ነቀምቴ፡ – በምዕራብ ኦሮሚያ ከአንድ ሺህ 800 በላይ የጠላት ኃይል ላይ እርምጃ መወሰዱን የምዕራብ ዕዝ ኦሮሚያ ልዩ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ከማል ገለፁ።
ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ላይ በተለያየ ጊዜ በታቀደ መልኩ በተካሄደ ዘመቻ በአንድ ሺ 836 በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሺ 643 የጠላት ታጣቂዎች መገደላቸው፣ 106 የሚሆኑት ደግሞ እጅ የሰጡ መሆናቸውና 87 የሚደርሱ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ደግሞ መያዛቸውን ተናግረዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ አሸባሪው የኦነግ ሸኔ፣ በቤኒሻንጉል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ቤኒን የተባለ አማፂ ኃይልና አማራን የማይወክሉ ከአማራ የወጡ ፅንፈኛ ኃይሎች በአካባቢው በስፋት በመንቀሳቀስ ኅብረተሰቡ ላይ በተለያየ መንገድ ችግር እያደረሱ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በምስራቅ ወለጋ ዞን በጥምረት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አረጋግጠናል ብለዋል፡
ምስራቅ፣ ምዕራብና ቄለም ወለጋ አብዛኛውን አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ኃይል የጸጥታ ጥበቃ የሚያካሄድባቸው መሆናቸውን ጠቁመው፤ በምስራቅ ወለጋ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ከተሰጠው በኋላም በጥምረት የተለያዩ አሰሳዎችና እርምጃዎች በመወሰዳቸው በሽብር ቡድኑ ላይ ኪሳራ እየደረሰበት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በዕቅድ ተመስርቶ በተካሄደ ዘመቻም አንድ የብሬን መሳሪያ ከአራት ሺ 278 ጥይቶቹ ፣ 105 የክላሽ መሳሪያዎች ከ47ሺህ 900 ጥይቶች፣ 70 ሽጉጦች ከ324 ጥይቶች ጋር እንዲሁም 11 የሚሆኑ የተለያዩ የወገብ ትጥቆችም ከሽብር ቡድኑ መማረኩን ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡
ወንጀሎች ከመፈጸማቸው አስቀድሞ መሠራት የሚገባቸውን ሥራዎች በመሥራታችን የጠላት ኃይል ሊያደርስ የነበረውን ከፍተኛ ውድመት ለማስቀረት ችለናል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ፣ የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት ጠላት ላይ በተወሰደው እርምጃ ሕዝቡ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡
በአሁን ጊዜ የጠላት ኃይል በተለይም በምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች በኦሮሞና በአማራ መካከል የብሔር ግጭት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሥራ እየሠራና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ፅንፈኛ ኃይሎች የብሔር ግጭት በማስመሰል ማኅበረሰቡን እየዘረፉና የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን እያወደሙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ረዳት ኮሚሽነሩ ገለፃ ከላይ እስከ ታች ካሉት የፀጥታ አካላትና የመንግሥት አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት በመሠራቱ በርካታ ድሎችና ለውጦች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡
መከላከያ ሠራዊት ወደ ሰሜኑ የግዳጅ ቀጠና በሚንቀሳቀስበት ወቅትም የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ኃላፊነት በመውሰድ ከሁለት ዓመታት በላይ በእነዚህ የሽብር ቡድኖች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃና በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ይሄ ሽብርተኛ ኃይል ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ስለሚገኝ ማኅበረሰቡ የራሱን ሰላም በራሱ አቅም መጠበቅና መረጃዎችንም ለሚመለከተው የፀጥታ አካላት በመስጠት ትብብር ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ ኅብረተሰቡን እየገደለ፣ ንብረቱን እያወደመና እየዘረፈ፣ በርካታ ነውረኛ ተግባራትን እየፈፀመ መሆኑን ማኅበረሰቡ በመገንዘብ ከፀጥታው ጎን በመቆም መተባበር እንደሚጠበቅበትና በግንዛቤ ችግር ወደ ሽብር ቡድኑ የገቡ ልጆችም ካሉት እንዲመክርም ረዳት ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም