የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከወር በፊት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ኖቬምበር 21፣2021 ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ላይ አሜሪካ በአፍሪካ ስላላት ፖሊሲ የሚከተለውን ብሎ ነበር::”አፍሪካን በተመለከተ የምንከተለው ፖሊሲ አፍሪካን ብቻ የተመለከተ ነው::ስለ ቻይና አይደለም” ይህ የብሊንከን ንግግር ብዙ እንድምታ አለው::
አሜሪካኖች በአፍሪካ ያላቸው ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛው የአፍሪካውያንን ጥቅም ሳይሆን የቻይናን እንቅስቃሴ መግታት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው በሚል ይታማሉ::በእርግጥም ነገሩ እንደዚያ ይመስላል::አሜሪካውያን በአፍሪካ ያላቸው ቦታ ቀን በቀን እየሟሸሸ ይገኛል:: በአንፃሩ ቻይና፣ ሩሲያ ፣ ቱርክ እና ኢራን ያላቸው ቦታ ከፍ እያለ ነው::
ይህ ለአሜሪካውያኑ ያላስተዋሉት ዱብ እዳ ሆኖባቸዋል:: ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሜሪካ መሪዎች አፍሪካ በዚህ መልኩ ከእጃችን ታመልጣለች የሚል ግምት አልነበራቸውም:: ጆርጅ ቡሽ የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት መካከለኛው ምስራቅ እና ሽብር ነበር::
በዘመነ ኦባማ አሜሪካ ትኩረቷን ወደ ደቡብ እስያ በማዞር ቻይና በደቡብ እስያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ መግታት ላይ አተኮሩ:: በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመን አሜሪካ ሙሉ ትኩረቷን በሷና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን በማስተካከል ላይ አተኮረች:: በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ቻይና ትኩረቷን አፍሪካ ላይ አድርጋ ስትሰራ ነበር::
ለዚህም ብዙ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል:: አሚር ሞህሰኒ የሚባሉ ምሁር በታዋቂው አትላንቲክ ካውንስል ገጸ ድር ላይ China and Sub-Saharan Africa trade: A case of growing interdependence በጁላይ 22 ቀን 2021 በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ቻይና ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ከፈንጆቹ 2001 እስከ 2020 ባሉት 20 አመታት ውስጥ በ1864 ፐርሰንት ሲያድግ በተቃራኒው የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት ጋር ያለ የንግድ ግንኙነት ግን እያሽቆለቆለ ነው ብለዋል::
ቻይና ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ድርሻ በፈረንጆቹ 2001፤ 4 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን በ2020 ይህ ቁጥር 25 በመቶን አልፏል::
በተቃራኒው አሜሪካ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ከ15.5 በመቶ ወደ 5.6 በመቶ ሲወርድ የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ከ30.3 በመቶ ወደ 22.3 በመቶ አሽቆልቁሏል::
ይህ ሁሉ ሲከሰት ግን አሜሪካውያን ትኩረታቸው አፍሪካ ላይ አልነበረም:: በመጨረሻ ግን ነቁ:: ቻይና በብዙ ርቀት አልፋቸው እንደሄደች እና አፍሪካውያን የቻይና ወዳጅነት እንደተመቻቸው አስተዋሉ:: ስለዚህም ጆ ባይደን ወደ ስልጣን እንደመጡ ቅደሚያ ትኩረት ሰጥተው ከተንደፋደፉባቸው ጉዳዮች አንዱ ይሄ ነው:: የቻይና እና የአፍሪካውያኑ ወዳጅነት ግን ከኢኮኖሚ ጉዳዮችም ያለፈ ነው::
የቻይና የመንግሥት አስተዳደር መንገድ ላይም ሰፊ ልዩነት ከምእራባውያን ጋር እየታየ ነው:: ሄውንግ ትራን የሚባሉ ምሁር በአፕሪል 2021 በዚሁ አትላንቲክ ካውንስል ገጽ ላይ Is the US-China strategic competition a cold war? በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሁፍ የቻይና እና አሜሪካውያን ልዩነት ከሚመሰረትባቸው ሶስት ምሰሶዎች መሀከል አንዱ ርእዮተ አለማዊ እንደሆነ ያስገነዝባሉ::
የቻይና መንግስታዊ ሞዴል ባለፉት 40 አመታት በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ልማት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሆኖ የሚመራው ካፒታሊዝም እና ያስመዘገበው ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚው እድገት በተለይ ለታዳጊ አገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል:: በዚህም የተነሳ ብዙዎች ይህን የአስተዳደር መንገድ ለመከተል ፍላጎት አሳይተዋል::
