ትውልድና እድገታቸው በቆጮ ተክሎች በተዋበችው በጉራጌዋ ምድር ሶዶ ዘሙቴ በምትባል አካባቢ ነው። የእርሳቸውን በቅቤ የተለወሰ የስጋ ክትፎ የቀመሱ ሰዎች የእጃቸውን ሙያ ሲያደንቁ ግማሽ ምዕተ ዓመትን አሳልፈዋል። የእናትነት ባህሪያቸው ከነጋዴነታቸው የበለጠ ዘለቆ ይሰማል የሚሉት ደግሞ በጉርሻቸው ፍቅር የወደቁት ደንበኞቻቸው ናቸው። ወይዘሮ በቀለች በሯዋቅ ይባላሉ። ዝናው ከአዲስ አበባ አልፎ በአውሮፓ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን / ዳያስፖራዎች/ ዘንድ የናኘው የበቀለች ክትፎ ቤት ባለቤት ናቸው። በልጅነታቸው ለእናታቸው ስፌት እና የሸክላ ምርቶችን በማዘጋጀት ያግዙ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እናታቸው ጠንካራ ሠራተኛ ናቸውና በአራት አህያ ቆጮ እና ቡላውን ጭነው አዲስ አበባ ድረስ እየመጡ ይሸጡ ነበር። ይህ ለእርሳቸው ተምሳሌትነት የሆነ ጥንካሬና ለሥራ ያላቸውን ፍቅር እንዳሳደገው ያስታውሳሉ። ወይዘሮ በቀለች ገና በ14 ዓመታቸው ነበር የተዳሩት። በወቅቱ በአገሩ ባህል መሰረት እናታቸው ለድግስ የሚሆን 30 ብር ለአማቻቸው ይልካሉ። ገንዘቡ የደረሳቸው አማቻቸው ግን ድግሱን እንጂ ብሩን አልፈልግም ብለው 30ውን ብር ሙሽሪት ፊት ላይ ወርውረው ይወጣሉ። ወይዘሮ በቀለች ግን የተወረወረባቸውን 30 ብር ይዘው ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለትልቅ ዓላማ ተነሱ።
በገንዘቡ ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን አሰናድተው ሶዶ ውስጥ አነስተኛ ምግብ ቤት ከፈቱ። ዘመኑ በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ነውና ሴት ምግብ ቤት ከፍታ በመሥራቷ የምትደነቅበት አልነበረም። ይልቁንም ግርምት የሚፈጥር በመሆኑ ብዙ ፈተናዎች ታግሰው በስሙኒ ምግብ መሸጥ ቀጠሉ። በየቀኑ 50 ሳንቲም ትርፍ ስለሚያገኙ እሷኑ በቆርቆሮ ሳጥን ይደብቋታል። ይሁንና ለአንዱ የቆጠቡትን ለአንዱ የቤት ወጪ ያውሏት ስለነበር ስምንት ዓመት ሠርተው ትርፋቸው 30ብር ብቻ ነበር። ከዚያም እህታቸው ወላይታ ሶዶ ነበረችና ወደዚያው ለሥራ አቀኑ። በወላይታ ጠጅ እና አልኮል መጠጦችን ሲነግዱ ቆዩ።
