አቅም በአጭር ቀናት ውስጥ ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግረዋል፡፡ በዚህም በምዕራብ፣ በምስራቅና በደቡብ ቀጣናዎች በሽምቅ ውጊያ ቁመና ላይ የነበሩትን የመከላከያ እዞችን በጥቂት ቀናት ውስጥ በማዘጋጀት አንቀሳቅሰው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በጠላት የተወሰዱበትን ትጥቆች ለማስመለስና ጠላት ጦርነቱን ወደ አጎራባች ክልሎች አስፋፍቶ አገር የማፍረስ እቅዱን እንዳያሳካ በፍጥነት የአገር ህልውናን የማስጠበቅ ተግባር አከናውነዋል፡፡
ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፅም ጦሩ ወደ ኤርትራ እንዲያፈገፍግ ትዕዛዝ በመስጠት የአገሪቱን ከፍተኛ ጦርና መሳሪያ ከመታደጋቸውም በላይ ጠላት እንዳይጠቀምባቸው የማድረግ አመራር ሰጥተዋል። ወደ ኤርትራ አፈግፍጎ የነበረውና ከጥቃት የተረፈው ኃይል መልሶ እንዲሰባሰብና እንዲደራጅ የሚያደርጉ አመራሮችን በማሰማራት ሠራዊቱ መልሶ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚህም ጦሩ ወደ መልሶ ማጥቃት እንዲገባ አድርገዋል፡፡
ጠላት ‹‹ውጊያውን ከትግራይ ውጭ አደርገዋለሁ›› የሚለውን እቅዱን በማክሸፍም በሁለት ሳምንታት ውስጥ የስበት ማዕከሉን መቆጣጠር እንዲቻል በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡ ጦርነቱ መቀሌ ከተማ ውስጥ እንዳይካሄድና ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ለማድረግ በተቀየሰው ስልትም ዋና ሚና ነበራቸው፡፡ የመከላከያ ቀዳሚ መምሪያ መቀሌ ላይ እንዲቋቋም በማድረግ ሠራዊቱ የቅርብ አመራር እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ ቀዳሚ መምሪያውና ጠቅላይ መምሪያው እንዲተሳሰሩ በማድረግ ውጊያው በከፍተኛ ጥበብ እንዲመራ አድርገዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱን ትኩረትና ኃይል በመበታተን ዋና ዋና ኮሪደሮችን የመቆጣጠር ሕልም የነበረው ጠላት ሕልሙ እንዳይሳካ በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ተግባራቸው ቀጣናው እንዲረጋጋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕወሓት ወረራውን ወደ አማራና አፋር ክልሎች ባስፋፋበት ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በርካታ ኃይል በማሰልጠንና በማስታጠቅ የወገን ኃይል አስተማማኝ የኃይል የበላይነት እንዲኖረውና ውጊያውን ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንዲያሸጋግር በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች አገራዊ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮችንም በመምራትና በማስተባበር አስደናቂ አመራር የሰጡ ናቸው፡፡ በዚህ አስተዋፅኦዋቸውም ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ብሔራዊ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ጄኔራል አበባው ታደሰ
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ከለውጡ በፊት በጦር ሜዳ ጀግና፤ በሰላም ቀጠናው ደግሞ የተረጋጉ በሳል መሪ በመሆን በሠራዊቱ ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ የሠራዊቱን እዞች በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበብ መርተው በርካታ ኢትዮጵያዊ ጀግኖችን ኮትኩተው ያሳደጉ የአገር ባለውለታ ናቸው፡፡ ሠራዊቱን በዘር በተዘረጋ ኔትወርክ ጠፍንጎ ይዞት የነበረው የሕወሓት አስተዳደር፣ ጄኔራሉ ብዙ ሊሠሩ በሚችሉበት ብቃትና እድሜ ላይ ሳሉ ከሠራዊቱ በጡረታ እንዲሰናበቱ አደረጋቸው፡፡ በጡረታ ላይ ሆነው የሚወዷትን አገራቸውን ሁኔታ በቅርበት ይከታተሉ ነበር፡፡ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፅም የተደረገላቸውን አገር የማዳን ጥሪ ተቀብለው አያሌ የጀግንነት ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡
ጄኔራል አበባው በቀጥታ ወደ ሰሜን በማምራት ከፍተኛ የሞራል ጉዳት ደርሶበት የነበረውን ጦር እንደ አባት በፍቅር፤እንደተዋጊ በወኔ በመምራት ለግዳጅ አነሳስተው በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ መልሶ ማጥቃት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ በዚህ የወገን ማጥቃት በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማድረስ የወገን ኃይል የበላይነት እንዲላበስ ማድረግ ችለዋል፡፡ መቀሌ ላይ የተቋቋመውን ቀዳሚ መምሪያ በመምራት የጁንታው የበላይ አመራሮችና ጀሌው እንዲደመሰሱ እንዲሁም ከተደበቁበት ጉድጓድ ውስጥ እንዲለቀሙ አድርገዋል፡፡