ብዙዎች የቻይናን መንገድ ሲከተሉ በተቃራኒው የምእራቡ የአገዛዝ ስርአት ማሽቆልቆል ይዟል:: ምእራባውያኑም ይህን የነሱ መንገድ ተፈላጊነት ማጣት ለመግለጽ ሲፈልጉ “በአለም ዙሪያ ዲሞክራሲ እያሽቆለቆለ ነው” ሲሉ ይሰማል:: እነሱ ዴሞክራሲ አሽቆለቆለ ከሚሉባቸው የአለም ቀጣናዎች መሀከል ደግሞ አንዱና ዋነኛው ከሰሀራ በታች ያለው የአፍሪካ ክፍል ነው::
ሀቁ ግን ዴሞክራሲ እያሽቆለቆለ ሳይሆን አፍሪካውያን የምእራቡን የዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ጽንሰ ሀሳብ እንዳልተቀበሉት እና ለእድገት የማይጠቅም እንደሆነ እንዳስተዋሉ ነው:: አሜሪካውያኑ ይሄም የገባቸው ሰንብቶ ነው::
ሰንብቶ ሲገባቸው በአዲስ መልክ ዴሞክራሲን እናስተምር እናስፍን ብለው ተነሱ:: አላማቸው በአፍሪካ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ሳይሆን የቻይናን መስፋፋት መግታት ነው:: እነ አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ በአፍሪካ ያላት ፖሊሲ ቻይናን ታሳቢ ያደረገ አይደለም ቢሉም ሀቁ ግን ትግላቸው በሙሉ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በመዘናጋት ያጧትን አህጉር መልሶ መቆጣጠር ነው::
አሜሪካኖቹ አሁን ደንግጠው ነው የሚንደፋደፉት:: ባለፉት 20 አመታት የሰሩትን ስህተት ለማስተካከል እና ቻይናን ሩሲያን እና ሌሎች ከነሱ በተቃራኒ የቆሙ አገራትን ከአፍሪካ አህጉር አስወግደው እንደ ቀድሞው ብቸኛ ጌታ መሆን ይመኛሉ::
ይህ የአሜሪካኖቹ መደናገጥ የገባቸው ጩልሌዎች ደግሞ ይህን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይሞክራሉ::ከነዚህ መሀከል አንዱ ደግሞ የጁንታው የጦር መሪ ጻድቃን ገ/ትንሳይ ነው::ሰውየው ሰሞኑን የግሌ አቋም ነው ብሎ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቻይና ኢራን እና ቱርክ ለፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍ እንዳደረጉ እና አሜሪካ ግን ለሕወሓት ምንም እንዳላደረገች በመግለጽ ይወቅሳል:: መልእክቱን ማስተላለፍ የፈለገው በቻይና እንቅስቃሴ ለደነገጡት የዋሽንግተን ሰዎች ነው::
አላማውም እየመጣበት ካለው አይቀሬ ሽንፈት እንዲታደጉት ሲሆን ለዚህም ውለታቸው በቀጣይ ታዛዣ ሆኖ አሜሪካውያኑ የሚመኙትን የቀድሞ ጌትነታቸውን መመለስ ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራሉ መንግሥት እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት ከቻይና የልማት አጋርነት ብዙ መጠቀም ይፈልጋል::
ምእራባውያኑ ከሚለግሱት እርዳታ ይልቅ ቻይና የምታመጣው ኢንቨስትመንትን ይመርጣል::እንደ ማንኛውም ጤናማ መንግሥት በውስጥ ጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብነትን ስለማይፈልግ ከቻይና ጋር ያለውን ወዳጅነት ማስቀጠል ይፈልጋል:: ነገር ግን ይህ ማለት ከምእራባውያኑ በተለይም ከአሜሪካ እና አውሮፓ ጋር ያለውን ወዳጅነት አይፈልገውም ማለት አይደለም::
በተቃራኒው ያ ወዳጅነት በተለይ ከኢኮኖሚ አንጻር በጣሙን አስፈላጊ ነው:: ችግሩ አሜሪካውያኑ አሁን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ቻይናን በመፋታት እና ለአሜሪካ ፍጹም ተገዢነትን በማወጅ እንዲጀመር መፈለጋቸው ነው::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ አፍሪካን ሲጎበኙ አፍሪካውያን አማራጭ እናቀርብላቸዋለን፤ ነገር ግን ከኛ ወይም ከቻይና አንዳችንን ምረጡ አንላችውም ቢሉም በተግባር ግን እንደሚታየው አሜሪካውያኑ አፍሪካውያን ከቻይና ጋር እንዲቆራረጡ ይፈልጋሉ:: ወደ ሩሲያም እንዲያማትሩ አይፈልጉም::ቱርክን እንዲያናግሩ አያበረታታቱም::ከኢራን ጋር የተወዳጀ ጠላታቸው እንደሆነ ያምናሉ:: በዚህም የተነሳ አሜሪካ እና አፍሪካውያን መግባባት አቅቷቸዋል::
ለመግባባት አሜሪካውያኑ ከቻይና ፎቢያ ለመላቀቅ መቁረጥ አለባቸው:: አሁን አሜሪካውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው የሚነኩሩትም የሰብአዊ መብት ጉዳይ አሳስቧቸው ወይም የኢትዮጵያ ሰላም እንቅልፍ ነስቷቸው ሳይሆን አዲስ አበባ ያለው መንግሥት በስሌት የሚንቀሳቀስ እና ለተንበርካኪነት ያልተዘጋጀ በመሆኑ በተቃራኒው ትግራይ ውስጥ የመሸገው ሀይል ለተንበርካኪነት የቆረጠ በመሆኑ ነው::ለአሜሪካውያኑ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከአለም አቀፍ እና አፍሪካ ተኮር ስትራቴጂያቸው ጋር የተሳሰረ ብቻ ነው::
የኢትዮጵያን ጉዳይም እያዩ ያሉት ከቻይና እና ሩሲያ አንጻር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር በተዛመደ አይደለም:: አሜሪካውያን በእውነት ስለ ኢትዮጵያ ሰላም የሚጨነቁ ከሆነ ቻይናን እና ሩሲያን ከስሌታቸው አውጥተው 150 አመት ወዳጅነት እንዳላቸው ሁለት አገራት ሊያስቡ ይገባል::
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014