ባለፈው ሳምንት በተካሄደው አምስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ 290 የሚሆኑ ዳኞች ለመጀመሪያ ደረጃ ወይም ለወረዳ ፍርድ ቤት ሹመታቸው ጸድቋል። እነዚህ ተሿሚዎች አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከልም 19ኙ ሴቶች ናቸው፡፡ ወጣት ዳኞቹ በክልሉ ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች ተመድበው ሊያገለግሉ በምክር ቤቱ ቃል ገብተዋል፡፡
በእርግጥ ይህ እድሜ ለወጣቶቹ ፈተና ነው። አንደኛው ፈተና እንደወጣት በማህበረሰቡ ዘንድ ‹‹ፍትህ እና ጥቅም ክፉኛ ተቆራኝተዋል›› እየተባለ ወጣቶቹ ‹‹በጥቅም ተደልለው ፍትህ ያዛባሉ›› ሲሉ እምነት እያሳጡዋቸው ሲሆን ሁለተኛው ፈተና ደግሞ ‹‹በአሁኑ ወቅት ፍትህ የለም፤ ፍትህ በራሱ በወቅቱ ሥርዓት ተዛብቷል›› ሲሉ በሌላ ወገን ዘርፉ እንደ ዘርፍ ችግር ውስጥ ነው ሲሉ የሚሞግቱ አልጠፉም፡፡
ይሁን እንጂ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይቀርም›› እንዲሉ ወጣቶቹ ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ፈተና በእውቀት፣ በእውነትና በሙያዊ ስነምግባር ታንፀው ፍትህ ሊያሰፍኑ ቃለመሀላ ፈፅመዋል፡፡ እኛም የእነዚህን ወጣቶች አስተያየት እንዲህ አስነበብን፡፡ ‹‹እውነት መናገር፣ ስለ እውነት መመስከር፣ እውነት የሆነ ነገር ሁሉ ያስደስታል፡፡ ሀሰት የሚናገር፣ በጥቅም የሚደለል ሰው አትወድም፡፡ ፍትህን በጉቦ የሚያጣምመውን ደግሞ አምርራ ትጠላለች። እውነትን የተላበሰው ባህሪዋ ለውጤት እንጂ ለችግር ሲዳርጋት አላጋጠማትም፡፡ ‹እውነት አብሮኝ አድጓል› ›› የምትለው ወጣት በእውነት ስለእውነት ለመስራትም የህግ ባለሙያ የመሆን የልጅነት ፍላጎትዋን አሳክታለች።
ወጣትዋ በ2009 ዓ.ም በህግ በመጀመሪያ ዲግሪ ከአዳማ ዩኒቨርስቲ 3 ነጥብ 47 በማምጣት በማዕረግ ነበር የተመረቀችው፡፡ የትምህርት ውጤትዋ አብረዋት ይማሩ ከነበሩ ሴቶች የላቀ መሆኑ ደግሞ ልዩ አድርጓታል፡፡ ወጣትዋ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በሚዳቀኝ ወረዳ አጋዥ ዳኛ ሆና በማገልገል የአንድ ዓመት ተኩል የሥራ ልምድ አግኝታለች፡፡ ባለፈው ሳምንትም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆና ተሹማለች፡፡
ሹመቱ የተሰጣት በአምስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ ወጣት ደራርቱ ጀቤሳ ስለሙያዋ አንደበቷ ብቻ ሳይሆን ለሙያው ያላት ፍላጎት በገጽታዋ ላይም ይነበባል፡፡በአንድ ዓመት ተኩል የህግ ሥራ ቆይታዋ የሰራችውንም፣ የታዘበችውንም፣ ወደፊት መድረስ ስለምትፈልግበት ደረጃ እንዲህ ነበር ያጫወተችኝ። አጋዥ ዳኛ ሆና በሳራችባቸው ጊዜያቶች ጥሩም መጥፎም ነገሮችን ታዝባለች፡፡
እርሷ እንዳለችው አጋዥ ዳኛ የሰራው ሥራ በነባር ዳኛ ስም እንደተሰራ ተደርጎ ነው ውሳኔው የሚተላለፈው። ያሳለፈችውን ውሳኔ በስሙ የሚያጸድቅ ሰው ፍለጋ ለእርሷ አድካሚ ነበር። ነባር ዳኞች ከማገዝ ይልቅ እንደ ጀማሪ ማየት፣ እምነት አለማሳደር፣ ነገ ተተኪዎች እንደሆኑ አድርጎ አለማሰብ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ኃላፊነት ላለመስጠት ሲባል የተዘረጋው አሰራር ብዙም የሚያበረታታ ሆኖ አላገኘችውም፡፡
