ምን ላይ እንደሆነ ዘነጋሁት እንጂ «ከምታየው ሁሉንም ከምትሰማው ግማሹን እመን» የሚል ጥቅስ አንብቤ ነበር። «ማየት ማመን ነው» የሚለውን የወል አባባል ልጨምርበት። የሁለቱም አባባሎች መልዕክት ተመሳሳይ ነው። ከምንሰማው ነገር በምናየው ነገር እንተማመናለን። በተለያየ አጋጣሚ የትግራይ ተወላጅ ጓደኞች አሉኝ።
የትግራይን ምድር ግን አይቼው አላውቅም ነበር። ከሰሞኑ አየሁት ለማለት ነው። ማየት ቢሏችሁ ደግሞ ዝም ብሎ ጫፍ ደርሶ መመለስ አይደለም፤ ወይም በአውሮፕላን መቀሌ ደርሶ መምጣት አይደለም። በአላማጣ ገብቼ፣ በማይጨው አድርጌ፣ ገደላማና ሰንሰለታማውን የትግራይ ምድር አቋርጬ፣ ደጋውንም ቆላውንም የተምቤን ለምለም ምድር ረግጬ፣ ጠጄን ጠጥቼ፣ መቀሌን ዘወር ዘወር ብዬ አይቼ፣ ዓድዋንና አክሱምን ዳስሼ ነው የመጣሁ ብላችሁ ታምናላችሁ? ይሄ ሁሉ በአንድ ጉዞ? አዎ በአንድ ጉዞ! ለዚያውም ስማቸውን ባልጠቀስኳቸው ቦታዎች ሁሉ ብዙ ነገር እያየሁ ነዋ! ዳሩ ግን ከአዲስ አበባ ተነስቼ አክሱም ለመድረስ ሰባት ቀናትን ተጠቅሜያለሁ።
ሰባቱንም ቀን በጉዞ! በቃ ከሰኞ እስከ ሰኞ(ከእሁድ እስከ እሁድ አለ ጎሳዬ) ጉዞ ነበር። መሃሉ ብዙ ስለሚያስወራ ለዛሬው አንድ ነገር ላይ ብቻ ላተኩር። የትግራይ ወጣቶች ላይ የታዘብኩት ነገር። ከመግቢያዬ ልነሳና ‹‹ማየት ማመን ነው›› የሚለው አባባል ብዙ ነገር ግልጽ አድርጎልኛል። የአገራችን ፖለቲካ የተጨመላለቀ ነው። ሀቀኛ ባለሥልጣንና ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ሽማግሌም አጥተናል። ባለሥልጣንና ፖለቲከኛ በአክቲቪስት ተጠልፏል። ሀቀኛ ፀሐፊም አጥተናል።
በመንጋ መነዳት ግልጽ የሆነ ብልሽት እያደረሰብን ነው። የዘንድሮውን ዓድዋ ልብ ብላችሁ እዩት! ስለትግራይ ብዙ ነገር ተብሏል። ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያለው ነገር በግልጽ ያየነው ነው። አንዳንዱ «የትግራይን ሕዝብ ከሕወሓት ለዩ፣ የትግራይ ሕዝብ ምስኪን ነው» ሲል የተቀረው የለም «ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተሳሰሩ ናቸው» ይላል።
ይሄ ነገር እንደኔ ትግራይ ሄዶ ለማያውቅ የሚፈጥረውን ስሜት አስቡት! በሥራ አጋጣሚ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሄጃለሁ (ትግራይ ግን የመጀመሪያዬ ነው) የፈለገውን ያህል ይግረማችሁ የትግራይ ሕዝብ የተሻለ ሆኖ ነው ያገኘሁት(ያላመነ ሄዶ ማየት ነው) የሕዝቡ የዋህነትና ቅንነት ሲያስገርመኝ አንድ ነገር አሰብኩ። እነዚህ ሰዎች በወቅታዊው ፖለቲካ ስማችን ጠፍቷል ብለው ስላሰቡ ለማካካስ ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ለዚህም ለፖለቲካ ሩቅ ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ሳስተውል ነበር።
ለምሳሌ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሌለበት በረሃ ውስጥ የሚኖሩ ምስኪን ነዋሪዎች፣ በቀላል ሥራዎች ሲከፋም በልመና ላይ የተሰማሩ ሰዎች የማህበራዊ ገጾች መርዝ አይደርሳቸውም። የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና ማስተዋል የሚቻለው ከእነዚህ ሰዎች ነው። አንድ በጫማ መጥረግ ሥራ ላይ ያለ ወጣት አንድ ቦታ ብትጠይቀው ‹‹በዚህ ሂድ›› አይልህም፤ ሥራውን ትቶ ቦታውን ሊያሳይህ ይሄዳል(አባቴ ይሙት በዓይኔ ያየሁት ነው)። እንደ አጋጣሚ ለእኔ ያጋጠሙኝ ይህን ስላደረጉ ብዙዎችን ሊያስመሰግን አይችልም ብዬም አሰብኩ። ከዚህ በፊት ወደእዚያ አካባቢ የሄዱ ሰዎች ሲነግሩኝ ግን የሰዎቹ ባህሪ እንዲህ ነው።
ሌላው ደግሞ የታዘብኩት ነገር አንድ ቦታ ሲጠየቁ ስለዚያ ቦታ ማስረዳት ይወዳሉ። በተለይም ቦታው ታሪካዊ ቦታ ከሆነ ልክ እንደ አስጎብኚ ማብራራት ይወዳሉ። እንዲያውም ሌላ ተጨማሪ ቦታ ጠርተው ይሄንንም ብታየው ማለት ይዳዳቸዋል። ይሄም ከአንዴም ሁለቴ ያስተዋልኩት ነው። ግብረ መልስም ይጠይቃሉ። ‹‹መቀሌን እንዴት አገኘሃት፣ ዓድዋን እንዴት አገኘሃት፣ አክሱምን እንዴት አየሃት….›› የተለመዱ ጥያቄዎች ነበሩ። ምን ዋጋ አለው ይሄንን ሁሉ የዋህነትና ቅንነት የተጨመላለቀው ፖለቲካ አፈር ድሜ እያበላው ነው። የትግራይ ወጣቶች ተመርዘዋል። የመረዛቸው ደግሞ የትግራይ አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን የመሃል አገሩ የመንጋ አራጋቢ ነው። በመሃል አገር ሲደረግ የነበረው በቀጥታ በትግራይ ወጣቶች ተደረገ።
