ዚያድ ባሬ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ከዝቀተኛ ማርሃን ጎሣ አባል ከሆነው ዳሮድ ጎሣ ቡድን በጣሊያን ሶማሌላንድ ውስጥ እኤአ በ1919 ተወለደ። በ1941 እንግሊዝ ግዛቱን እንደተቆጣጠረች የሶማሊያ ፖሊስ ኃይል አባል ሆኖ ተቀላቀለ፤ በዚያም እስከ ዋና ኢንስፔክተር ደረጃ ደርሶ ነበር። በ1950 ዓ.ም ደግሞ ጣሊያን ሄዶ ወታደራዊ አካዳሚ ተቀላቅሎ ተምሮ ነበር።
ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ኦጋዴን ግዛት መላ ጅቡቲንና ሰሜን ኬንያን ግዛት በወታደራዊ ኃይል አንበርክኮ ግዛቶቹን ነጥቆ ታላቋ ሶማሊያ ለመመሥረት አስቦ የተንቀሳቀሰ እና ኢትዮጵያ ላይ ውጊያ የከፈተ መሪ ነው። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ 24 ቀን 1987 ዓ.ም (ጃንዋሪ 2 1995) በናይጄሪያ በስደት ሆኖ ያረፈበት ቀን ነው። ዚያድ ባሬ ውጊያውን ሲከፍት ኢትዮጵያን ኬንያንና ጅቡቲን በወረራ በማካተት ታላቋን ሶማሊያ እመሠርታለሁ የሚል ምኞት ነበረው።
በዚህም ጅቡቲንና ኬንያን ለጊዜው ዘንግቶ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ኃይል አጥቅቶ ወረራውን ኢትዮጵያ ላይ አደረገ፤ ሆኖም የዚያድ ባሬ ሕልም እልም ብሎ ጠፋ፤ ፋታ ያጣው ፉከራና ድንፋታው በኢትዮጵያ ጦር አንገቱን ደፋ። ጅቡቲና ኬንያም በኢትዮጵያ ጦር ብርታትና ድል አድራጊነት ከጦርነት ቀጠናነት ነፃ ሊወጡ የቻሉ አገራት ናቸው።
በወቅቱ ዚያድ ባሬ ጦርነቱን ኢትዮጵያ ላይ የከፈተው የኢትዮጵያ ጦር በሰሜኑ ውጊያ ስለነበረበት በማደርገው ውጊያ ኢትዮጵያን አንበረክካታለሁ አሸንፋታለሁ ታላቋን ሶማሊያ እመሠርታለሁ በሚል ዕብሪት እና ትዕቢት ነው። ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦር ብትሸነፍ ኖሮ ኬንያና ጅቡቲ በታላቋ ሶማሊያ የመመሥረት የዚያድ ባሬ ዕብሪት ተጠቂዎች ተወራሪዎች ይሆኑ ነበር።
ዚያድ ባሬ የአገሪቱ መሪ ከሆነ በኋላ በ1963 አገሪቱ ሶሻሊስት እንድትሆን አወጀ። ታኅሣሥ 6 ቀን 1953ዓ.ም ከግብጽ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የደረሰችው ሶማሊያ ታኅሣሥ 19 ቀን በግብጽ ድጋፍ በዳኖት በኩል ውጊያ ከፍታ በ72 ሰዓት ውስጥ በኢትዮጵያ የተሸነፈች ሲሆን ግብጽም የሐፍረት ማቅ ለበሰች።
በ1960 በሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ሲመሠረትም ተዛውሮ በአባልነት ተቀላቀለ። በስድስት ዓመቱ የሜጀር ጄኔራል ማዕረግ አግኝቶ እና ዋና ኣዛዥ ሆነ። በጦሩ የያዘውን ሥልጣን ተጠቅሞ 1969 ራሱን የአገሪቱ ከፍተኛ አብዮታዊ ጉባኤ መሪ የአውቶክራቲክ አመራር በመያዝ የራሱን ስብዕና በመጫን የሳይንቲፊክ ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም አመራርን በአገሪቱ ላይ በከባድ ማስፈጸሚያ እንዲተገበር አደረገ። በዚህም በወቅቱ ከሶቪየት ኅብረት ጋር የነበረውን ትብብር በማጠናከር ሠርቷል።
በወቅቱ ቀስ በቀስ በመፈንቅለ መንግሥት የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አብዲራሺድ አሊን በማስገደል በትረ ሥልጣን የጨበጠው ዚያድ ባሬ፤ የሶማሊያ ግዛቶች ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ ጠቅላይ የአገሪቱ ማለትም የሶማሊያ ዴሞክራክ ሪፐብሊክ ሦስተኛ ፕሬዚዳንት ሆኖ እንደ ምዕራባውያን አቆጣጠር ከ1969 እስከ 1991 መሥርቶ ነበር። በአገሪቱ በይፋ የጎሳ ታማኝነት በማገድ ውስጥ ውስጡን ግን ለራሱ ዓላማ ማዳበሪያ የጎሣ አለቆችና ሽማግሌዎችን በገጠራማ አካባቢዎች ሥርዓት ለማስያዝ ተጠቅሞባቸዋል።