ጠላት ከሰሜን ዕዝ የነጠቃቸውን መሳሪያዎች እንዲመለሱና አግቷቸው የነበሩ በርካታ የወገን ጦር አባላት (መኮንኖችን ጨምሮ) ነፃ እንዲወጡ ያስቻለ የተሳካ ኦፕሬሽን እንዲፈፀም አመራር ሰጥተዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ መንግሥት ያወጀውን የተኩስ አቁም እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥሮ ወረራውን ወደ አማራና አፋር ክልሎች ባስፋፋበት ወቅት ጠላት ዋና ዋና ኮሪደሮችን ለመቆጣጠር የተፋለመበት እቅዱ እንዳይሳካ ያስቻለ በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡
የሕወሓት ኃይል ከአማራና አፋር ክልሎች ተጠራርጎ እንዲወጣና በከበባ እንዲቀጠቀጥ የጄኔራል አበባው የአመራርነት ሚና የላቀ ነበር፡፡ የግንባሮች እንቅስቃሴ ያለአንዳች የመረጃ ፍሰት ችግር እንዲከናወን በማድረግና በየደረጃው ያሉ አዛዦችን አፈፃፀም በመከታተል የላቀ የመሪነት ችሎታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ምርጥ መሪ ናቸው፡፡ ጀኔራል አበባው ያሰቡትን ሳያሳኩ የማያርፉ፣ ለአስቸጋሪ ፈተናዎች የማይበገሩ፣ በተረጋጋ ሁኔታ የችግርን መፍትሔ የሚያስቡና ልበ ሙሉ የሆኑ የጦር መሪ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ጄኔራል አበባው ኢትዮጵያ ድል እንድታስመዘግብ ያስቻሉ ጀግና የጦር መሪ በመሆናቸው ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ብሔራዊ ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ጄኔራል ባጫ ደበሌ
ጄኔራል ባጫ ሰራዊቱ የተሟላ ወታደራዊ ቁመና እንዲይዝና በዲስፕሊን የታነፀ እንዲሆን ያልተቋረጠ ጥረት አድርገዋል፡፡ የሚመሩትን ሠራዊት እንደአባትም እንደአለቃም በመሆን የሚመሩ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ጄኔራል ባጫ በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል በአዛዥነት ባገለገሉባቸው ዓመታት የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደምሰስ በሳል አመራር ሰጥተዋል፡፡ የሚመሩት ሠራዊት ወታደራዊ ቁመናው እንዲስተካከል በማሰልጠንና በማብቃት እጅግ አኩሪ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራሉ ብዙ ሊሠሩ በሚችሉበት ብቃትና እድሜ ላይ ሳሉ የሕወሓት አስተዳደር ከሠራዊቱ በጡረታ እንዲሰናበቱ አደረጋቸው።
በግል ሥራና በጡረታ ላይ ሳሉ ግፈኛው ሕወሓት ጄኔራሉ በሚወዷትን አገራቸው ላይ ጥቃት ፈፀመ። ጄነራል ባጫም ወደ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ሄደው ‹‹እኔ በሕይወት እያለሁ ይህን ክህደት ቆሜ መመልከት አልችልም›› በማለት ለማንኛውም ወታደራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡ በማግሥቱም በመንግሥት የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኤርትራ አመሩ፡፡ በዚያም በዛላንበሳና በፆረና እየተዋጋ የወጣውን ሠራዊት አሰባስበውና አደራጅተው ለመልሶ ማጥቃት እንዲዘጋጅ አድርገዋል፡፡
በአፋርና በሰሜን ወሎ ለግዳጅ የተሰማራውን የወገን ኃይል አደራጅተው አሸባሪው ኃይል እንዲደመሰስ ከጓዶቻቸው ጋር አመራር ሰጥተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ሥራዎችን አቀናጅተው እንዲተገበሩ አድርገዋል። ሰራዊቱ የጠላት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን፣ የጦሩን ገድል በየወቅቱ ለሕዝቡ በማድረስ ተዋጊው ኃይል በሞራል ከፍ እንዲል ያስቻሉ ወታደራዊ መኮንን በመሆናቸው ከፍተኛው ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ብሔራዊ ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ
በሐረር እና በገነት ጦር አካዳሚዎች ወታደራዊ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ለከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት ወደ ሶቭየት ኅብረት ሄደው በሌኒንግራንድ መድፈኛ አካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለው የአካዳሚው ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑ ጀግና ናቸው፡፡ የሶማሊያን ወረራ በመመከት ታላቅ ገድል ፈፅመዋል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው በጀግንነታቸው አገራቸውን አስከብረዋል፡፡ የጥምር ጦር ውጊያ መሐንዲሱ ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት፤የአየር ወለድ ውጊያን ከአየር ኃይል ጥቃት ጋር አቀናጅተው በፈፀሟቸው ጀብዶች ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነውም አገልግለዋል፡፡