እርሷ ግን የወደፊቷን መልካም ነገር በማሰብ ለገጠማት ነገር ትኩረት ሳትሰጥ ለሹመት መብቃቷን ትናገራለች፡፡ ወጣት ደራርቱ በአንድ ዓመት ተኩል የሥራ ቆይታዋ በሥራዋ ያጋጠማትንም እንዲህ ገልጻለች። እርሷ እንዳለችው ትሰራበት በነበረው ወረዳ ውስጥ ለፍርድ ቤቱ ይቀርቡ ከነበሩት ጉዳዮች አብዛኞቹ በሀገር ሽማግሌና በባለጉዳዮቹ ሊፈቷቸው የሚችሏቸው ናቸው፡፡ ፍች፣የቀለብ ጥያቄ በአጠቃላይ ከባልና ሚስት ጋር እና መሬት ሽያጭ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም እንዲሁ ይበዛሉ፡፡
የጉዳዩ ብዛት ከሰው ኃይሉ ጋር እንዳይመጣጠን አድርጎታል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱና የማይሄዱ ጉዳዮች የሚለዩበት የአሰራር ሥርዓት ቢዘረጋ ግን ችግሩ እንደሚቀረፍ ትናገራለች። በአንድ ዓመት ተኩል የሥራ ቆይታዋ ያገኘቻቸውን ልምዶች ለወደፊት ሥራ እንደሚጠቅማት አስታውቃለች፡፡ ዳኞች የሚታሙባቸውን በጥቅም ፍትህ የማዛባት ጉዳይ ላይም ወጣት ደራሩቱ እንደተናገረችው ሁሉንም በእኩል ማየት ባይቻልም ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ መኖራቸውን በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምታለች።
‹‹እኔ ግን እንዲህ ያለው ነገር ውስጥ እንደማልገባ አረጋግጣለሁ›› በማለት ጠንካራ አቋም እንዳላት ተናግራለች፡፡ ህዝቡም ከዚህ ቀደም የሚያውቀውን ብቻ ይዞ ከመናገር እንደርስዋ ለፍትህ ለመስራት የተዘጋጁትንም ለማየት ጥረት እንዲያደርግ መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡ ‹‹ጉቦ የሚሰጥ ከሌለ ጉቦ ተቀባይ ስለሌለ ፍትህ ፈላጊው ጉቦ እንዳይሰጥ ነው የምለው›› በማለትም ጉቦ ባለመስጠት ምንጩን ማድረቅ እንደሚቻልና ጉቦ መስጠት ባይለመድ የህግ ባለሙያውም ኃላፊነቱን በሚገባ እንደሚወጣ አስረድታለች፡፡
ወጣት ደራርቱ ራዕይዋ በህግ ሙያ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሀገር እስከመምራት ደረጃ ለመድረስ ከወዲሁ ጠንክራ ለመስራት ተዘጋጅታለች፡፡ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ በህግ ተመርቆ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ አጋዥ ዳኛ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ወጣት ሰምበቶ ጡቃ ከተሿሚዎቹ ዳኞች መካከል ነበር፡፡ ህዝቡ የፍትህ አካል መኖሩን እንጂ ፍትህ እንደሌለ ሲናገር ይሰማል፡፡ ‹‹የዛ ጉበኛ ልጅ›› እየተባሉ ስም የወጣላቸው ልጆችም መኖራቸውን ያስታውሳል፡፡ ‹‹ዳኛና ጠመንጃ አፍ ውስጥ ካልተከተተ አይናገርም›› የሚል የቆየ አባባል እንዳለ እና እንዲህ ያለው አባባል ዛሬም ከህዝቡ አዕምሮ እንዳልወጣ ይገልጻል፡፡ አባባሉን ለማስቀረትም ሆነ ህዝቡ በፍትህ ላይ እምነት እንዲኖረው ሰርቶ ለማሳየት ዝግጁ መሆኑን ወጣቱ ተናግሯል፡፡