በዚህም የከፍተኛ አብዮታዊ ጉባዔ ወታደራዊ ጁንታ በሥሩ አድርጎ ዚያድ ባሬ ሶማሊያን የአንድ ማርክሲስት ሌኒኒስት ኮሚዩኒስት ፓርቲ ግዛት ያደረጋት ሲሆን አገሪቱን የሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በማለት ሰይሞ ከሶቪየት ኅብረት ርዕዮተ ዓለሙን ወስዶ በመተግበር ድጋፍ ያገኝ ነበር።
የዚያድ ባሬ አገር ሶማሊያ፤ በወቅቱ ከኮሙኒስቷ ሶቭየት ህብረት እስከ አፍንጫዋ ድረስ በዘመኑ የጦር መሣሪያ ያስታጠቀቻት ጡንቻዋ የፈረጠመች በዕብሪት የተወጠረች አገር ነበረች። የመሪዎቿም ዓላማ በዙሪያዋ ያሉትን ጨፍልቃ ታላቂቱን ሶማሊያ መፍጠር ብቻ ነበር። ለዚህም ነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ዚያድ ባሬ መሪነትና አዋጊነት ኢትዮጵያን በኃይል ለመውረር የተነሳችው።
ይህም የንጉሡ አገዛዝ ወድቆ የደርግ ጊዚያዊ መንግሥት ምሥረታ ላይ ለነበረችውና በሰሜን ካሉ ወያኔዎች ጋር ሠራዊቱ ውጊያ ላይ ለነበረባት ኢትዮጵያ ወቅቱ ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር። በወቅቱ አገሪቱ ሕዝቡ የአገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ከወራሪዋ ሶማሊያ እንዲከላከል ላደረገችው የእናት አገር ጥሪ ምላሹ፤ ፈጣንና በአገር ፍቅር ወኔ የተሞላ ምላሽ በመስጠት ለሶማሊያ ወረራ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጀ።
መጀመሪያ ሶማሊያን በመሣሪያ ያስታጠቀችው የሶሻሊስት ሶቪየት ህብረት ነበረች፤ ሶማሊያ ለረጅም ዘመን ወታደራዊ ኃይሏን ስታፈረጥም ነበር የቆየችው፤ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የኃይል አለመመጣጠን መኖሩንና የኢትዮጵያ ጦር ከወያኔዎች ጋር በሰሜን በነበረበት ውጊያ በምሥራቁ እና ደቡብ የአገሪቱ አካባቢ የነበረው የጦር ኃይል ክፍተት ተጠቅሞ 1967 ዓ.ም ገና በለውጥ አብዮት ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጵያ ወረረ።
ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የዚያድ ባሬ ታላቋን ሶማሊያ የመፍጠር ሕልም እልም ብሎ ጠፍቶ እርሱ ከአገሩ ሲሰደድ በጎሳ የተከፋፈሉ ታናናሽ ሶማሌዎች እንዲፈጠሩ ጥቁር ጠባሳውን ጥሎባቸው አለፈ። ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን የወረረችው።
ዘግይቶም ከሶቪየት ኅብረት ጋር የነበረውን ትብብር አቁሞ ፊቱን ወደ አሜሪካ አዞረ። ይህም እርዳታ በመሻትና በተደጋጋሚ ይቀርብበት የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ በዓለም አቀፍ ሁኔታ ስላስጨነቀው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ማድረጉ እና ዚያድ ባሬም ፊቱን ወደ ካፒታሊዝም ማዛወሩ በምዕራባውያን ዘንድ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቀመበት። ይህ ሁሉ ሳይሳካለት ቀርቶ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች የዚያድ ባሬ ሕልም ከሸፈ፤ ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቷን አስጠበቀች።
ኃይለማርያም ወንድሙ አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014