ከሃዲው ሕወሓት የአገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል በነበረበት ወቅት ይህን ታላቅ የጦር ጠቢብ አስሮ አንገላቷቸዋል፤ማዕረጋቸው ተገፍፎ ከሠራዊቱ እንዲሰናበቱም አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሠልጣን ከመጡ በኋላ የጀግናው ማዕረጋቸው እንዲመለስላቸውና ጡረታቸውም እንዲከበርላቸው አድርገዋል፡፡ ጀግና ወታደር ምንጊዜም ቢሆን አገሩን ያስቀድማልና በተፈፀመባቸው በደል ቂም ያልያዙት ጀግናው ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት፤ የተደረገላቸውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ከሃዲው ቡድን አከርካሪው እንዲሰበር አድርገዋል፡፡
በከሃዲው የሕወሓት ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀመር ጠላትን ድባቅ ለመምታት በዘመናዊ ወታደራዊ ትምህርትና በልምድ የታገዘ የጦር አመራርና ውጊያ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ የውጊያ ስልጠናና ልምድ ካላቸው ወታደራዊ አዛዦች መካከል አንዱ ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ነበሩና ጀኔራሉ የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ብርቱና ቆራጥ የሆነ ተጋድሎ ፈፅመው አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል፡፡ ጄኔራል መኮንኑ ባላቸው የዳበረ የሜካናይዝድ ጦር አመራር ብቃት የጠላት ኃይል፣ በተለይ በራያ ግንባር ከባድ ምት እንዲያርፍበት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ‹‹በምስራቅ በኩል በተለይ ከባድ መሣሪያን በማስተባበር ሥራ የጀመረው ወታደራዊ ሊቁ ጄኔራል ዓለምእሸት ነበር›› ብለው የመሰከሩላቸው ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት፤ በራያ ግንባር የከባድ መሳሪያዎች አስተባባሪ ሆነው የተካኑበትን የውጊያ ስልት በመተግበር ጠላትን ዶጋ አመድ አድርገውታል፡፡ በመድፍና በሜካ ናይዝድ ኃይል የተቀናጀ እቅድ በመንደፍ በአፋር በኩል አድርጎ ወደ ትግራይ ዘልቆ የገባውን የመከላከያ ሠራዊት ኃይል መርተዋል፡፡ በዚህ የላቀ ችሎታ ጠላትን እየደመሰሱ ገስግሰው ከጄኔራል ባጫ ደበሌ ጦር ጋር ማይጨው ላይ ተገናኝተዋል፡፡ ተራሮችን እየሰነጠቀ፣ አለቱን እየሰባበረና ገደሉንም እየዘለለ ከምዕራብና ከሰሜን አቅጣጫ ከመጣው የጀኔራል አበባው ታደሰ ጦር ጋር መቀሌ ገብተዋል፡፡
የጦር ሊቁ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሄዋነ ላይ በሰጡት መግለጫ፡- ‹‹ … ወጣ ገባ የሆነው መሬት ጠላት እመክትበታለሁ፤አቆምበታለሁ ብሎ ያሰበበት ቦታ ነበር፡፡ ያሉንን መሣሪያዎች በማስተባበር በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በአካባቢው መሽጎ የነበረው ኃይል ለሦስት ቀናት ያህል መራራ ውጊያ ካደረገ በኋላ ተፍረክርኮ እንዲበተን ማድረግ ተችሏል፡፡ … ውጊያ ማለት ተኩስና ንቅናቄ ነው፡፡ ንቅናቄውን የሚሰራው እግረኛው ነው፤በእርግጥ ሜካናይዝዱም ይነቃነቃል፡፡ ግን ዋናው ሥራ ተኩስ ነው፡፡ ተኩስ በጥሩ ሁኔታ ከተሠራ ጠላት በሙትም በቁስለኛም ጉዳት ይደርስበታል። ለእግረኛው ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል፡፡ ይህ ሥራ በሚገባ በመሠራቱና ጠላት በሚገባ በመመታቱ ሸሽቶ ሄዷል … በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝባችን የድል ብስራት እናሰማለን ›› ብለው ነበር፡፡ በተናገሩት የጀግና ቃላቸው መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድል ብስራት አሰምተዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት በትግራይ የተቋቋመው የመከላከያ ቀዳሚ መምሪያ አባል በመሆንም የሕወሓት አመራሮችን ለማደንና የተበታተነውን ኃይሉን ለመደምሰስ ለተካሄዱ የዘመቻ እቅዶች እንዲሁም ለመከላከልና ለፀረ-ማጥቃት የውጊያ ስልቶች ሲነደፉ የዳበረ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት በካበተ ልምዳቸውና በውጊያ ችሎታቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 11/2014