(ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው ከጻፈው የተወሰደ )
ቴዎድሮስ በፌስቡክ ከ450ሺ በላይ ተከታይ ያለው ቡክ ፎር ኦል ግሩፕ መስራች እና ደንበኛ የመጻሕፍት ቀበኛ ነው)ብዙ ከማይነገርላቸው የስነጽሑፍ ዘርፎች መካከል አጫጭር ልብወለዶች ዋነኛዎቹ ናቸው። አጭር ልብወለድ ራሱን የቻለ ሰፊ ዓለም ነው። የሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ መምህራችን እንደነገረን ከሆነ አጭር ልብወለድን ከረዥም ልብወለድ የሚለየው ዋና ምክንያት የጭብጥ ጉዳይ ነው። ረዥም ልብወለድ ከዋና ጭብጡ ባሻገር በስሩ ብዙ አጃቢ ጭብጦች ይኖሩታል።
አጭር ልብወለድ ግን አንድና አንድ ጭብጥ ብቻ ነው የሚኖረው። በተጨማሪ ረዥም ልብወለድ ብዙ ገፀባህርያት ሊኖሩት ሲችሉ የአጭር ልብወለድ ገፀባሕርያት ግን ውሱን ናቸው። ሴራውም ቢሆን የአጭር ልብወለዶች ያልተወሳሰበ ነው። የመጨረሻው መለያ ምክንያት የገፅ ብዛት ነው። ረዥም ልብወለዶች ገፆቻቸው ከጥቂት መቶዎች እስከ ሺህ ሊደርስ ሲችል የአጭር ልብወለዶች በ10 ቤት የተወሰነ ነው።
በአጫጭር ልብወለዶች ከሚጠበቡት መሐል ፈረንሳዊው ጊ ደ ሞፓሳ፣ ሩስያዊው አንቷን ቼኾቭ፣ አሜሪካዊው ኤድጋር አለን ፖ፣ እንግሊዛዊው ሶመርሴት ሞም እና ሌላኛው አሜሪካዊ ኦ ሄንሪ ተጠቃሽ ናቸው።
ለኔ ቁጥር አንድ የአጭር ልብወለድ ማስተርፒስ የጊ ደ ሞፓሳ The Necklace ወይም የአንገት ጌጡ ነው። ይህ ሥራ አንድ የተዋጣለት አጭር ልብወለድ ማሟላት ያለበትን ሁሉንም ባሕሪያቶች ይዟል። ገፀባህሪያቱ ከተአማኒነታቸው የተነሳ ከመጽሐፍ ገጽ፣ ከወረቀት ዓለም አምልጠው መሬት ላይ የሚራመዱ፣ አየር የሚተነፍሱ ይመስላሉ—በተለይ ዋና ገፀባሕርይዋ። ሴራው ምንም ወንፊት የሌለው ነው። ደራሲው ሞፓሳ በጥቂት ገፆች ለዘለዓለም አብሮን የሚቆይ ጥልቅ ቁምነገር ያስጨብጠናል። አንዳንዴ እንደዚህ አንጀት አርስ አጭር ልብወለድ ማንበብ ብዙ ገፆች ካለው ከተዝረከረከ ረዥም ልብወለድ ሺ እጥፍ የበለጠ ቁምነገር ያጋባል።
ሌላው እጅግ ተወዳጅ የአጭር ልብወለድ ስራ የኒኮላይ ጎጎል The Overcoat/ካፖርቱ ነው። ዶስቶቭስኪ ስለ ታላቋ ሩስያ ስነጽሑፍ እና ደራሲያን ሲያወራ እንዲህ አለ፦ “ሁላችንም የተገኘነው ከጎጎል ካፖርት ስር ነው” ከዶስቶቭስኪ እስከ ቶልስቶይ፣ ከቼኾቭ እስከ ሌርሞንቶቭ የጎጎል ተፅዕኖ ያላረፈበት የሩስያ አቢይ ደራሲ ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል። አካኪይ አካኪየቪች የልብወለዱ ዋና ገፀባሕሪ ነው። ይህ አይረሴ ገፀባህሪ ከባዱን የሩስያ ብርድ ለመከላከል ሲል በሚያሰፋው አዲሱ ካፖርቱ ውስጥ የሰዎችን ስነልቡና፣ የመንግሥትን ብልሹ አስተዳደር ወዘተ ያሳያል። ይህ ካፖርት አንድ ተራ ካፖርት ብቻ አይደለም። ካፖርቱ የማኅበራዊ ደረጃ፣ የክብር ተምሳሌት ነው። ጎጎልን የምናደንቀው እንደ ካፖርት ያለ መናኛ ነገር አንስቶ ስለ ሰው ልጅ ባህሪ ብዙ ቁምነገር ስለሚነግረን ነው።
ሌላው እጅግ ያስደነቀኝ አጭር ልብወለድ የሄርማን ሜልቪል Bartleby The Scrivener ነው። ይህ ልብወለድ ከጎጎል ካፖርቱ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለው።
ኦ ሄንሪ በማይጠበቅ በማይገመት አጨራረሱ የአንባቢዎችን ቀልብ የሚይዝ ሌላኛው የአጭር ልብወለድ ጠቢብ ነው። ይህ ደራሲ እውነተኛ ስሙ ዊሊያም ሲድኒ ፖርተር ሲባል ኦ ሄንሪ በሚል የብዕር ስም የሚፅፈው ማንነቱን ከአንባቢዎች ለመደበቅ ነበር።
