የሥዕል ጥበብ የሠዓሊው የምናብ ውጤት ነው። ሁሉም ሰው ሥዕልን የሚተረጉመው ሥዕሉን በተረዳበት መንገድ ነው። በሌላ በኩል ሰዎች ስለፎቶ የሚኖራቸው ስሜትና አረዳድ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው።
ያም ሆኖ ግን በፎቶ ውስጥም መጠነኛ የሆነ የዕይታ ልዩነት ይኖራል። አንድነታቸው ደግሞ፤ ሁለቱም ጥበባት ሁነትና ክስተት ገላጭ መሆናቸው ነው። ዘመንን እና ማህበራዊ መስተጋብርን ይገልፃሉ።
ስለሥዕል ከዚህ ቀደም ብዙ ስለፃፍን ዛሬ የምናወራው ስለፎቶ ጥበብ ብቻ ነው። ‹‹አርት ዴይሊ›› የተሰኘ የፎቶ ጥበብ ድረ ገጽ፤ ፎቶ ጥበብ መሆኑን በአምስት ምክንያቶች ያብራራዋል። ድረ ገጹ እንደሚያብራራው፤ አንድ ፎቶ ማራኪ እና የብዙዎችን ቀልብ ሳቢ የሚሆነው በፎቶ አንሽው የአነሳስ እና የአተያይ ጥበብ ነው። የብርሃን አመራረጥ እና የአንግል አያያዝ ጥበብ ነው። ፎቶ ጥበብ መሆኑን ለመግለጽም አንድ የንጽጽር ምሳሌ ይጠቀማል።
በተመሳሳይ ካሜራ፣ በተመሳሳይ ብርሃን፣ በተመሳሳይ ቦታ አንድን ነገር በተለያዩ ሰዎች ፎቶ ብናስነሳ የተለያየ ይሆናል። ይህም የፎቶ ጥበብ ተሰጥኦ መሆኑን ያሳያል ይላል። ‹‹ፎቶግራፍ አካላዊ ገጽታዎችን ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ስሜት ማሳየት ነው›› ይላል ድረ ገጹ። ይህም የፎቶግራፍ አንሽውን ጥበብ ያሳያል።
ከትልልቅ ሁነቶች ውስጥ ልብ የማይባሉና ትንንሽ የሚመስሉ ክስተቶች ጎልተው እንዲወጡና እንዲታዩ ያደርጋል። በቦታው የነበረ ሰው ያላየውን ሁሉ እንዲያየው ያደርጋል።
አንድ ሰው ላይ በብዙዎች ልብ ያልተባለን ቅጽበታዊ ውስጣዊ ስሜት አውጥቶ እንዲታይ ያደርጋል። ይህም ፎቶግራፍ ጥበብ መሆኑን ያሳያል። ምሳሌ ሲያስቀምጥም ‹‹አንዲት የውሃ ጠብታ በፎቶግራፍ ጎልታ እንዲትታይ ያደርጋል›› ይላል።
በሥዕል ውስጥ ረቂቅነት እንደሚታይ ሁሉ፤ ፎቶግራፈር ደግሞ የሚመቸውን ብርሃንና የሚያስፈልገውን ሌንስ በማስተካከል ለማንም ልብ የማይባል ረቂቅ ነገርን አውጥቶ ያሳያል። ይህ የካሜራ ባለሙያው ጥበብ ነው። የአንድን ሰው ፈገግታ ወይም ውስጣዊ መረበሽ ልብ ሳንለው ሰውየው ሊቀይረው ይችላል፤ በካሜራ ባለሙያው ግን ያቺ ቅጽበት ትያዝና ጎልታ እንዲትታይ ትደረጋለች።
ስለፎቶ ጥበብ ያነሳነው ባለፈው ሰኞ ታኅሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተከፈተውን የፎቶ ዓውደ ርዕይ ምክንያት በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 80ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ከእነዚህም አንዱ ባለፈው ሰኞ የተከፈተው የፎቶ ዓውደ ርዕይ ነው። በፎቶ ዓውደ ርዕዩ አሸባሪው ሕወሓት በጥቅምት 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን የክህደት ድርጊት ከፈጸመበት ድርጊት ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዘመቻ እና በቅርቡ የተፈናቀሉና የተደፈሩ አሰቃቂ ግፎች ሁሉ በፎቶ ቁልጭ ብለው ይታያሉ። ፎቶዎቹን ማየት፤ ጥበብን ማየት ነው፣ ሳይንስን