የአሁኑ ትውልድ ትዕግስቱ አፍንጫው ስር ነው። የሆነ ረብ የሌለው ወሬ ስታወራለት ከሰማ አልያም የምታወራው አልጥምህ ካለው ፈጥኖ “አቦ አታዝገኝ” ይልሀል። የወሬ ብቻ አይደለም፤ የአመለካከት ዝገትም አለ፤ በዱሮ በሬ ልረስ የሚል አይነት። በዚህ መንገድ ሀገርንና ህዝብን መመልከት ዝገት ነው።
አዎ በዚህ መንገዳቸው እነዚያ ዝገቶች ሊያዝጉን እየሞከሩ ናቸው። የእነሱ በሽታ ዝገት ነው። ዝገዋል። የዛገ ደግሞ ረብ የለውም፣ ካልተጠረገና ካልፀዳ ሌላውንም ይጎዳል፤ ራሱንም በልቶ ይጨርሳል። ዝገት ነው። ለዚህ ሁሉ መነሻቸው መዛጋቸው ነው።
ከላኛው መንደር ተነስተው አገርን የሚበጠብጡት በዝገት ምክንያት ነው። ከዛጉ አይበጁ ነውና በዝገታቸው ሊያዝጉን እየሞከሩ ናቸው። ለራሳቸው የማይበጅ ህዝቤ ለሚሉትም የማይጠቅም ተልካሻ ስራ ላይ ተጥደዋል። መዛግ በሁለት መልክ ይታያል፤ ከአገልግሎት ውጪ መሆን አልያም መበላሸትን ሊወክል ይችላል።
ዝገት የሶስት ነገሮች ውህደት ነው። ዝገት የሚሉት ቃል በሌላም መልክ የእነዚህን ባህሪ በደንብ ይገልፃል። ዝሙት፣ ገንዘብና ትዕቢት ብቻ ነው የሚፈልጉት። አዎን እነዚህ ሰዎች ዝገዋል። የእነዚህ ሰዎች መነሻና መጥፊያም ይሄው ነው። ይህን ቃል ብትንትን አድርገን እንየውማ።
ግንባር ላይ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ጠላታቸውን ብትንትኑን ሲያወጡት አላያችሁም፤ የዛጉትን ሲበታትኑ አልተመለከታችሁም? አንዳንዱ ዝግት የበላው ጸድቶም የማይጠቀም ነው፤ ይሰባበራል፤ ከአፈር ይቀላቀላል። መልሶ ሊያገለግል አይችልም፤ ታዲያ እኛ ዝገት የተሰኘውን ቃል ብትንትን አድርገን ብናይ ምን ይለናል። ዝ….ገ…ት ከመጨረሻው ፊደል እንጀምር።
ሰዎቹ የኔ ነገር ተሳስቼ ሰዎቹ አልኩኝ። ከስብዕና ከራቁ ቆይተው የለ እንዴ፤ የምን ሰዎቹ ዝገቶቹ ይባሉ እንጂ። ለዚህ ሁሉ መነሻቸው የሆነ ባህሪያቸው ትዕቢት ነው። እነዚህ ዝገቶች ትዕቢት ዋንኛ መገለጫቸው ነው። ከጅምሩ ብንመረምር ውስጣቸው የሞላው ትዕቢት ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገርን እንዲንቁ አደረጋቸው። ምክንያቱም ትዕቢት እውነት ፈፅሞ አያሳይማ።
ትዕቢት ከኔ ወዲያ ሌላ ምንድነው ያስብላል። በትእቢት ሰክረው በትዕቢት አብደው ትቢያ ለብሰውም ከኛ ወዲያ ላሳር የሚሉት ለዚህ ነው። ይህ ትዕቢታቸው ከፍ ያለ ዋጋ አስከፈላቸው። ችግሩ ግን ትዕቢት አሁንም ዋንኛ ባህሪያቸው መሆኑ ላይ ነው፤ እስኪጠፉ የማይላቀቃቸው የማይተዋቸው ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው።