«እንጀራ ሲሸሸኝ እኔ ስከተል፣ ስንዝር መሬት ቀረኝ ገደብን ልዞር» የሚለው ግጥም እርሳቸው ላይ እንደሠራ የሚናገሩት ወይዘሮ በቀለች የእህል ውሃ ነገር ሆነና ከዚያ ደግሞ ለሥራ ወደጅማ ማምራታቸውን ያስታውሳሉ። ጅማ ላይ ደግሞ እንጀራ እየጋገሩ ሦስቱን በሃያ አምስት ሳንቲም መሸጥ ጀመሩ። በአምስት ዓመት የጅማ ቆይታቸው በእንጀራ ንግድ ያፈሩትን ጥሪት ሰባስበው 20 መሃለቅ ወርቅ ገዙበት። ወርቁን ይዘው ደግሞ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ አመሩ። ከአንዱ ከተማ ወደ አንዱ ሲወስዳቸው የነበረው የህይወት መስመር አዲስ አበባ ላይ ለመከተም አስገድዷቸዋል። በመዲናዋ ከጅማ የያዙትን መሃለቅ ወርቅ አንዱን በሦስት ብር ሸጠው ያገኟትን ገንዘብ እና ሌላም ተጨማሪ ገንዘብ ከወዳጃቸው ተቀብለው ካዛንቺስ አካባቢ አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ንግድ ጀመሩ። ዳቦ ቆሎ እና ሚጥሚጣ እያዘጋጁ ሸጠዋል። ሌሎች ምርቶችንም ከገበያ እየገዙ ያቀርባሉ።
ይሁንና የሱቋ ገበያ አዋጭ አልሆነም። በወር 50 ብር ለሱቅ ኪራይ ስለሚከፍሉ አከሰራቸው። መውደቅ እና መነሳት በንግድ ዓለም ያለ መሆኑን የተረዱት ወይዘሮዋ አዲስ የንግድ አማራጭ ሲያማትሩ አዋጭ እንደሚሆኑ ያመኑበት መላ ዘይደዋልና ሱቋን ወደ ክትፎ ቤት ቀየሯት። የጥንቷ በቀለች ክትፎ ቤት በካዛንችስ መሃል ሥራ ጀመረች። የዛሬ 50 ዓመት አንድ ክትፎ በ50 ሣንቲም ነበር የሚሸጠው። ለክትፎ የሚሆነውን ሥጋ ደግሞ ከአራት ኪሎና ከቀጨኔ አለፍ ሲልም ከዱከም ድረስ ያስመጡ ነበር። ንቅል ሥጋ ተሸክመው መርካቶ ይገቡና በዘጠኝ ቁጥር አውቶቡስ ተሳፍረው ካዛንችስ ይደርሳሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ እስከ አንድ ብር ድረስ ክትፎ እየሸጡ ታዋቂ ክትፎ ቤት ቢኖራቸውም ትርፉ ግን ድካም ብቻ ሆነባቸው።
በዚህ ጊዜ የቀድሞውን ቤት ለቀው እዚያው ካዛንቺስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ አንድ ግቢ ተከራዩ። የክትፎውን ዋጋ በአንድ ብር ከ50 ሣንቲም መሸጥ ቀጠሉ። ይሄኛው ቦታ ከእርሳቸው የሥራ ጥንካሬ ጋር ተዳምሮ ለገበያም አመቺ፤ ለትርፍም ቀና ሆነላቸው። ጥቂት ጥሪት መያዝ ሲጀምሩ 22 አካባቢ አንድ ቦታ ካሬውን በ17 ብር ሂሳብ 860 ካሬ ሜትር ቦታ ገዙ። በቦታው አንድ ቤት ሠርተው ክትፎ ቤታቸውንም ከካዛንቺስ አዘዋወሯት። አሁን ለቤት ኪራይ የሚሆን ክፍያ የለባቸውም። በመሆኑም ሙሉ ትኩረታቸው የክትፎ ደንበኞቻቸውን ለማስደሰት አደረጉ።
ገበያው በወረፋ ሆነ። በ22ቱ ክትፎ ቤት ማለትም ከ30 ዓመት በፊት እስከ 22 ሠራተኞች ተሰማርተው ደንበኞችን ሲያስተናግዱ ይውላሉ። በወይዘሮ በቀለች ዋና አለቃነት የሚመራው ክትፎ ቤት ትርፍ በትርፍ ላይ እየጨመረ። ከሚሊየነሮች ተርታ አሰለፋቸው። አሁን የሚሊየነርነት ደረጃ መድረሳቸው ያስደስታቸዋል። ይሁን እንጅ በየወቅቱ ያሳለፏቸው ፈተናዎችን ዛሬም ድረስ አይዘነጉም። ከከባድ ፈተናዎቻቸው