ማየት ነው፣ ማህበረሰባዊ ፍልስፍናን ማየት ነው። በፎቶ ጥበብ ላይ ያየናቸው ማብራሪያዎች ሁሉ በተግባር ይታያሉ። በሰዎች ውስጥ ያለ ስሜት ጎልቶ ይታያል። እያንዳንዷ ቅጽበት ሰፋፊ ትርጉም አላት። ፎቶዎችን ማየት ውስጥን ለብዙ ነገር ያነሳሳል፤ በተለይም የጥበብ ተሰጥኦ ላላቸው ሰዎች ሌላ ተጨማሪ ጥበብ እንዲፈጠር ያደርጋል። በተለያዩ ግንባሮች በመገኘት ፎቶዎችን ያነሳው እና ድንገተኛ ቅጽበቶችን በማንሳት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፎቶግራፈር ዳኜ አበራ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸው፤ ፎቶግራፍ ማለት ለባለቤቱ እንኳን ልብ የማትባል ቅጽታዊ ስሜትን ማስቀረት ነው። ድርጊቱ በሚከሰትበት ቅጽበት በቦታው ካለ ሰው በላይ ወይም ነገርየውን በቪዲዮ ከማየት በላይ በፎቶ የበለጠ ጎልቶ ይታያል። በቪዲዮ ሲሆን ‹‹ጎርፍ እንደማየት ነው›› የሚለው ባለሙያው፤ በፎቶ ሲሆን ግን እያንዳንዷ ቅንጣት ጎልታ ትታያለች ይላል።
እንደ ካሜራ ባለሙያው ዳኜ ገለጻ፤ ፎቶ ማንሳት ጥበብ ነው፤ልክ እንደ ጥይት አተኳኮስ ነው። ምላጭ እንደ መሳብ ነው። ፎቶ አንሽው ጣቱን የካሜራው ምላጭ ላይ በተጠንቀቅ ያስቀምጣል፤ ቅጽበቷን በተጠንቀቅ ሲጠባበቅ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ነው። ልክ በዚያች ቅጽበት ክስተቷን ማስቀረት አለበት። አውቶማቲክ በሚወርድ የጥይት እሩምታ ውስጥ ብልጭታዎችን ያነሳል። ጥይት ሲነድ የሚወጣውን ብልጭታና ጨረር ሁሉ ሳይቀር ያነሳል። ተኳሹ ምላጭ ሲስብ፣ መሳሪያው እያስፈነጠረ ሲያቀባብል… እነዚህ ሁሉ ቅጽበቶች ይነሳሉ። እንግዲህ እጅግ በጣም ፈጣን የሆነውን የጥይትን ቅጽበት በፎቶ መያዝ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን እውነትም ጥበብ ነው።
የፎቶ ባለሙያው ዳኜ እንደሚለው፤ በተለይም በጦር ሜዳ የሚነሱ ፎቶዎች ብዙ ነገር ናቸው። ታሪክን ሰንደው ከማስቀመጣቸው በተጨማሪ ለጥበብ እና ለማህበራዊ ፍልስፍና የሚያነሳሱ ናቸው። ባለሙያው ግንባር በነበረበት ወቅት አንድ ክስተት ተመለከተ። ይሄውም በማህበረሰባችን ውስጥ ብዙም ያልተለመደና ያልታየ ነው። አንዱ ወታደር የሴቷን ወታደር ፀጉር ለመሥራት እየፈታ ነው።
በዘመናዊው ፀጉር ቤት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ገጠር ውስጥ ወንድ የሴትን ፀጉር ሲፈታና ሲሰራ ማየት አልተለመደም። ዳኜ ይህን ሲያደርጉ አየ፤ በካሜራውም አስቀረው። ይህ ፎቶ፤ በፎቶ ዓውደ ርዕዩ ላይ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ሲታይ ነበር። ይህ ፎቶ የማህበራዊ ፍልስፍና አብዮት ፈጠረ ማለት ነው። ፎቶዎች በተለይም ለጥበብ ሰዎች የሃሳብ ግብዓት እንደሚሆኑም ዳኜ ይናገራል።
እነዚያን ፎቶዎች ያየ ሰው ግጥም ይጽፋል፣ ዘፈን ያንጎራጉራል፣ ሥዕል ይስላል። እነዚህ የጥበብ አይነቶች የሚገኙት የሆነ ነገር በማየት ነው። አነሳሽ ክስተት ይፈልጋሉ። ኪነ ጥበብ ዝም ብሎ አልጋ ላይ ተኝቶ አይመጣም። የሆነ ነገር በማየት ነው።