እነርሱ ያልመሯት አገር፣ እኛ የማናስተዳድራትን ኢትዮጵያ ፈፅሞ ማየት አንፈልግም፣ ሲኦልም ገብተን ቢሆን እናፈርሳታለን ያስባላቸውም ይሄው ትዕቢታቸው ነው። ትናንት ለግጭትና ለጦርነት ሲያሟሙቁ ተው ሲባሉ አልሰማ ያሉት፣ እናቶች ተንበርክከው እያለቀሱም ጭምር ግጭት ይቅር ሲሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት በትዕቢታቸው ነው። የሚችሉ መስሏቸው የማይችሏትን ኢትዮጵያ ጦርነት መግጠም የጀመሩትም በዋንኛው የትዕቢት ባህሪያቸው የተነሳ ነው።
ትዕቢተኛ ስትሆን ውስጥህን በትዕቢት ስትሞላው ምድር ላይ ያለ እውነት ይደፈንብሀል፤ ሀቅ የሚሉት ጉዳይ ምንህም አይሆንም። ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንዲሉ እስኪያጠፋህ ድረስ በትዕቢትህ እሳቤ ላይ ትቆማለህ። ሴጣንንም ከገነት ወይም ከጀነት ያስባረረው ትዕቢቱ እንደ ሆነ ሁሉ እነዚህን ዝግጅቶችም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ልብ ያወጣቸው ትዕቢታቸው ነው።
ሕወሓትም ትዕቢት ወጥሯት በትዕቢት አብዳ እየተቅበዘበዘች ትገኛለች። ይሰውረን ነው። የዝገታቸው ሌላኛው ባህሪ ለገንዘብ ያላቸው ከፍ ያለ ፍቅር ነው። ገንዘብ ለማግኘት ያልሄዱበት ርቀት የለም። ህጋዊም ህገወጥም። ይህቺ አገር እጅግ ሀብታም መሆኗን ማወቂያው አንዱ መንገድ ሕወሓቶች ዘርፈው ዘርፈው የያዙትን ገንዘብ አውጥተው አውጥተው መጨረስ አለመቻላቸው ነው።
ያልዘረፉት፣ ያልሸጡት የአገሪቱ ሀብት የለም። ከመርከብ እስከ ሊጥ ዘርፈዋል። ይህም የዚህችን አገር ሀብትና ንብረት በመስረቅ ሀብት ለማካበት ያላቸው ፍቅር ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያመለክታል። የጁንታው አንድ የጦር መሪ ሰሞኑን በራሱ ወታደሮች ተሳለቀ አሉ። ምን ብሎ አትሉኝም።
“እኛ ፌደራል ላይ እያለን የምንሰርቀው መርከብ፣ አውሮፕላን ነበር፤ ዘንድሮ ሊጥ ሰርቃችሁ ትልቁ የሌብነት ልምዳችን አኮሰመናችሁት” አለ አሉ። ነብሱን አይማረውና እንዲህ ያለው የጦር መኮንን ባለፈው ሲዶልቱ በጀግኖቹ ልጆቻችን ወደ ሲኦል ከተሰኙት ውስጥ ነው አሉ፤ ይህንን ያለው።
እናም ልክስክስ ያደረጋቸው የገንዘብ ፍቅራቸው ነው። እንደፈለኩ ካልዘረፍኩ እንደፈለገኝ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ካልዘወርኩ በፍፁም አብሬ አልኖርም ብለው አይደል ተለቃቅመው ሄደው መቀሌ የከተሙት። አሰባችሁት ምን ያህል እየዘገኑ ሆዳቸውን ሲሞሉ ሌላውን ሲያስርቡ እንደነበር። አውሮፓውያን አብረው የሚያላዝኑት ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ገንዘብ የተሞሉት ባንኮቻቸው እንዳይራቆቱ ሰግተው ነው።
የገንዘብ ፍቅር አሳውሯቸዋልና በሰፊው ያላግባብ ማግበስበስ በህገ ወጥ መንገድ ማጋበስ የለመዱት የሌብነት ባህሪያቸው ነው፤ አሁንም በእዚሁ መንገድ ከእነ ዝገታቸው ሆነው ሊዘርፉን ይፈልጋሉ፤ ስልት ሳይቀይሩ። በእርግጥ ገንዘብን እንዳፈቀሩ ወደመዳረሻቸው ሲኦል እየተሸኙ ነው። የዘረፍዋት ሀብታሟ አገር ኢትዮጵያ ከእነሱ ተገላግላ ሁሌም በከፍታ ትወነጨፋለች።