ኦ ሄንሪ ልብወለዶቹን በሚፅፍበት ወቅት በወንጀል ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን አንባቢዎቹ ይሄንን እውነታ ከደረሱበት በወንጀለኛ የተፃፈ ነገር ለማንበብ ፍላጎት አይኖራቸውም ብሎ ስለሰጋ በብዕር ስም መፃፉን መርጧል።
ኤድጋር አለን ፖ በብዙ መልኩ ታላቅ ደራሲ ነው። የወንጀል ታሪኮች ፈርቀዳጅ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህ ብቻ ሳይሆን የአጭር ልብወለድ ላይ እጅጉን መጠበቡ ይነገርለታል። ግጥሞቹም ቢሆን የዋዛ አይደሉም። በተለይ The Raven የተሰኘው እጅግ ተወዳጅ ነው። ፖ በድርሰት ሥራ ብቻ ለመተዳደር የሞከረ የመጀመሪያው ደራሲ ሳይሆን እንደማይቀር ማንበቤን አስታውሳለሁ። ይሄ ደግሞ ከባድ ውሳኔ ነው። ስነጽሑፍ ያኔም ሆነ አሁን ወፍራም እንጀራ አያበላም። በዚህ የተነሳ የፖ አጭር ሕይወት በመከራ እና ሰቆቃ የተሞላ ነበር። ፖ በችጋር ኖሮ ገና በ41 ዓመቱ በችጋር ሞተ።
በሕይወት ዘመኑ ሃብትም ሆነ ዝና አልነበረውም። ፖ ከሞተ ከረዥም ግዜ በኋላ ፈረንሳዮች ተመሰጡበትና ወደ ቋንቋቸው ተረጎሙት። ፖ በፈረንሳይ ዝነኛ ሆነ። ይሄኔ አሜሪካውያን የፖን መጻሕፍት አቧራውን አራግፈው እንደ አዲስ ማንበብ ጀመሩ። እንዴት ያለ እሳት የላሰ ደራሲ እንደነበራቸው እና እንዳጡት ተረዱ። ፖ ከሞተ በኋላ መከበር ጀመረ። መስፍን አለማየሁ ወደ አማርኛ ከመለሳቸው የፖ አጫጭር ልብወለዶች መሀል The Cask of Amontillado አንዱ ነው። ፈልጋችሁ አንብቡት ትወዱታላችሁ። The Tell Tale Heart የፖ ማስተርፒስ ነው።
ሩስያ በረዥም ልብወለድ ደራሲዎች እጅግ የታደለች አገር ናት። ታዲያ እነዚህ ደራሲዎች አጫጭር ልብወለዶችም ፅፈዋል። ነገር ግን አጫጭር ልብወለዶችን ሙሉ ሥራ ብሎ የያዘ አንቴን ቼኾቭ ብቻ ነው። ቼኾቭ ከ400 በላይ አጫጭር ልብወለዶችን ፅፏል። ቼኾቭ በሙያው ሐኪም ነው። ስለራሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ ሕክምና ሚስቴ፣ ድርሰት ደግሞ ውሽማዬ ናት። አንዷ ስትሰለቸኝ ወደ ሌላዋ እየሄድኩ ኑሮዬን እገፋለሁ። ቼኾቭ በአጭር ልብወለድ ብቻ እንዳይምል፣ ጥቂት እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ተውኔቶችንም ፅፏል።
በግሌ ከአጫጭር ልብወለድ ደራሲዎች ሁሉ አብልጬ የምወደው ጊ ደ ሞፓሳን ነው። ከላይ ከተጠቀሰው የአንገት ጌጡ ሌላ ደወል፣ ትንሿ ደምበጃን ወዘተ ምርጥ የአጭር ልብወለድ ድርሰቶቹ ናቸው። ጊ ደ ሞፓሳ ከ300 ያላነሱ አጫጭር ልብወለዶችን ፅፏል። ሞፓሳ ከዚህም በላይ መፃፍ ይችል ነበር። ነገር ግን በአለሌነቱ የተነሳ ገና በ43 አመቱ በሸመተው የቂጥኝ በሽታ ይህንን ዓለም በግዜ ተሰናብቷል።
በነገራችን ላይ አዳም ረታ እጁን ያሟሸው በአጭር ልብወለድ ነበር። እንደዛሬው ዝነኛ ከመሆኑ በፊት ለመጀመሪያ ግዜ ስሙን የሰማሁት ስብሐት ማስታወሻ ላይ ሲያነሳው ነው። እንደ ስብሐት ከሆነ አዳም የአማርኛ አጭር ልብወለድ ቁንጮ ነው። ታዲያ ያኔ ይህንን ቁንጮ ማንም አያውቀውም ነበር። በብዙ ፍለጋ ማህሌትን አግኝቼ ለመደመም በቃሁ። 97 ላይ ግራጫ ቃጭሎች እንደታተመ ተሽቀዳድሜ አነበብኩት። የመጀመሪያው ረዥም ልብወለዱ ነበር። መጀመሪያ ወደ አእምሮዬ የመጣው ስብሐት አንብቦት ይሆን ወይ ነበር። ምን ተሰማው?! አሁን አዳም የአጭር ልብወለድ ብቻ ሳይሆን የረዥም ልብወለድ ጠቢብ ጭምር እንደሆነ የማያውቅ ስለ ስነፅሁፍ ምንም የማይረዳ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014