የደፈረሰ የወንዝ ወይም የኩሬ ውሃ የሚጠጣ ወታደር ማየት የተለመዱ ነገሮችን እንደማየት አይደለም፤ እንኳን የኪነ ጥበብ ተሰጥኦ ያለውን ሰው የሌላውንም ውስጥ ይበረብራል። እሳት ለማንደድ አቧራ ላይ ያጎነበሰ፣ ፀጉሯ አፈር የለበሰ ወታደር ማየት፤ ከተማ ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን እንደማየት አይደለም። ወይም መዝናኛ ቤት ውስጥ የሞዴል ፎቶ እንደማየት አይደለም። በእነዚህ አስገራሚና አሳዛኝ ፎቶዎች ምክንያትና አነሳሽነት ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችም ይሰራሉ ማለት ነው።
ዳኜ በረጅም ዓመታት የሥራ ልምዱ አንድ ነገር በትልቁ ታዝቧል። ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ ብዙ እውቀትና ልምድ አላቸው የሚባሉ ታዋቂ ሰዎች ሁሉ ሳይቀር የቪዲዮ ሱስ ያለባቸው ናቸው።
ፎቶን ያህል ጥበብና ታሪክ ሰናጅ ትኩረት አይሰጡትም። ቃለ መጠይቅ ለመስጠት እንኳን ከህትመት መገናኛ ብዙኃን ይልቅ ቴሌቪዥንን ይመርጣሉ። አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በከፍተኛ ጥራትና ብቃት እነዚህን ሥራዎች ለዕይታ ቢያቀርብም ዘርፉ ግን ትኩረት የተነፈገው መሆኑን ታዝቧል።
ይህ አመለካከት እንደቀየረም ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል። የኪነ ጥበብ ባለሙያው አቶ ነብዩ ባየ በዓውደ ርዕዩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኪነ ጥበብ የአገር ፍቅር ስሜትን ቀስቃሽ ነው። ኢትዮጵያውያን ወኔ አላቸው።
ያንን የሚቀሰቅሰው ኪነ ጥበብ ነው። ያ ኪነ ጥበብ ከሚቀመጥባቸውና ከሚወራረስባቸው መንገዶች መካከል ፎቶ አንዱ ነው። በሌላ በኩል ኪነ ጥበብ መዝናኛ ብቻ እንዳልሆነም ባለሙያው ተናግረዋል። ፎቶዎችን የሚያዩ ሰዎች እየተዝናኑ ሳይሆን እየተመሰጡ እና ሃሳብ እያመነጩ፣ በውስጣቸው እያንሸራሸሩ ነው፤ በሚያዝናኑትም ሊዝናኑ ይችላሉ።
የፎቶግራፍ ጥበብ ቅጽበትን በአራት መቃን (ፍሬም) ውስጥ አድርጎ ማየት ነው። በቅጽበት የተፈጠረችን ክስተት ተመልካቹ ተረጋግቶ ረጅም ደቂቃ ወስዶ ተመስጦ እንዲያየው ማድረግ ነው። አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲህ አይነት ሥራዎችን በመሥራት የተዋጣለት መሆኑንና ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ባለሙያው አሳስበዋል።
አራት ኪሎ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፊት ለፊት በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አንደኛ ወለል ላይ የተከፈተው የፎቶ ዓውደ ርዕይ እስከ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
ከሁነቶች ሁሉ አስገራሚ፣ አሳዛኝና ያልተለመዱ ክስተቶች የሚታዩበት የጦር ሜዳ ክስተት ነውና ይህን የፎቶ ዓውደ ርዕይ እንድትጎበኙም እናሳስባለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014