መካከል ሆነውም በየወሩ እቁብ የሚጥሉለት የቀበሌ ሊቀመንበሩ ጉዳይ መቼም አይረሳቸውም። በደርግ ጊዜ የቀበሌ ሊቀመንበር የሆነ አንድ ሰው በየሳምንቱ የሦስት መቶ ብር እቁብ ያስጥላቸው ነበር። የእቁቡን ብር ሲጠይቁት ይክዳቸዋል። እርሳቸውም መብታቸውን ተገፈው ጠያቂ በሌለበት ለሦስት ዓመታት እቁቡን እንደጣሉለት ያስታውሳሉ። ሂሳቡን ሲያሰሉት በወር 1ሺ ሁለት መቶ ብር በዓመት ደግሞ 14ሺ 400 ብር ነው።
ይህን ያህል ገንዘብ በወቅቱ ቢጠቀሙበት ኖሮ አሁን ላይ የበለጠ ሊመነደጉ የሚችሉበት እድል እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። የሆነ ሆኖ ጊዜውን በጽናት አልፈው ለዚህ ዘመን ደርሰዋል። በተጨማሪ በክትፎ ቤታቸው ውስጥ የደረሰውን የጥይት እሩምታ ከፈተናዎቻቸው መካከል ከከባዶቹ ውስጥ ይመድቡታል። ወቅቱ የደርግ ጊዜ ነው ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት አስከፊ ጊዜ ነውና ክትፎ ቤታቸው በር ላይ አንድ ወታደር ይገደላል። በጊዜው ወታደሩን የገደለው ከእርሳቸው ቤት የወጣ ሰው ነው ተብሎ ተጠቁሟል። አንድ አስር አለቃ ደግሞ ክትፎ ቤቱ ውስጥ ገብቶ ከጣሪያው ጀምሮ እስከ መስታወቶቹ ድረስ በጥይት እሩምታ ቤቱን አተራመሰው። ዕቃዎቹንም ፈጃቸው። ይህ ሁሉ ፈተና ካለፈ በኋላ ታዋቂው ክትፎ ቤት እንደወትሮው በደንበኞች ሲጨናነቅ ቀናት አልፈጀበትም።
ምክንያቱም የክትፎ አሰራር ሙያቸውን የሚወዱ ደንበኞች እርሳቸውን ብለው መምጣታቸው አይቀርምና። ገበያው ሲደራ ልበ ጠንካራዋ ነጋዴ 22ና ሾላ አካባቢ መኖሪያ ቤት ገዝተው ከብት ማርባት ጀመሩ። ይሁንና አሁንም የንግድ ህይወታቸውን የሚፈታተን ጊዜ መጣባቸው። ይሁን እንጅ ፈተናውን በጽናት ለማለፍ ተዘጋጅተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ ከዘጠኝ እና እስር ዓመት በፊት መሬት በሊዝ የሚሸጥበት እና አቅም የሌለው አፍርስ እየተባለ አቅም ላለው የሚሰጥበት ጊዜ ነበር። ክትፎ ቤታቸው አደጋ ላይ ወደቀች። አንድም ቦታው ለባለፎቅ ሰሪዎች የሚሆን ነውና አፍርሰው ይሥሩበት ሲባሉ በሌላ በኩል ደግሞ ያንን ለማድረግ በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው ሲያስቡ መላ ዘየዱ። እጃቸው ላይ ያለውን አራት ሚሊዮን ብር እና አንደኛውን ቤታቸውን ሸጠው ያገኟትን ገንዘብ ይዘው ቀድመው የሚያውቋቸው ጣሊያኖች ቤት አመሩ።