ሶስተኛው የእነዚህ ዝገቶች ባህሪ ዝሙተኝነት ነው። በእርግጥ በፌደራል መንግስት ስልጣን ላይ እያሉ ትልልቅ ባለስልጣኖቻቸው ጭምር በዚህ ባህሪያቸው እጅጉን ይታወቁ ነበር። በዘረፉትና እንዳሻቸው ያዙበት በነበረው አገር ላይ ቅንጡ ሆቴሎችን እያዘጉ አስፀያፊ ተግባሮችን ይፈጽሙ እንደነበር ደጋግመን ሰምተናል።
ይህ የዝሙት አባዜ ተራው ታጣቂ ድረስ የዘለቀ መሆኑን በአማራና አፋር ክልል ወረራቸው ወቅት በሚገባ ተረድተናል። ታጣቂዎቻቸው እና መሪዎቻቸውም ጭምር ሊጥ እየሰረቁም ይዘሙታሉ፤ ጨቅላ ህጻናት፣ መነኩሴ ጨምሮ በርካታ ሴቶችን ደፍረዋል። ለዚያውም በመሳሪያ እያስገደዱ፤ በቡድን።
እነዚህ ነውረኞች አያቶቻቸው ሊሆኑ የሚችሉ እናቶችን ደፍረዋል። መነኩሴን (ስጋቸውን ጠልተው ለነብሳቸው ያደሩ፤ አለም በቃኝ ያሉ እናትን) ተፈራርቀው ደፍረው ንፅህናቸውን አቆሽሸዋል። ህሊና ሲከዳ ስብዕና ሚዛኑን ይስታል፤ ማስተዋል ይርቃል።
አይን ከተጨፈነ በእውር ድንብር መጓዝ መድረሻ ሳያውቁ መዋከብ ውስጥ ያስገባል። ከሰሞኑ በየመገናኛ ብዙኋኑ እየተላለፈ ያለው የሽብርተኛው ቡድን ሕወሓት የፈፀማቸው አስነዋሪ ተግባሮች የሰው ልጅ አደረጋቸው ተብለው ለማመን የሚከብዱ ጭካኔዎች ወደ ኋላ ብዙ እንድናስብ የሚያደርጉን ናቸው። እውነት ሰው የሚባል ፍጡር ከሰዎች የተገኘ ስብዕና የተቃባ ለዚያውም ኢትዮጵያ በምትባል ምድር ላይ የበቀለ ይህንን ያደርጋል ቢባል ለማመን የሚከብድ ግን ደግሞ ያደረጉት ሆኗል።
እነዚህ ከሀዲዎች ሰው ሳይሆኑ ሰው የሚመስሉ በጥላቻ ያበዱ፣ በተንኮል የሰለጠኑ/ የሰየጠኑ ቢባል ይሻላል/ በዘራፊነት የታወኩ ተስፋ የቆረጡ ግብስብሶች መሆናቸውን አስመስክረዋል። ሰዎቹ ከስብዕና ርቀዋል፣ ሰው ከመሰኘት ወርደዋል፣ ሰዋዊነትን ተሰናብተዋል። ቦታ እና ተቋም ሳይለዩ ሁሉንም በየደረሱበት ያገኙትን ሁሉ አውድመዋል፤ የሀይማኖት ተቋማትን ተዳፍረዋል፣ አማኞችን ከመድፈር እስከ መግደል ደርሰዋል፤ ትምህርት ቤቶችን የጤና ተቋማትን፣ ኢንዱስትሪዎችን ዘርፈዋል፤ የተረፈውን አውድመዋል። ይህ ሁሉ የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አባዜ ነው።
እነሱ ሀገር ካልገዙ ሀገሪቱ መፍረስ አለባት እንዳሉት ለማፍረስ ሞክረዋል። ይሄ ዝገትነት ነው፤ በቀላሉ ሊለቅ የማይችል፤ ተፈረካክሶ የሚያልቅ። እነሱም እንደዚያ እየሆኑ ናቸው። ሀገራችን በእነዚህ ዝገቶች ጨርሶ አትበላም። እኛ ልጆችዋ አለንና ዝገቶችን እናፀዳለን፤ ከስራ ውጪ እናደርጋለን፤ በተባበረ ክንዳችን ይደቆሳሉ። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁሌ አሸናፊ ነንና።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014