‹‹እኔ ዝግጁ ስሆን መንግሥትም የሚጠበቅበትን ማሟላት አለበት›› የሚለው ወጣት ሰምበቶ የህግ ባለሙያዎች ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲሰሩና በጥቅምም እንዳይደለሉ መንግሥት ጥበቃ በማድረግም ሆነ ጥቅማጥቅሞቻቸው እንዲከበሩላቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ወጣት ሰምበቶ የህግ ባለሙያው ጥቅም ይከበር ቢልም፤ የተማረውም ሆነ ቃል የገባው ህዝቡን ለማገልገል በመሆኑ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም መብቱን ይጠይቃል፡፡ የማህበረሰብ ግንዛቤን የማሳደግ ስራ መሰራት እንዳለበትም በአጭር ጊዜ የሥራ ቆይታው ተገንዝቧል። በቤተሰብ እና በጓደኛ አማላጅነት ጉዳያቸው እንዲፈጸምላቸው የሚጠይቁ፣ ዳኛው እንደፈለገ ፍርድ የሚሰጥ የሚመስላቸው ጥቂት እንዳልሆኑ ያስረዳል። እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች ቀደም ሲል በነበሩ አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች የተለመዱ እንደሆኑ ይገልጻል። በአጠቃላይ ችግሩን ለመፍታት የህብረተሰቡን ንቃተሂሊና የሚያሳድግ ሥራ መስራት እንደሚገባ ተናግሯል። ‹‹ህዝብ በሚያውቀው ህግ መተዳደር ስላለበት ህጉን እንዲያውቅ መደረግ አለበት›› ብሏል፡፡
ሌላው ተሿሚ ወጣት ሚነወር ተማም ይባላል። ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በ2009ዓ.ም ነው በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው፡፡ የህግ ሙያን ስለሚወድ በምርጫው ነው የተማረው። ሙያው ጥንቃቄን እንደሚፈልግም ያውቃል። የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ህዝቡን ለማገልገል ተዘጋጅቷል። ‹‹የፍትህ ሥርአቱ ገለልተኛ አይደለም፡፡ የመንግሥት ጣልቃብነት አለበት፡፡
በጫና ውስጥ ነው የሚሰራው›› ሲባል እንደሚሰማ የሚናገረው ወጣት ሚነወር ተቋሙ ኃላፊነቱን እንዲወጣም የህግ ባለሙያው ድርሻ መኖር እንዳለበት ያምናል፡፡ እርሱም በፍትህ ሥርአቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ ሀገር የሚያድገው ጠንካራ የፍትህ ሥርአት ሲኖር እንደሆነም ይገልጻል፡፡
ወጣት ሚነወር በሰሜን ሸዋ ደራ በሚባል አካባቢ የስምንት ወር የሥራ ልምድ በማግኘቱም በቆይታው ለወደፊት ሥራው የሚረዳው ተሞክሮ አግኝቷል፡፡ ወጣት ዳኞቹ ትኩስ ጉልበታቸውንና ንጹህ አዕምሯቸውን ተጠቅመው በፍትህ ሥርአቱ ውስጥ አሻራቸውን ለማሳረፍ ከወዲሁ ያላቸው ዝግጁነት ያስደስታል፡፡ በፍትህ ሥርአቱ ላይ እምነት ያጣውን የህብረተሰብ ክፍልም ለመካስ ተዘጋጅተዋል፡፡
በሹመት ሥነ ስርአቱ ላይ ያገኘናቸው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻም በወጣቶቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ተሿሚዎቹን አስመልክተው እንዳስረዱት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቀው እንደወጡ ለ10 ወራት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ረዳት ዳኛ ሆነው እንዲሰሩም ተደርጓል፡፡ በሥነ-ምግባራቸውም የተመረጡ በመሆናቸው ለክልሉ የዳኝነት ሥራ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ የዳኝነት ሥርአቱ ወደ ወረዳ በመውረዱም ዳኞቹ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ወጣቶች መሆናቸው ደግሞ የተሻለ ውጤት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በለምለም መንግሥቱ