በከተማዋ ታዋቂ የሆኑት ጣሊያናዊ ግለሰቦች ‹‹ቤቴ በሊዝ ምክንያት ከሚወሰድብኝ ሆቴል ልገነባ አስቤያለሁና እንተጋገዝ›› ብለው አማከሯቸው። በጉዳዩ የተስማሙት ጣሊያናዊ ወዳጆቻቸው በ22 አካባቢ ባለ አምስት ወለል ሊገነባ የታሰበውን ሆቴል መሰረት ለማውጣት እና ለመገንባት ተስማሙ። ሰርቼ እከፍላለሁ ብለው የተነሱት ጠንካራዋ ወይዘሮ አሁን በስማቸው የሚጠራ ባለ አምስት ወለል ሆቴል ባለቤት ሆነዋል። ሆቴሉ አርባ ዘመናዊ የመኝታ ክፍሎች እና ለሠርግና ለስብሰባ የሚሆኑ አዳራሾች አሉት።
ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለበርካቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። ሆቴሉ አሁን ላይ ለወይዘሮ በቀለች ጥንካሬ ምስክር ሆኖ በአዲስ አበባ ምድር ላይ ከፍ ብሎ ይታያል። ሆቴሉ ባለአራት ኮከብ ደረጃ እንዲያገኝ ተደርጎ የተገነባ ነው። በቅርቡ ደረጃው ይሰጠዋል ብለው እንደሚጠብቁ የሚናገሩት ወይዘሮ በቀለች፤ የማጠናቀቂያ ግንባታ ሥራው ላይም እየተሳተፉ ይገኛል። ከልጅነት የጀመረው የሥራ ፍቅር አሁንም በስተርጅና አልለቀቃቸውም።
ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ከጽዳት ጀምሮ ያሉትን ሥራዎች ሁሉ ይሠራሉ። ምንም እንኳን የሆቴል ግንባታው ላይ 26 ሚሊዮን ብር እዳ ቢኖርባቸውም አሁን ላይ አጠቃላይ ሀብታቸው 90 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይገልፃሉ። ከሰላሳ ብር የተነሳው ህይወታቸው በርካታ ሥራዎች ላይ ቢያሰማራቸውም አሁንም የበለጠ ለአገራቸው ለማበርከት ሥራ ሳይንቁ እንደሚሠሩ ይናገራሉ። ‹‹ለልጄ ብዬ የማቆየው ነገር የለም፤ ሁሉም ለአገሬ ልማት ነው። የእኔ ብቻ ማደግ አያኮራኝም ምክንያቱም ብቻየን ማጌጥ ሳይሆን ከአገርና ከህዝብ ጋር ማደግ ነው የሚያኮራው›› ይላሉ። ለሆቴላቸው የሚሆኑ እቃዎችን ለመምረጥ ቻይና በሄዱበት ወቅት እንዳለቀሱ የሚናገሩት ወይዘሮ በቀለች።
ለቅሶው ያቺ አገር ያን ያህል አምራና አድጋ ሲያይዋት ኢትዮጵያስ ለምን እንደዚህ አልሆነችም? ከሚል የቁጭት ስሜት የመነጨ መሆኑን ያስረዳሉ። ከማንም ያላነሰ የተፈጥሮ ሀብት እና ቅርሶች እያሉ በትጋት ሠርቶ መለወጥን ማሰብ የማንም ሰው ግብ መሆን እንዳለበት ያምናሉ። ሠርቶ ለመለወጥ ነግዶ ለማትረፍ ለሚነሳሱ ሁሉ የሚለግሱት ምክር አላቸው። ሰዎች ከወሬ ይልቅ ትጋት ላይ፤ ከነገር እና ምቀኝነት ይልቅ ደግ መሥራት ላይ ያተኮረ ህይወት ይኑራቸው ይላሉ። «ፈተናን እየታገሰ ኪሳራንና ውድቀትን እያለፈ የሚሠራ ሁሉ ለብልጽግና መድረሱ አይቀርምና ስንፍናን ወዲያ ጥለን እንጓዝ። ለኢትዮጵያችን ከብረት የጠነከረ ሠራተኛነት ያስፈልጓታልና እኛው ማገር እንሁናት» መልእክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 3/2011
በጌትነት ተስፋማርያም