ለምሳሌ የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ተቃጥሏል፤ ከየተሰቀለበት ይውረድ ተብሏል(ወርዷልም) ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በላይ ጨካኝና አረመኔ ተደርገው ተስለዋል። የዚህ አፀፋ በትግራይ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ተደገመ። በትግራይ ከተሞች ውስጥ የክልሉን ባንዲራ ብቻ የያዙ ብዙ ናቸው። በትግራይ ባንዲራ ቀለምና አርማ የተሠራ ልብስ ነው የሚለበስ። የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ የትግራይ ባንዲራ ምልክት አለባቸው። ወፍራሙን ጥፋት ደግሞ ልንገራችሁ። ከዓድዋ በዓል ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዕለቱ ፍጻሜ ድረስ የአጼ ምኒልክ ፎቶ በከተማዋ ውስጥ የለም። የአቶ መለስ ዜናዊና የአጼ ዮሐንስ 4ኛ ግን እዚህም እዚያም ይታያል።
በዕለቱ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከመቀሌ እስከ ዓድዋ ድረስ በእግር የተጓዙ የመቀሌና አካባቢዋ ወጣቶች ለምስጋና ወደ መድረክ ተጠሩ። ሁሉም የለበሱት ‹‹ዓድዋ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ቲሸርት ከሥሩ ያለው የትግራይ ባንዲራ ነው። የትግራይ ባንዲራ መኖሩ አስፈላጊ ነው ከተባለም ቢያንስ ለምን ከፌዴራሉ ጋር አልሆነም? የያዙት ባነር ላይ ያለው ፎቶ የአቶ መለስ ዜናዊና የአጼ ዮሐንስ 4ኛ ነው፤ አለፍ ሲልም እንደነ አሉላ አባነጋ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ብቻ ናቸው። በዓድዋ ታሪክ ውስጥ አጼ ምኒልክ ምንም ድርሻ የላቸውም ማለት ነው? ሁሉም መሪዎች የራሳቸው ታሪክ አላቸው፤ ከአቶ መለስ ዜናዊና ከአጼ ምኒልክ የዓድዋ ታሪክ ተሳታፊ ማን ነበር? ይሄ ሁሉ በስህተት የተደረገ አይደለም፤ ታስቦበት ነው። አቶ መለስ ዜናዊ በዓድዋ ጦርነት ታሪክ ውስጥ ምንም ድርሻ እንደሌላቸው እነዚያ ወጣቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ነገሩ የብሽሽቅ ፖለቲካ መሆኑን ግልጽ የሚያደርገው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ጎልቶ የሚታየው የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ነው።
የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የድሉ ከፍተኛ ባለድርሻ የራስ አሉላ አባነጋ እንኳን ጎልቶ አልታየም። ይህን ድርጊት ካስተዋሉ ጋዜጠኞች ጋር እያወራን ነበር። አንደኛው በጽኑ ተከራከረ፤ በተለይም የእናቶችን ነገር ነው የተከራከረው። ብዙ እናቶች በትግራይ ክልል ባንዲራ አርማና ቀለም የተሠራ ቀሚስ ለብሰዋል። ‹‹እነዚህ እናቶች እኮ ከቤት ሲወጡ ምንም አያውቁም›› ብሎ ነበር የተከራከረው። በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ ሳይደርሱ ከተማው ውስጥ በሰልፍ ሲሄዱ ያያቸውን እናቶች በካሜራው አስቀርቶም አሳየን። ባህላዊውን የትግራይ ቀሚስ ነው የለበሱት።
‹‹እነዚህን እናቶች ወደ መድረኩ ሲገቡ ማነው ይሄን ያለበሳቸው?›› ብሎም ተገረመ። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው እነዚህን እናቶችና ሕጻናት መርዘኛ ፖለቲከኞች እንዳበላሿቸው ነው። አዎ! በዓድዋ ድል ላይ የአጼ ምኒልክን ፎቶ አለመያዝ መበላሸት ነው። ወጣቶች ራሳቸው ናቸው ያደረጉት ብንል እንኳን እናቶችና ሕፃናት ለሴራው ምስክር ይሆኑናል። ምክንያቱም እነዚያ ሕፃናትና እናቶች አድርጉ ተብለው እንጂ የአጼ ምኒልክን ታሪክ እንኳን አውቀው አይደለም። እንግዲህ ፖለቲካችን እዚህ ድረስ ተበላሽቶልናል። የአዲስ አበባው ዓድዋም እንደእዚሁ የብሽሽቅ ነበር። እንግዲህ አስቡት! ጀግኖች አባቶች የአገርን ሉዓላዊነት ያስከበሩበትን ታላቅ ድል የመንደር አውደልዳይ ሲከፋፈልበት ማየት አሳፋሪ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በዋለልኝ አየለ