ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአትሌቲክሱ ዓለም በተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ውዝግብ ውስጥ ሲገባ መመልከት ተለምዷል። በስፖርቱ በርካታ ዓመታት ታሪክ ውስጥ አሯሯጮች ቀርተው በቴክኖሎጂ እየተተኩ አዳጋች የተባሉ የዓለም ክብረወሰኖች በተደጋጋሚ እየተሰበሩ መገኘታቸውን ተከትሎ ብዙ ውዝግብ ሲነሳ ይስተዋላል።
አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ላይ እያሉ ከሚጠጡት ውሃ ጀምሮ ሃይል ሰጪና የተሻለ ፈጣን ሰዓት እንዲያስመዘግቡ እንዲረዳቸው ተደርጎ በቴክኖሎጂ እየታገዙ መምጣታቸው የመከራከሪያ ሃሳቦች እንዲነሱ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር የመሮጫ ጫማዎች እጅግ እየዘመኑና እየተራቀቁ መምጣታቸው ለአትሌቶች ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ አከራካሪ አጀንዳ ነው።
ቀደም ባሉት ዓመታት በተለመዱ የመሮጫ ጫማዎችና በተፈጥሯዊ መንገድ በሚባል ደረጃ አትሌቶች የሚያስመዘግቧቸው የዓለም ክብረወሰኖች በዚህ ዘመን በቴክኖሎጂ ታግዘው በሚሮጡ አትሌቶች መሰበራቸው ፍታዊ አለመሆኑን በማንሳት ምክንያታዊ ሙግት የሚያነሱ ጥቂቶች አይደሉም። በአንጻሩ አትሌቲክሱ እንደሌሎች ስፖርቶች ሁሉ ከዘመኑ ጋር መራመድ እንጂ በነበረበት መቀጠል አይገባውም የሚሉ በርካቶች ናቸው። በተለይም አትሌቶች እንደየአቅማቸውና ስፖንሰር እንደሚያደርጋቸው የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ውድድር ላይ የሚጠቀሙት ጫማ በውጤት ረገድ ተጨባጭ ልዩነት እየፈጠረ መምጣቱ በህግና በደንብ ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ የሚያምኑ በርካታ እየሆኑ መጥተዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የአትሌቶች የመሮጫ ጫማን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ህጎችን ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የአትሌቶች የመሮጫ ጫማን በተመለከተ የሚነሳው ጠንካራ ሙግት ሚዛን የሚደፋ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎም የዓለም አትሌቲክስ በጉዳዩ ዙሪያ ህግ ለማውጣት ተገዷል። ከቀናት በፊትም ይህንኑ በተመለከተ አዲስ ህግ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም በመም ውድድሮች ላይ አትሌቶች የሚጠቀሙት ጫማ የሶሉ ውፍረት ከ20 ሚሊ ሜትር እንዳይበልጥ የሚደነግግ ሲሆን እኤአ ከ2024 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጀምሮ ህጉ ተግባራዊ እንደሚሆን አሳውቋል፡፡
በዚህ ህግ መሰረት የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባያዎች በምርቶቻቸው ላይ ማሻሻያ ለማድረግ በቂ ጊዜ እንዳላቸው የገለፀው የዓለም አትሌቲክስ፤ በአሁኑ ወቅት አትሌቶች በመም ውድድሮች የሚጠቀሙት የመሮጫ ጫማ ሶል ውፍረት ከ20 እስከ 25 ሚሊ ሜትር እንደሚወፍር አስታውሷል፡፡ ማራቶንን በመሳሰሉ የጎዳና ላይ ውድድሮች አትሌቶች የሚጠቀሙበት የመሮጫ ጫማ ሶል ውፍረት 40 ሚሊ ሜትር እንደሆነም ጠቁሟል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ የአትሌቶች የመሮጫ ጫማን በተመለከተ ይህን ህግ ይፋ ያድርግ እንጂ አትሌቲክሱ ከዘመኑ ጋር የሚጓዝበትንና በውድድሮች ላይ ቴክኖሎጂዎችን አትሌቶች በፍትሃዊ መንገድ የሚጠቀሙበትን አሰራር ዘርግቶ ለውዝግቦች መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርግ ሮይተርስና ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ ያወጡት ዘገባ ያመለክታል፡፡
እየተራቀቁ የመጡ የመሮጫ ጫማዎች በመምና በጎዳና ላይ ውድድሮች በርካታ ክብረወሰኖች እንዲሻሻሉ የጎላ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፤ ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኖርዌያዊው የአራት መቶ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪ ካርስቲን ዋርሆልም በራሱ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ0ነጥብ76 ሰከንድ ካሻሻለ በኋላ የመሮጫ ጫማ ቴክኖሎጂ የፈጠረውን ልዩነት መናገሩን ጠቁሟል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ እኤአ በ2024 የዓለም ቻምፒዮና ተግባራዊ እንደሚሆን ይፋ ያደረገውን የመሮጫ ጫማ ህግ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የመሮጫ ጫማ ጉዳይ በእያንዳንዱ የውድድር አይነት ህግና ደንቦችን ለማውጣትና ለመሞከር በሂደት ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግም በቅድመ ውድድር ወቅት የአትሌቶች ጫማ ላይ ትኩረት አድርጎ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ የሰው ኃይል እንደሚመደብ ተጠቁሟል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም